
ከ 5 ሰአት በፊት
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ዋነኛ ተዋናይ ሆኖ የቆየው ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሁለተኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናው ተሰርዟል።
ምርጫ ቦርድ ረቡዕ ግንቦት 6/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ከሦስት ወራት በፊት በሰጠው ማስጠንቀቂያ መሠረት የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስታውቋል።
የትግራይ ጦርነትን ተከትሎ ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣው ህወሓት፤ አሁንም ከምዝገባ የተሰረዘው ለዚሁ ጉዳይ በመፍትሔነት የተቀመጠው አማራጭን በተመለከተ መግባባት ላይ ባለመደረሱ ነው።
ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ፓርቲውን የሰረዘው የትግራይ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ ህወሓት “በአመጻ ድርጊት” መሳተፉን በመግለጽ ነበር።
ጦርነቱ እንዲያበቃ ያደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት ተፈርሞ በህወሓት ላይ የተጣለው የአሸባሪነት ፍረጃ ከተነሳ በኋላ ፓርቲው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ አቅርቦ ነበር።
ምርጫ ቦርድ በበኩሉ የተሰረዘን ፓርቲ መልሶ ለመመዝገብ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ አለመኖሩን በመጥቀስ የፓርቲውን ጥያቄ ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል። ከብዙ ምልልስ በኋላ የፌደራል መንግሥት ህወሓት “በልዩ ሁኔታ” እንዲመዘገብ የሚያስችለውን የሕግ ማሻሻያ ቢያደርግም ይህም አማራጭ በህወሓት ተቀባይነት አላገኘም።
ፓርቲው የቀድሞው ሕጋዊ እውቅና እንዲመለስለት እንጂ በልዩ ሁኔታ መመዝገብ እንደማይፈልግ ገልጿል። ይህ ክርክር እንዳለ፤ ፓርቲው ከአዋጅ ማሻሻያው በኋላ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ምርጫ ቦርድ ህወሓትን በልዩ ሁኔታ መዝግቦ የምስክር ወረቀት መስጠቱን አስታውቋል።
ለፓርቲው የተሰጠው ሕጋዊ እውቅና ግን አከራካሪ ሆኖ ሰንብቷል። ህወሓት፤ ለቦርዱ ጥያቄ ያቀረበው የቀድሞ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ እንደነበር በመግለጽ በልዩ ሁኔታ የተደረገለትን ምዝገባም ሆነ የተሰጠውን እውቅና እንደማይቀበለው በተደጋጋሚ ገልጿል።
ምርጫ ቦርድ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ፓርቲው ከአዋጁ መሻሻል በኋላ ያስገባው ማመልከቻ ከዚህ ቀደም ከነበረው “በተለየ መልኩ” የቀረበ እንደነበር አስታውቋል። ምርጫ ቦርድ እንደሚያስረዳው ፓርቲው ጥያቄውን ያቀረበው “በልዩ ሁኔታ” ለመመዝገብ “ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት” ነው።

ህወሓት ጥያቄውን ያቀረበው በልዩ ሁኔታ መመዝገብን የተመለከተው ሕግ “ዓላማ እና አፈጻጸምን በግልጽ በማወቅ እና በመረዳ” መሆኑን ጠቅሷል። ጥያቄው የቀረበው በአዋጅ ማሻሻያው ላይ ” ‘በልዩ ሁኔታ’ የፖለቲካ ፓርቲ ሆኖ ለመመዝገብ እንዲቀርቡ በሕጉ የተመለከቱትን ዝርዝር ሰነዶች” በማያያዝ እንደሆነ በቦርዱ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።
ምርጫ ቦርድ፤ “የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በቦርዱ ዋና መሥሪያ ቤት በመገኘት ሰርቲፊኬቱን እና ደብዳቤውን በሚገባ አይተው፣ አንብበው እና ተስማምተው በፈቃዳቸው ፈርመው” መውሰዳቸውን አስታውቋል። ይህ በመሆኑም “ይህ ‘በልዩ ሁኔታ’ ተመዝግቦ የተሰጠን የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫን አንቀበለው ማለት ተቀባይነት የለውም” ሲል የህወሓትን አቋም ተችቷል።
ምርጫ ቦርድ ይህንን እውቅና ከሰጠ በኋላ፤ ፓርቲው በህጉ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ እንዲያደርግ ታኅሣሥ ላይ አሳስቦ ነበር። የካቲት ወር ላይ ደግሞ ይህ ትዕዛዝ አለመፈጸሙን በመጥቀስ ፓርቲውን “ለሦስት ወራት ያገደ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥም “ጠቅላላ ጉባኤ ለማድረግ የሚያስችለውን የጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች” እንዲያከናውን አስጠንቅቆ ነበር።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው መግለጫ፤ “ፓርቲው የተጣለበትን የሕግ ግዴታ ለመወጣት ፈቃደኛ አልሆነም” ብሏል። በመሆኑም ህወሓት “ከግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ቀን ጀምሮ ከፖለቲካ ፓርቲነት የተሰረዘ መሆኑን” አስታውቋል።
“ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዝ የመጨረሻ ውሳኔ አይደለም”
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና በሥራ ኃላፊነታቸው ምክንያት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የምርጫ ሕግ ባለሙያ፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ እውቅናው ተዘረዘ ማለት “ሰው ሕይወቱ እንደሚያልፈው ሁሉ ሞተ ማለት ነው” ሲሉ ይገልጹታል።
በ2011 ዓ.ም. የወጣው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ እና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ” ፖለቲካ ፓርቲዎች በሦስት መንገዶች ሊሰረዙ እንደሚችሉ ደንግጓል።
አዋጁ ከሚዘረዝራቸው ሁኔታዎች መካከል ፖለቲካ ፓርቲው በራሱ ፈቃድ ከምዝገባ እንዲሰረዝ ሲጠይቅ እና ምርጫ ቦርድ ሲወስን የሚሉት ይገኙበታል። “የፖለቲካ ፓርቲው ከምዝገባ እንዲሰረዝ በዚህ አዋጅ መሠረት ፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሰጥ” የሚለው ደግሞ ሦስተኛው ሁኔታ ነው።
የአሁኑን ጨምሮ ለሁለት ጊዜያት ሕጋዊ ሰውነቱን ያጣው ህወሓት፤ ሁለቱንም ጊዜ ከምዝገባ የተሰረዘው በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ነው።
የምርጫ ሕግ ባለሙያው፤ “ህወሓት አሁን የተሰረዘበት ምክንያት በአዋጁ እና በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄድ ስላልቻለ ነው” ሲሉ ያብራራሉ። ይህ ድርጊት አዋጁን እና የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ የሚጥስ መሆኑንም ይጠቅሳሉ።
ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ፓርቲውን በመሰረዝ የወሰደው እርምጃ “የመጨረሻ ውሳኔ” እንዳልሆነም ያስረዳሉ።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሊሰረዙ የሚችሉባቸውን ምክንያቶች የሚዘረዝረው የአዋጁ ክፍል፤ ፓርቲው ውሳኔውን የመቃመው መብት እንዳለው ደንግጓል።
“ቦርዱ ያሳለፈውን ውሳኔ የተቃወመ” የፖለቲካ ፓርቲ ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ የማቅረብ መብት እንዳለው በሕጉ ላይ ሰፍሯል።
ይህ ይግባኝ መቅረብ ያለበት ፓርቲው ውሳኔው በደረሰው በ30 ቀናት ውስጥ እንደሆነም አዋጁ ያስረዳል።
ባለሙያው፤ “በዋናውም ሆነ በማሻሻያው አዋጅ፤ የምርጫ ቦርድ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ሁሌም ለከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ አስተዳደራዊ ውሳኔዎች ናቸው” ሲሉ ይህንን የሕግ ክፍል ያብራራሉ።
ይሁንና በ30 ቀናት ውስጥ አቤቱታው የማይቀርብ ከሆነ ፓርቲው ጉዳዩን “እንደተወው እንደሚቆጠር” እንዲሁም “በይርጋ” ምክንያት በፍርድ ቤት ተቀባይነት እንደማያገኝ ገልጸዋል።

ከፖለቲካ ፓርቲነት መሰረዝ ውጤቱ ምንድነው?
የምርጫ ሕግ ባለሙያው፤ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ከምዝገባ ሲሰረዝ “ሕጋዊ ሰውነቱ ህልውና የሌለው እንደሚሆን” ይናገራሉ።
“ሕጋዊ ሰውነቱን የሰጠው አካል ሕጋዊ ሰውነቱን ከወሰደበት እና ከሰረዘው፤ ለምሳሌ ከዚያ በኋላ ህወሓት የሚባል ፓርቲ በሕግ አይታወቅም፣ ከሕጋዊ ሰውነቱ ጋር አብረው ያሉ መብቶች፣ ንብረት ማፍራት፣ አመራሮቹ፣ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ በስሙ መጠቀም… በአጠቃላይ ይቆማል ማለት ነው” ይላሉ።
ባለሙያው የዘረዘሯቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሰረዝ ውጤቶች በአዋጁ ላይም የተንጸባረቁ ናቸው። በ2011 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ፓርቲው ከፈረሰበት ጊዜ ቀን ጀምሮ “ፓርቲው ወይም የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ አይችሉም” በማለት ደንግጓል።
የምርጫ ሕግ ባለሙያው ይህንን ሲያብራሩ፤ “ፓርቲው ስለፈረሰ የህወሓት አመራር የሚባል አይኖርም። በፓርቲው ስም ደብዳቤ ሊጽፉ፣ ማህተማቸውን ሊጠቀሙ አይችሉም። አሁን መፍረሱ ለሕዝብ በደብዳቤ ተገልጿል። በፓርቲው ስም ማንኛውንም ዓይነት ግንኙነት ማድረግ አይችሉም” ይላሉ።
ምርጫ ቦርድ የፓርቲውን መሰረዝ ባሳወቀበት መግለጫ ላይ፤ ውሳኔው “በህወሓት እና በአመራሮቹ ላይ እንዲፈጸም” እንደወሰነ መጥቀሱንም በማስረጃነት ያነሳሉ።
በአዋጁ ላይ የተጠቀሰው ሌላኛው የመሰረዝ ውጤት የፖለቲካ ፓርቲውን ንብረት የሚመለከት ነው። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ሲፈርስ ንብረቱ “ላለበት ዕዳ መሸፈኛ ” እንደሚውል ያስረዳል። ፓርቲው ያለበት እዳ ተከፍሎ የሚተርፍ ንብረት ካለ “ቀሪው ገንዘብ እና ንብረት በቦርዱ ትዕዛዝ ለሥነ ዜጋ እና መራጮች ትምህርት እንዲውል” እንደሚደረግም በአዋጁ ላይ ሰፍሯል።
የምርጫ ሕግ ባለሙያው ይህ እርምጃ ህወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ በ2013 ዓ.ም. በተሰረዘበት ወቅትም ተግባራዊ እንደሆነ ያስታውሳሉ።
ምርጫ ቦርድ፤ ህወሓት ጦርነቱን ተከትሎ የተላለፈበት ስረዛ ውሳኔ እንዲነሳለት ላቀረበው ጥያቄ ከሁለት ዓመት በፊት ግንቦት 2015 ዓ.ም. በሰጠው ምላሽ ላይም ይህ ጉዳይ ተመላክቷል።
ቦርዱ በወቅቱ ለፓርቲው በጻፈው ደብዳቤ፤ የፓርቲው ንብረት ለሥነ ዜጋ እና ለመራጮች ትምህርት እንዲውል መደረጉ “የስረዛ ውሳኔ ውጤት” መሆኑን አስታውቆ ነበር።
በመሆኑንም በፓርቲው አመራሮች እና በንብረት ላይ የተላለፉት ውሳኔዎች “እንደ አዲስ ሊጠየቁ የሚችሉ” እንዳልሆኑም ገልጿል።
የምርጫ ሕግ ባለሙያው ንብረትን ተመለከተውን የሕጉ ክፍል ለማስፈጸም “የዕዳ አጣሪ እንደሚሾም” ይናገራሉ። ይህ አካል “ባንክ ውስጥ ያለ ገንዘብ፣ የሚንቀሳቀስ፣ የማይንቀሳቀስ ንብረት እንዲታገድ እንደሚያድርግ” ያስረዳሉ።
ዕዳ ካለ የመክፈል ሥራ የሚከናወነው ይህ የማጣራት ተግባር ከተጠነቀቀ በኋላ እንደሆነም አክለዋል። ይሁንና ህወሓት ላይ ይህንን ተግባር የማስፈጸም ጉዳይ “ውስብስ” እንደሆነ ይገልጻሉ።
“የመጀመሪያው እውቅና ይመለስልኛ እያለ ሲጠይቅ ስለነበረ፤ በልዩ ሁኔታ ሲመዘገብም የተወሰኑ የፓርቲው አመራሮች ተቀብለውት ስለሄዱ፤ ገንዘብ በየትኛው እውቅናው እንደነበር [መረዳት] በጣም አስቸጋሪ ነው። ከዚያኛው እውቅና ወደዚህኛው የተላለፈበት ሁኔታ ምን ዓይነት እንደሆነ ብዙ አላውቅም” በማለት ይናገራሉ።

መፍትሔው የት ነው?
‘የቀድሞው ሕጋዊ እውቅና ይመለስልኝ’ በሚል አቋሙ የጸናው ህወሓት፤ ‘በልዩ ሁኔታ’ እውቅና ለማግኘት ጥያቄ ማቅረብ፤ “ከሌሎች የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለየ መልኩ እንዲመዘገብ የሚያደርገው” ተግባር መሆኑን ገልጿል።
እንደ አዲስ ለመመዝገብ መስማማት “የትግራይ ሕዝብ ጄኖሳዳዊ ጦርነት በሚክድ መልክ ግዴታ እንዲኖረን የሚያደርግ ነው” ሲልም ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ ሀሳቡን የተቃወመበትን ምክንያት አስረድቷል።
ህወሓት በመግለጫው የፓርቲውን “ነባር ሕጋዊ እውቅና የመመለስ ጉዳይ በዋነኛነት የፖለቲካ ውሳኔ እንጂ፤ የሚከለክል ሕግ አለመኖሩን” ጠቅሷል። ብሔራዊ ምርጫ ቦርድንም፤ “‘በሕግ ሽፋን’ መተማመንን የሚሸረሽር ፖለቲካዊ አቋሙን ቀጥሎበታል” ሲልም ወቅሷል።
“ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ሕግን ጥላ መከታ አድርጎ እየሄደበት ያለውን የፖለቲካ ጨዋታ ትቶ ቅንነት የተሞላበት ነባሩን ሕጋዊ የእውቅና ሰርቲፊኬት” እንዲሰጥ ጠይቋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የምርጫ ሕግ ባለሙያ፤ “የፖለቲካ ፍትጊያ ነው እንጂ፤ በሕጋዊ [አሠራር] ምርጫ ቦርድ የሚጠበቅበትን ጠብቆ እንደሠራ ነው የማምነው” ይላሉ።
“ምርጫ ቦርድ የሚሠራው ቴክኒካል ሥራ ነው። ቴክኒካል ሲባል፤ ሕግ አለ፣ ሕግ ከሌለ ሕግ ይወጣል በሕጉ መሠረት ይፈጽማል” በማለት ይከራከራሉ።
የህወሓት እውቅና ጉዳይን በተመለከተ “የሕግ ጉዳዩ ተሟጦ አልቋል” የሚሉት ባለሙያው፤ ከአሁን በኋላ በሕግ በኩል የሚገኝ “ብዙ መፍትሔ አለመኖሩን” ያነሳሉ። ጉዳዩ “ፖለቲካዊ ውይይት የሚያሻው” መሆኑንም ያክላሉ።
“በ30 ቀናት ውስጥ ምርጫ ቦርድ በሰጠው ውሳኔ ላይ ህወሓት አቤቱታ ካላቀረበ በሕግ ንግግር ከዚያ በኋላ ህወሓት አይኖርም። ነገር ግን ፖለቲካሊ ይኖራል፤ ምክንያቱም አደረጃጀት አለው፣ ሕዝብ ያውቀዋል፣ ሠራዊትም አለ” ይላሉ።
” ‘እውቅና የላችሁም፣ ከዚህ በኋላ በክልሉ ፖለቲካ ውስጥ ልትሳተፉ፣ ሕዝብ ልትሰበስቡ አትችሉም’ የሚል ነገር ሊመጣ ይችላል። የፌደራል መንግሥቱ ይህንን የምርጫ ቦርድ ውሳኔ ሊጠቀምበት ይፈልጋል” ሲሉም ግምታቸውን ያስቀምጣሉ።
በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል ንግግር የማይደረግ ከሆነ “ወደ ሌላ ግጭት ውስጥ ሊገባ ይችላል” በማለትም ስጋታቸውን ያስረዳሉ።
በልዩ ሁኔታ መመዝገብን የፈቀደው የአዋጅ ማሻሻያ “የፖለቲካ ውሳኔን ሕጋዊ ለማድረግ የወጣ” መሆኑን የሚከራከሩት ባለሙያው፤ ፖለቲካዊ ንግግር ተደርጎ ተመሳሳይ ሕግ ማውጣት እንደሚቻል ያነሳሉ።
“ምርጫ ቦርድ ሕግ አያወጣም። አዋጆቹን የሚያወጣለት ፓርላማው ነው። ፓርላማው፤ ህወሓትን ወደ ቀደመ ማንነቱ ሊመለስ የሚያስችል ሕግ ካወጣ አሁንም ምርጫ ቦርድ የሚከላከልበት ምክንያት አይኖርም። ምክያቱም ተጠሪነቱ ለፓርላማ ነው፤ ፓርላማው ያወጣውን ሕግ ያስፈጽማል” ሲሉ መፍትሔው የሚወድቀው በፌደራል መንግሥት እና በህወሓት መካከል በሚደረግ ፖለቲካዊ ንግግር ውስጥ መሆኑን አጽንኦት ይሰጣሉ።