
ከ 5 ሰአት በፊት
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በጋዛ ባለው የሰብዓዊ ሁኔታ ዩናይትድ ስቴትስ “መረበሿን” ገለፁ።
ሩቢዮ ይህንን ያሉት ሐሙስ ዕለት እስራኤል በጋዛ ሰርጥ በፈጸመችው የአየር ጥቃት ቢያንስ 114 ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጤና ባለስልጣናት ከተናገሩ ወዲህ ነው።
የዓይነ እማኞች እስራኤል በጃባሊያ የስደተኞች መጠለያ በፈጸመችው ጥቃት 13 ሕጻናትን ጨምሮ በርካቶች መገደላቸውን ተናግረዋል።
እስራኤል ዳግም ወታደራዊ ጥቃቷን አጠናክራ ከቀጠለች ወዲህ አስከፊ ነው በተባለው የአየር ጥቃት የተነሳ በርካቶች መገደላቸውን ተከትሎ ሐሙስ ዕለት በደቡባዊ ጋዛ የካን ዮኒስ ጎዳናዎች የቀብር ሥነ ሥርዓት በሚፈጽሙ እና ሐዘናቸውን በሚገልፁ ቤተሰቦች ተሞልቶ ነበር።
በከተማው የተፈናቀሉ ቤተሰቦችን የተጠለሉባቸው ቤቶች እና ድንኳኖች በሌሊት በቦምብ ሲደበደቡ ሴቶችና ሕፃናትን ጨምሮ 56 ሰዎች መሞታቸውን በአካባቢው የሚገኘው ናስር ሆስፒታል አስታውቋል።
የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ጋዛ ሃማስ እና የፍልስጤም እስላማዊ ጂሃድ ተዋጊዎችን መምታቱን አስታውቋል።
አንድ ሰው ለቢቢሲ አረብኛ ሚድል ኢስት ዴይሊ ፕሮግራም እንደተናገረው የናስር ሆስፒታል አስከሬን ማቆያ “ከአቅም በላይ ሞልቷል” እና በርካታ አስከሬኖች ከመቀበራቸው በፊት በኮሪደሩ ላይ መቀመጥ ነበረባቸው ብሏል።
እስራኤል እየወሰደችው ያለውን ወታደራዊ እርምጃ የትራምፕ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ እንደሚደግፍ የተጠየቁት ውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሃማስ እጅ እንዲሰጥ እና ያገታቸውን እንዲለቅ ጫና ለማድረግ የሚፈጸም መሆኑን በመግለጽ ቡድኑ እስካለ ድረስ ዘላቂ ሰላም አይኖርም ብለዋል።
“ይህ ሲባል እኛ በጋዛ ሕዝብ ላይ በሚደርሰው ስቃይ በምንም መልኩ ቸልተኛ አይደለንም፤ ለእነርሱ እርዳታ ለማቅረብ እድሎች እንዳሉ አውቃለሁ” ብለዋል።
እስራኤል ላለፉት 10 ሳምንታት ወደ ጋዛ ምንም ዓይነት የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦቶች ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ ከልክላለች።
የእስራኤል መከላከያ በጋዛ ሊያደርግ ካቀደው ሰፊ ቦታዎችን በቋሚነት መቆጣጠር በፊት የሃማስ ተዋጊዎች እና መሰረተ ልማቶች ናቸው በሚሏቸው ላይ የቦምብ ድብደባውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮ ይህንን አስተያየት የሰጡት በቱርክ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ከተካሄደ በኋላ ነው።
ስብሰባው በጋዛ የእርዳታ መስጫ ቦታዎችን ለማዘጋጀት የግል አቅራቢዎችን ለመጠቀም በእስራኤል እና አሜሪካ የቀረበው አወዛጋቢ ዕቅድ ላይ ለመወያየት ነበር።
ይህንን ዕቅድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀባይነት የሌለው እና ተግባራዊ የማይሆን ሲል ውድቅ አድርጎታል።
ስብሰባው የተካሄደው ዶናልድ ትራምፕ የባሕረ ሰላጤውን አገራት በጎበኙበት ወቅት እና በሃማስ እና በእስራኤል መካከል አዲስ የተኩስ አቁም እና ታጋቾችን የመልቀቅ ስምምነት ላይ ቀጥተኛ ያልሆነ ድርድር እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው።
በሌላ በኩል ሃማስ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ “ሆን ብለው ወታደራዊ ጥቃቶችን በማጠናከር የሚደረጉ የድርድር ጥረቶችን ያበላሻሉ” ሲል ወንጅሏቸዋል።
የእስራኤል መንግሥት ቃል አቀባይ እስራኤል በታጋቾች መፈታት ላይ የሚደረገው ድርድር እንዲሳካ ትፈልጋለች፤ ነገር ግን ያም ቢሆን ሃማስ በወታደራዊ ጫና ውስጥ እያለ ሊካሄድ ይችላል ብለዋል።

ዶክተሮች በአልጋ እጦት ምክንያት የተቃጠሉ፣ የተቆረጡ እና የውስጥ ደም መፍሰስ ያጋጠማቸውን ጨምሮ የቆሰሉትን ሰዎች በቃሬዛ፣ ወንበሮች እና ወለል ላይ ለማከም መገደዳቸውን ተናግረዋል።
“በዛሬው ዕለት ከተገደሉት መካከል 36 ሕጻናት ነበሩ… ሙሉ ቤተሰቦች ከመዝገብ ላይ ተፍቀዋል” ሲሉም አክለዋል።
“በአሳዛኝ ሁኔታ ይህ የጥፋት ደረጃ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን አካል ሆኗል።”
በአካባቢው በሚንቀሳቀስ የመብት ተሟጋች የተጋራው አንድ ቪዲዮ የሕክምና ባለሙያዎች በአካባቢው በሚገኝ የመቃብር ስፍራ በርካታ አስከሬኖችን መሬት ላይ ሲያስቀምጡ ያሳያል።
የእስራኤል መከላከያ ባለፉት ሁለት ቀናት በመላው ጋዛ 130 “የሽብር ዒላማዎችን” መምታቱን ተናግሯል።
ከነዚህም መካከል የተዋጊዎች ቡድኖች፣ የሮኬት ማስወንጨፊያዎች እና የመሠረተ ልማት ቦታዎች እንደሚገኝበት ተገልጿል።
የእስራኤል ጦር በሪማል የተፈናቀሉ ዜጎችን የሚጠለሉበት ሆስፒታል፣ ዩኒቨርሲቲ እና በርካታ ትምህርት ቤቶች የአሸባሪዎች ምሽግ ሆነዋል ሲል ገልጾ በቅርቡ “በጠንካራ ኃይል” እንደሚያጠቃቸው ተናግሯል።
እስራኤል ለ10 ሳምንታት ምንም አይነት እርዳታም ሆነ ሌሎች አቅርቦቶችን ወደ ጋዛ እንዲገባ አልፈቀደችም።
ይህንንም ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች ለረሃብ እንደሚጋለጡ አስጠንቅቋል ።
እስራኤል እርዳታ እንዳይገባ ያገደችው ለሁለት ወራት የቆየውን የተኩስ አቁም ማብቃቱን ተከትሎ ነው።
ሃማስ ቀሪዎቹን 58 ታጋቾች እንዲፈታ ጫና ማድረግ እንደሚጠይቅ የእስራኤል መንግሥት በተደጋጋሚ ይናገራል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እስራኤል በዓለም አቀፍ ሕግ መሰረት ለጋዛ ሕዝብ የምግብ እና የሕክምና አቅርቦቶች መድረሳቸውን የማረጋገጥ ግዴታ አለባት ብሏል።
እስራኤል የዓለም አቀፍ ሕግን እያከበረች እንደሆነ እና የምግብ እጥረት እንደሌለ ተናግራለች።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ጥቅምት 7/2023 ቡድኑ እስራኤል ላይ ጥቃት አድርሶ 1,200 ሰዎች መገደላቸውን እና 251 ሰዎች መታገታቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጦር ሃማስን ለማጥፋት ወታደራዊ ዘመቻ ጀምሯል።
እስካሁን ድረስ በጋዛ ቢያንስ 53,010 ሰዎች በእስራኤል ወታደራዊ ዘመቻ መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።