
ከ 3 ሰአት በፊት
በ2028 የኦሎምፒክ ጨዋታዎች ወቅት ተመልካቾች በሎስ አንጀለስ ሰማይ በመብረር ከከተማው የትራፊክ መጨናነቅ እንዲድኑ ለማድረግ አዘጋጆቹ ጥረት ማድረግ ጀምረዋል።
የኤልኤ28 አዘጋጅ ኮሚቴ በኦሎምፒክ እና በፓራሊምፒክ ጨዋታዎች ወቅት የበራሪ ታክሲ አገልግሎት ለመስጠት ከአርቸር አቪዬሽን ጋር የትብብር ስምምነት ማድረጉን አስታውቋል።
ኩባንያው ደጋፊዎቸን ለማጓጓዝ በርካታ አውሮፕላኖችን ለመጠቀም ማቀዱን ተናግሯል ሲል ኤልኤ28 ሐሙስ ዕለት ገልጿል።
በራሪ ታክሲዎች ለረጅም ጊዜ ህልም ነበሩ። በ 2024 በፓሪስ ጨዋታዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ለማዋል ቢታቀድም፣ በአውሮፓ አየር ደህንነት ኤጀንሲ ማረጋገጫ አላገኙም።
በተመሳሳይ አርቸር አቪዬሽን እስካሁን ድረስ ከአሜሪካ የፌደራል አቪዬሽን አስተዳደር የምስክር ወረቀት አላገኘም።
በዚህም አውሮፕላኑ ለንግድ አገልግሎት ዝግጁ አይደለም ማለት ነው። መስራቹ እና ዋና ስራ አስፈጻሚው በዚህ ዓመት ከአቪዬሽን ተቆጣጣሪው የዲዛይን እና የደህንነት መስፈርቶችን ያሟላል የሚል ማረጋገጫ ለማግኘት ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ለ2028 ጨዋታዎች የእውቅና ማረጋገጫውን በጊዜው ካገኙ በራሪ ታክሲዎቹ ከ10-20 ደቂቃ በረራዎችን በተመረጡ መዳረሻዎች መካከል ለነዋሪዎች እና ጎብኝዎች ያቀርባሉ።
ይህም ትላልቅ የኦሎምፒክ ጨዋታ የሚዘጋጅባቸውን ቦታዎች ያካትታል።
እያንዳንዱ ጉዞ ምን ያህል እንደሚያስወጣ ግልፅ ባይሆንም የአርቸር አቪዬሽን መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ አዳም ጎልድስቴይን ዋጋቸው ከከፍተኛው የኡበር ዋጋ ጋር እንዲወዳደር እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ሲል ሎስ አንጀለስ ታይምስ ዘግቧል።
ደንበኞች በመተግበሪያ በኩል የበረራ ታክሲውን አገልግሎት መጠየቅ ይችላሉ። አውሮፕላኑ እስከ አራት ሰዎችን ማጓጓዝ የሚችል ሲሆን በሚነሳበት እና በሚያርፍበት ጊዜ ከሂሊኮፕተር ጋር ተመሳሳይ የሆነ ቴክኖሎጂ ይጠቀማል።
ታክሲው የ”ኢቪቶል” አካል ነው። ኢቪቶል በኤሌክትሪክ ሳይነደረደሩ መነሳት እና ማረፍን የሚያመለክት ነው።
በቦይንግ እና በዩናይትድ አየር መንገድ የሚደገፈው አርቸር፣ ለአጭር ርቀት የበረራ አማራጭን በማቅረብ በተጨናነቁ ከተሞች የትራንስፖርት አማራጭን ለመቀየር ከሚንቀሳቀሱ በርካታ የኢቪቶል አምራቾች መካከል አንዱ ነው።
ኢንዱስትሪው የባትሪ ጥንካሬን ጨምሮ ብዙ መሰናክሎች ገጥመውታል። እስካሁን ፈቃድ የተሰጠው በራሪ ታክሲም የለም።
የአርቸር ተሽከርካሪዎች በ12 ሞተሮች እና ሽክርክሪቶች የተሠራ ሲሆን “ከባህላዊ ሄሊኮፕተር ያነሰ ድምጽ እና ልቀትን ያመነጫል” ይላል ኤልኤ28።
አርቸር አቪዬሽን በፌዴራል አቪዬሽን አስተዳደር (ኤፍኤኤ) “እንደ ንግድ አየር መንገዶች የደህንነት ደረጃዎቹ” እንደሚረጋገጥ ተስፋ አድርጓል።
ጎልድስተይን በሰጡት መግለጫ “ሰዎች በሎስ አንጀለስ አካባቢ የሚጓጓዙበትን መንገድ መለወጥ እና የአሜሪካን የወደፊት የመጓጓዣ ሁኔታ የሚቀርፅ ታሪክ ለመሥራት እንፈልጋለን። ይህን ለማድረግ ከኤልኤ28 ጨዋታዎች የተሻለ ጊዜ የለም” ብለዋል።
በራሪ ታክሲዎችን ለማስተዋወቅ የሚሞክሩ ኩባንያዎች ደህንነት፣ ሕጎች እና ኢንቨስትመንት ትልቅ እንቅፋት ሆነውባቸዋል። እንቅፋቶች እና መዘግየቶች ቢገጥማቸውም ብዙዎች የወደፊቱ የመጓጓዣ አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ያምናሉ።
አርቸር አቪዬሽን የ2028 ኦሎምፒክን ከዓለም ጋር የመተዋወቂያ ዘዴ አድርጎ ይመለከተዋል።
የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት የመጀመሪያው በራሪ ታክሲ በ 2026 በዩኬ ውስጥ ይጀምራል ብሏል።
ሎስ አንጀለስ ከዚህ ቀደም እአአ በ1984 እና በ1932 ኦሎምፒክን ያስተናገደች ሲሆን ከተማዋ የክረምት ጨዋታዎችን ስታዘጋጅ ለሦስተኛ ጊዜ ይሆናል።