
ከ 4 ሰአት በፊት
በሁለት አህጉር የሚገኙ ተመራማሪዎች ከብርቱካናማ ወንድ ድመት ዘረ መል ጀርባ ያለውን ምስጢር እንደደረሱበት ገለፁ።
ሳይንቲስቶቹ ብርቱካናማ ድመቶች በጂናቸው ውስጥ ለቆዳቸው፣ ዓይናቸው እና ለፀጉራቸው ቀለም አስተዋጽኦ የሚያደርገው ህዋስን እንደሚያጡ ተናግረዋል።
ይህ ግኝት ምርመሩን ረዥም ጊዜ ሲከታተሉ ለነበሩት ተማራማሪዎች እና ምርምሩን በገንዘብ የደገፉ የድመት አፍቃሪዎችን ያስፈነጠዘ ዜና ሆኗል።
ተመራማሪዎቹ ይህንን እንቆቀቅልሽ መፍታት መቻላቸው እነዚህ ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ድመቶች ለተወሰኑ ጤና ስጋቶች ተጋላጭ መሆን አለመሆናቸውን ለማወቅ ይረዳል ብለዋል።
ለረዥም ዓመታት ድመቶች ብርቱካናማ ቀለም የኖራቸው በጂናቸው የተነሳ መሆኑ ይታወቅ ነበር።
ነገር ግን በዘረ መል መዋቅር ውስጥ የት ቦታ ይህ እንደተከሰተ ከሳይንቲስቶቹ ተሰውሮ ቆይቷል።
በጃፓን የኪዩሹ ዩኒቨርሲቲ እና በአሜሪካ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሚገኙ የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን ሐሙስ ዕለት በተመሳሳይ ጊዜ በታተሙ ወረቀቶች ላይ ምስጢሩን ይፋ አድርገዋል።
ቡድኖቹ ያገኙት ነገር ለድመት ቆዳዋን፣ ፀጉሮቿን እና የዓይኖቻቸውን ቀለም የሚሰጠው ሜላኖይተስ የተባለው ዘረ-መል (ARHGAP36) ህዋሶቻቸው ውስጥ የበለጠ ንቁ ሆነው ታይተዋል።
ጂኖች የድመት ህዋሶች (ሴሎች) ልክ እንደ ሌሎች ሕያው ፍጥረታት፣ እንዴት መስራት እንዳለባቸው መመሪያዎችን ከሚሰጡ የዘረ መል ቅንጣቶች የተሠሩ ናቸው።
ከበርካታ ብርቱካናማ ፀጉር ያላቸው እና የሌላቸው ድመቶች ዘረመሎችን በመውሰድ እና በማነፃፀር በሰሩት ጥናት ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ድመቶች በARHGAP36 ጂናቸው ውስጥ የዘረመል ኮድ ክፍል መጉደሉን ተገንዝበዋል።
ያለዚህ ዘረመል የARHGAP36 እንቅስቃሴ የበለጠ ንቁ ነው። የሳይንስ ሊቃውንት ጂን እነዚያ ሜላኖይቶች ቀለል ያለ ቀለም እንዲያመርቱ እንደሚያዝ ያምናሉ።

ለአስርታት ዓመታት ብርቱካናማ ቀለም ያላቸው ድመቶች አብዛኛውን ጊዜ ወንድ እንደሚሆኑ አስተውለዋል።
ይህ ደግሞ በኤክስ ክሮሞዞም ላይ በሚገኘው የጂን ዓይነት የሚከሰት ነው።
ክሮሞዞሞች የዘረመሎች አብዛኛው ክፍል ሲሆኑ ልክ እንደ ሌሎች አጥቢ እንስሳት ሁሉ ድመቶችም የተለያየ ቁጥር ያላቸው ጂኖችን የሚይዙ ኤክስ እና ዋይ ክሮሞዞም አላቸው።
በዚህ ምርምር ላይ እንደታየው ለድመቶቹ ቀለም ወሳኝ የሆነውን ቀለም የሚይዘው በኤክስ ክሮሞዞም ላይ የሚገኝ ጂን ሲሆን በዘረ መል ላይ የሚጎድል አንድ ጂን ድመቱን ሙሉ በሙሉ ቡናማ ለማድረግ በቂ ሆኖ ተገኝቷል።
በንጽጽር ሴት ድመቶች ሁለት የኤክስ ክሮሞዞም ያላቸው ሲሆን፣ የበለጠ ቀለል ያለ ቀለም እንዲኖራቸው ዘረመሉ በሁለቱም ክሮሞዞሞች ላይ መጥፋት ይኖርበታል።
በዚህም የተነሳ የተቀላቀለ ቀለም ያላቸው ድመቶች የመኖራቸው ዕድል ከፍ ይላል።
እነዚህ ብርቱካናማ እና ጥቁር ቀለም ያላቸው ድመቶች በልጅነታቸው በሁለቱም ህዋሶች ውስጥ የሚገኝ የኤክስ ክሮሞዞም በአጋጣሚ ጠፍቷል” ሲሉ የኪዩሹ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ሂሮዩኪ ሳሳኪ አብራርተዋል።
“ሕዋሶቹ በተከፋፈሉ ቁጥር፣ የተለያየ ቀለም የሚሰጡ ጂኖች እንዲፈጠሩ የሚያደርግ ሲሆን ይህም የተለየ ቀለም እንዲኖራቸው ያደርጋል”
ፕሮፌሰር ሳሳኪ ጥናቱን መጀመርያ ላይ ሲጀምሩት ለግል ፍላጎታቸው በሚል የነበረ ቢሆንም በኋላ ግን ምርመራቸውን ገፍተውበት በቂ ማብራርያ አስቀምጠውለታል።
ከሚመራመሩበት ዩኒቨርሲቲ ጡረታ የወጡት ሳሳኪ፣ የድመት ወዳጅ በመሆናቸው የብርቱካናማ ድመቶች ጂን “የድመት በሽታዎችን ለማሸነፍ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” በሚል ተስፋ በምርመሩ መቀጠላቸውን ተናግረዋል።
እርሳቸው እና ቡድናቸው ምርምሩን ለማካሄድ በጃፓን እና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ከሚገኙ የድመት ወዳጆች ከ55 ሺህ ዩሮ በላይ ማሰባሰብ ችለዋል።
አንድ ለምርመሩ ስራ ገንዘብ ያዋጣ ታዳጊ “አንደኛ እና ሦስተኛ ክፍል ያለን ወንድማማቾች ነን፤ ከሚሰጠን የኪስ ገንዘብ ላይ ነው ይህንን ያዋጣነው። ሦስት ቀለም ባላቸው ድመቶች ላይ ለሚያደርጉት ምርመር ይጠቀሙበት” ሲል ጽፏል።
የ ARHGAP36 ጂን በአንጎል እና በሆርሞን እጢዎች ላይ እንዲሁም በሌሎች የሰውነት ክፍሎች ላይም የሚሰራ ሲሆን ለእድገት አስፈላጊ ነው ተብሎ ይታሰባል።
ተመራማሪዎቹ በጂን ውስጥ ያለው የዘረ መል ለውጥ በእነዚህ የሰውነት ክፍሎች ላይ ከጤና ሁኔታ ወይም ከቁጣ ስሜት ጋር የተያያዙ ሌሎች ለውጦችን ሊያመጣ ይችላል ብለው ያስባሉ።
የ ARHGAP36 ጂን በሰዎች ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከቆዳ ካንሰር እና ከፀጉር መርገፍ ጋር ይያያዛል።
“ብዙ የድመት ባለቤቶች የተለያዩ ቀለሞች ያላቸው ድመቶች ከተለያየ ስብዕና ጋር የተሳሰሩ ናቸው በሚለው ሀሳብ አበክረው ያምናሉ” ብለዋል ፕሮፌሰር ሳሳኪ።
“ለዚህ እስካሁን ምንም ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም፤ ነገር ግን ትኩረት የሚስብ ሀሳብ በመሆኑ የበለጠ ለመመራመር እፈልጋለሁ።”