የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ

ከ 4 ሰአት በፊት

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማርኮ ሩቢዮ በቱርክ በሚካሄደው የዩክሬን-ሩሲያ የሰላም ድርድር ብዙ ተስፋ እንደሌላቸው እና ለውጥ እንዲኖር ዶናልድ ትራምፕ እና የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መገናኘታቸው አስፈላጊ መሆኑን ተናገሩ።

በደቡባዊ ቱርክ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ ላይ ከተገኙ በኋላ “ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ፑቲን በቀጥታ በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ እስካልተወያዩ ድረስ እዚህ ለውጥ የምናገኝ አይመስለኝም” ብለዋል።

ቮሎድሚር ዜሌንስኪ አገራቸው በኢስታንቡል ለሚደረገው ውይይት ልዑካንን እንደምትልክ አረጋግጠው፤ ነገር ግን በሞስኮ የተላከውን “ዝቅተኛ ደረጃ” ያለው ልዑካን ነው ሲሉ ነቅፈዋል።

የፑቲን የቅርብ ረዳት የሆኑት ቭላድሚር ሜዲንስኪ በቡላቸው የክሬምሊን ቡድን “ሁሉም አስፈላጊ ብቃቶች” እንዳለው ተናግረዋል።

መካከለኛው ምሥራቅን እየጎበኙ ያሉት ትራምፕ ቀደም ብለው እርሳቸው እና ፑቲን በአካል እስኪገናኙ ድረስ በሰላማዊ ንግግሮቹ ላይ ከፍተኛ መሻሻል የማይታሰብ መሆኑን ጠቁመዋል።

በሩሲያ የልዑካን ቡድን ቅር ተሰኝተው እንደሆነ ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “እኔና ፑቲን እስክንገናኝ ድረስ ምንም ነገር አይከሰትም” ብለዋል።

“እኔ ከሌለሁ አይሄድም። እናም እኔ እና እሱ እስክንገናኝ ድረስ ተወደደም ተጠላም ምንም ነገር ይከሰታል ብዬ አላምንም። ነገር ግን ብዙ ሰዎች እየሞቱ ስለሆነ መፍትሄ ማግኘት አለብን” ሲሉ አክለዋል።

ትራምፕ “ተገቢ” ከሆነ አርብ በቱርክ በሚደረጉ ንግግሮች ላይ እንደሚሳተፉ ቢናገሩም በኋላ ግን ወደ ዋሽንግተን እንደሚመለሱ ገልጸዋል።

ከቱርክ፣ ከአሜሪካ፣ ከዩክሬን እና ከሩሲያ የተወጣጡ ልዑካን እአአ ከ2022 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት በዩክሬን-ሩሲያ ጉዳይ ሐሙስ ዕለት ኢስታንቡል ውስጥ ሊገናኙ ነበር። አንዳንድ ዘገባዎች አርብ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

ቭላድሚር ፑቲን የአውሮፓ መሪዎች እና ዩክሬን ለ 30 ቀናት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ላቀረቡት ጥሪ ምላሽ በመስጠት ግንቦት 15 በኢስታንቡል ቀጥተኛ ውይይት እንዲደረግ ጠይቀዋል።

ዜለንስኪ ፑቲንን በአካል እንዲገኙ ቢጠይቁም ክሬምሊን ግን ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቀው ፕሬዝደንቱ የቡድኑ አካል አለመሆናቸውን ገልጿል።

የፕሬዚዳንት ፑቲን ረዳት እና የድርድሩ መሪ የሆኑት ቭላድሚር ሜዲንስኪ

ዜሌንስኪ በአንካራ ከኤርዶዋን ጋር ያደረጉትን የሁለትዮሽ ውይይትን ተከትሎ ከፍተኛ የሩስያ ልዑካን ቡድን ባለመኖሩ ሞስኮ ለትራምፕ እና ለኤርዶዋን “ክብር አላሳየችም” በማለት ከስሰው የሩስያው ፕሬዝዳንት በግል እንዲያገኙቸው ደግመው ጠይቀዋል።

“የስብሰባው ጊዜ አልተያዘም፤ አጀንዳ የለም፤ የልዑካን ቡድን የለም። ይህ ኤርዶዋንን እና ትራምፕን አለማክበር ነው።”

ሜዲንስኪ በበኩላቸው በኢስታንቡል ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ሩሲያ በጎረቤቷ ላይ ወረራ ከጀመረች በኋላ በ2022 የተካሄደውን ያልተሳካ ድርድር “ቀጣይ” አድርጋ ታየዋለች።

“ከዩክሬን ወገን ጋር ቀጥተኛ ድርድር የማድረግ ተግባር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የግጭቱን መሰረታዊ መንስኤዎች በማስወገድ ዘላቂ ሰላም መፍጠር ነው” ብለዋል።

ሐሙስ ዕለት በዜለንስኪ እንደተገለጸው ከሆነ የዩክሬን የልዑካን ቡድን በመከላከያ ሚኒስትሩ ሩስተም ኡሜሮቭ ይመራል። የስለላ ምክትል ኃላፊዎችን፣ ወታደራዊ ጄኔራሎችን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ያካትታል።

እአአ በ 2022 ከዩክሬን ጋር ተጀምሮ ያልተሳካውን ድርድር የመሩት ሜዲንስኪ የሩሲያ ልዑካንን እንደሚመሩ የክሬምሊን መግለጫ ዘግቧል ።

የሩሲያ ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር፣ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና የወታደራዊ መረጃ ኃላፊም ይገኛሉ።

የኢስታንቡል ውይይት እአአ በ2022 ካልተሳካው ሙከራ በኋላ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል የተደረገ የመጀመሪያው ቀጥተኛ ድርድር ነው።

ሩሲያ ድርድሩ ካቆመበት መቀጠል እንደምትፈልግ አመልክታለች።

በድርድር ላይ ያሉት ጉዳዮች ዩክሬን ገለልተኛ አገር እንድትሆን፣ የወታደራዊ ኃይሏን መጠን እንድትቀንስ እና የኔቶ አባልነት ፍላጎት እንድትተው የሚጠይቁትን ጥያቄዎች ያጠቃልላል። ዩክሬን እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች ደጋግማ ውድቅ አድርጋለች።

በዩክሬን የሚካሄደው ውጊያ የቀጠለ ሲሆን ሩሲያ ሐሙስ ዕለት በምሥራቅ ዶኔስክ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ሁለት መንደሮችን መያዟን ተናግራለች።

ሞስኮ በ2014 በህገ ወጥ መንገድ የቀላቀለችውን ደቡባዊ ክራይሚያ ልሳነ ምድርን ጨምሮ 20 በመቶ የሚሆነውን የዩክሬን ግዛት ትቆጣጠራለች።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ጆን ሄሌይ የዩክሬን አጋሮች በፑቲን ላይ ጫና እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐሙስ ዕለት በበርሊን ከጀርመኑ አቻቸው ቦሪስ ፒስቶሪየስ ጋር ከተገናኙ በኋላ ባደረጉት ንግግር ሄሌይ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ በመጣል “ወደ ድርድር ጠረጴዛው” እንዲመጡ ማድረግ ይገባል ብለዋል።