የምርጫ 97ን ከታዘቡት መካከል አንዱ የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር በወቅቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዳይሬክተር ከነበሩት ከማል በድሪ ጋር በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ
የምስሉ መግለጫ,የምርጫ 97ን ከታዘቡት መካከል አንዱ የአሜሪካ የቀድሞው ፕሬዝደንት ጂሚ ካርተር በወቅቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዳይሬክተር ከነበሩት ከማል በድሪ ጋር በአዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ

ከ 5 ሰአት በፊት

በኢትዮጵያ ታሪክ ከተካሄዱ ምርጫዎች ሁሉ የተለየ የነበረው የ1997 ዓ.ም. ምርጫ ከተካሄደ 20 ዓመት ቢሆንም በተራው ሕዝብ እና በፖለቲከኞች ዘንድ ትዝታው አሁን ድረስ አልደበዘዘም።

የወታደራዊው መንግሥት ከተወገደ በኋላ ለአራተኛ ጊዜ የተካሄደው አገራዊ ምርጫ የታክሲ እና የጎዳና ላይ ፖለቲካዊ ውይይቶች የተሟሟቁበት፣ መስቀል አደባባይ ታላላቅ የሕዝብ ሰልፎችን ያስተናገደበት የውጭ እና የአገር ውስጥ ታዛቢዎች በመላ አገሪቱ ምርጫውን ለመታዘብ የተሯሯጡበት ነበር።

በወቅቱ የአገሪቱ የምርጫ ቦርድ በሰጠው መግለጫ 26 ሚሊዮን ሕዝብ በመራጭነት መመዝገቡን፣ 32 የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ሦስት ሚሊዮን 119 ሺህ 194 ዕጩ ማቅረባቸውንም ይፋ አድርጓል።

ትናንሽ ግን ብዙ ፓርቲዎች ባሉበት አገር ተጽእኖ ለመፍጠር “መተባበር ወይ መሰባባር” የሚል ጠንካራ ግፊት ስለገጠማቸው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት (ሕብረት) እና ቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ (ቅንጅት) የተባሉ ሁለት ጥምረቶች ኢህአዴግን ለመፎካከር በዋናነት ቀረቡ።

የአሁኑ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ ልደቱ አያሌው፣ ኃይሉ ሻውል እና ያዕቆብ ኃይለማሪያም በቅንጅት ለአንድነት እና ለዲሞክራሲ ስር ሲሰባሰቡ፤ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እና ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደግሞ በሕብረት ጥላ ስር ተሰባሰቡ።

እነዚህ ሁለት ትልልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎች ስብስብ የድጋፍ መሠረታቸውም የተለያየ ነበር።

በሕብረት ስር የተሰባሰቡት ፓርቲዎች ብሔር ተኮር የሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የነበሩ ሲሆን የድጋፍ መሠረታቸውም በተለይ በኦሮሚያ እና በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ነበረ።

ቅንጅት ደግሞ አራት አገር አቀፍ ፓርቲዎች በጋራ በመሆን የመሠረቱት እና አብዛኛው የድጋፍ መሠረቱ በዋናነት በከተሞች አካባቢ ነው።

የ1997 ዓ.ም. አራተኛው አገራዊው ምርጫ በአንድ ፓርቲ የበላይነት ተይዞ የነበረውን የአገሪቱን ሥልጣን የበለጠ ፉክክር የሚታይበት እና ወደ ብዝኃ ፓርቲ ዲሞክራሲ ሽግግር የሚደረግበት ይሆናል ብሎ አብዛኛው መራጭ ይጠብቅ ነበር።

በኢህአዴግ እና በተቃዋሚዎች ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ክልል ከተሞች በሚያዝያ ወር የመጨረሻ ቀናት የተደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ የድጋፍ ሰልፎች በድምጽ መስጫ ቀን ላይ የሚፈጥረውን ለማየት ሁሉም በጉጉት እንዲጠብቅ አድርገዋል።

በወቅቱ ኢህአዴግ፣ ቅንጅት እንዲሁም ሕብረት የሚያካሄዷቸው የምርጫ ክርክሮች በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት ሲተላለፉ ሺዎች የቴሌቪዥን መስኮታቸው ላይ ዓይናቸውን ተክለው፣ ጆሮዎቻቸውን ሬዲዮኖች ላይ ለጥፈው ያዳምጡ እንደነበር በወቅቱ በሕብረት ፓርቲ ስር ተወዳዳሪ የነበሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ያስታውሳሉ።

በተቃዋሚዎች እና በገዢው ፓርቲ መካከል የተካሄዱት የምርጫ ክርክሮች “እንደ ተከታታይ ድራማ በጉጉት እና በቀጠሮ ይጠበቁ ነበር” ይላሉ።

በሚያዝያ 29/1997 ዓ.ም. ኢህአዴግ በአዲስ አበባ ያደረገውን ሕዝባዊ የድጋፍ ሠልፍ ተከትሎ የኢህአዴግ ሊቀመንበር እና የወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የመስቀል አደባባዩን የድጋፍ ሰልፍ “ሕዝባዊ ማዕበል” ሲሉ ጠርተውታል።

በማግስቱ ሚያዝያ 30/1997 በአዲስ አበባ ቅንጅትን በመደገፍ አደባባይ የወጡት የከተማዋ ነዋሪ ወጣቶች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ ስለነበር በንጽጽር “ሱናሚ” የሚል ቅጽል ተሰጥቶት ነበር።

የምርጫ 97 በከተሞች፣ በወጣቶች እና በአርሶ አደሮች ዘንድ ከፍተኛ የለውጥ መንፈስ የታየበት እንደነበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኢህአዴግ “እንከን የለሽ” ምርጫ ለማድረግ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም ግንቦት 7 ድምጽ ከተሰጠ በኋላ ግን ነገሮች ቃል ከተገቡት ውጪ ሆነው እስሮች፣ግድያዎች እና ስደት ተከትሏል።

አሁን የኦፌኮ ሊቀመንበር የሆኑት እና በምርጫ 97 በሕብረት ጥላ ስር በመሆን የተወዳደሩት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የነበራቸውን ትውስታ እና ግምገማን ለቢቢሲ አካፍለዋል።

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና

ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና በኢትዮጵያ ውስጥ ከንጉሡ ጊዜ ጀምሮ ምርጫ ይካሄድ እንደነበር አስታውሰው “በኢትዮጵያ ታሪክ ከቅርጫ ያለፈ ምርጫ የሚመስል ምርጫ የተካሄደው በ97 ነው” ይላሉ።

ለፕሮፌሰር መረራ ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ለማድረግ ትችልባቸው ከነበሩ የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ የነበረው ምርጫ 97 መሆኑን ገልጸው፣ ያም ልክ እንደሌሎቹ ጊዜያቶች ሁሉ እንዳመለጣት በቁጭት ይናገራሉ።

በ1997 የተደረገው አራተኛው አገራዊ ምርጫ “በኢትዮጵያ ሕዝቦች ዘንድ የተለየ የመለወጥ ተስፋ፣ የዲሞክራሲ ተስፋ፣ የተሻለ ነገር የማግኘት ተስፋ የፈጠረ ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።

ላለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ ወደ ዲሞክራሲ ሽግግር ማድረግ ትችል ከነበረባችባቸው እና ካመለጧት የታሪክ እጥፋቶች መካከል አንዱ ምርጫ 97 ነው ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።

አጼ ኃይለ ሥላሴ ከሥልጣን ሲወርዱ የኢትዮጵያ ሕዝብን ከዳር እስከ ዳር ያንቀሳቀሰው አብዮት በወታደራዊው መንግሥት መጨናፉን በማስታወስ ይህ በእርሳቸው ዕድሜ ከተከሰቱት መካከል አንዱ መሆኑን ያነሳሉ።

ከዚያ በመቀጠል ደርግ ከሥልጣን ሲወርድ “ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ይመሠረታል፤ ከታሪክ ተምረን አዲሲቷ ኢትዮጵያ ትፈጠራለች ብለን ተስፋ አድርገን የነበረ ቢሆንም” ይህም በኢህአዲግ መሪዎች በክሸፉን ይገልጻሉ።

በሦስተኛ ደረጃ በኢትዮጵያ ታሪክ ባልታየው እና ያልተደገመው ምርጫ 97፣ ይዞ የመጣውን ተስፋ ሚሊዮኖች መሪዎቻችንን መምረጥ እንችላለን በሚል አደባባይ ወጥተው ድምጻቸውን ቢሰጡም ይህም “በሥልጣን ስግብብነት የተነሳ” መጨናገፉን ተናግረዋል።

አራተኛው ደግሞ በ2010 ዓ.ም. ኢህአዴግ ከሥልጣን ሲወርድ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር የማድረግ ዕድል አመለጠን ይላሉ።

የምርጫ 97 ለምን ተጨናገፈ? የሚጠበቀውን ውጤት ለምን ሳያመጣ ቀረ? ለሚለው ጥያቄ ፕሮፌሰር መረራ ሲመልሱ “የኢህአዴግ የሥልጣን ስስት የፈጠረው” መሆኑን ይጠቅሳሉ።

የምርጫ 97 እጅግ ፍትሃዊ እና የብዙኃን ተሳትፎ የታየበት ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና፣ በመጨናገፉ የተነሳ “አሁን ለገባንበት አገራዊ ቀውስ አስተዋጽኦ ማድረጉ ጭምር መታየት አለበት” ባይ ናቸው።

ኢህአዴግ በወቅቱ ተቃዋሚዎች ከተማ ውስጥ እንጂ ሰፊው የአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች ላይ ብዙ ግንኙነት የላቸውም ይል እንደነበር አስታውሰው “መለስ ከዚያ በኋላ ‘ካልኩሌትድ ሪስክ’ [ተሰላ የድፍረት እርምጃ] መውሰዱን የገለፀው ያለንን ሕዝባዊ ድጋፍ [በገጠሪቱ ኢትዮጵያ] ካየ በኋላ ነው” ይላሉ።

የምርጫ ቅስቀሳን ከተሜው ብቻ ሳይሆን የገጠሩ ማኅብረሰብም በጉጉት እና በንቃት ሲከታተል ነበር የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ “የሌሎቹን ዓለም የሚመስሉ ቅስቀሳዎች፣ ክርክሮች ነበሩ። የኢትዮጵያ ምድር ዲሞክራሲ የተላበሰች ትመስል ነበር” ይላሉ።

ፕሮፌሰር መረራ በገጠር ለምርጫ ቅስቀሳ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ያዩዋቸውን ነገሮች ሲያስታውሱ “አርሶ አደሮች ራሳቸው ሬዲዮ ይዘው ነበር ማሳቸውን የሚያርሱት።”

“ቅጥ ያጣ የፖለቲካ ሥልጣን ስስት” ምርጫ 97 ፈጥሮት የነበረው ተስፋን ሁሉ አጨናገፈው ሲሉ ይቆጫሉ።

ፕሮፌሰር መረራ በኢትዮጵያ ታሪክ የመላ አገሪቱ ሕዝቦች የነቃ ተሳትፎ የተደረገበት ምርጫ “ከምርጫ 97 በፊትም ሆነ በኋላ ተደርጎ አያውቅም” ብለዋል።

የኢህአዴግን እና የኢትዮጵያን ባንዲራ የያዘ ወጣት

በወቅቱ የምርጫ 97ን በበላይነት የመሩት “የህወሓት መሪዎች ናቸው” የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ዛሬ በትግራይ ሕዝብ ላይ በደረሰው እልቂት እና ሰቆቃ እነርሱም ከእኛ ያላነሰ ማዘንም መፀፀትም አለባቸው የሚል እምነት አለኝ” ሲሉ ይናገራሉ።

ፕሮፌሰር መረራ የምርጫ 97 መጨናገፍ “ዛሬ ለገባንበት አገራዊ ቀውስ ቀጥተኛ ሚና አለው፤ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም” ካሉ በኋላ “የፖለቲካ ምኅዳሩ እየሰፋ ቢሄድ እና የተሳካ ሽግግር ውስጥ ብንገባ ኖሮ አሁን የገባንበት አጠቃላይ ቀውስ ውስጥ የምንገባበት ምክንያት አይኖርም ነበር” ብለዋል።

ለዲሞክራሲ ሽግግር የነበረው ተስፋ መጨናገፉ አሁን አገሪቱ ለገባችበት ቀውስ አስተዋጽኦ አድርጓል የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ ያ በመሆኑ “እኔን በጣም ያሳዝነኛል፤ ምናልባትም ከተቃዋሚዎች በላይ የኢህአዴግ መሪዎችን የሚያሳዝን ይመስለኛል። ውጤቱ ውሎ አድሮ ሁሉም ውድ ዋጋ የከፈለበት ነው።

“በምርጫ 97 መጨናገፍ የከሰረው ሁሉም ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ ከማንም በላይ ኢህአዴግ፣ እኛ ከከፈልነው፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከከፈለው በላይ ዋጋ ከፍሎበታል።”

በወቅቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያደረጓቸው ክርክሮች እና ቅስቀሳዎች ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ከተደረጉት አገራዊ ምርጫዎች ጋር ሲወዳደር “በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ . . . ፍፁም በተለየ መንገድ በአፍሪካ ደረጃ ሳይሆን በሰለጠነው ዓለም የተደረጉትን የምርጫ ክርክሮችን ይመስል ነበር።”

የምርጫ ቅስቀሳዎች በቀጠሮ የሚደመጡ እና የሚታዩ ነበሩ ሲሉ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።

ከዛሬ 20 ዓመት በፊት በምርጫ 97 የተካሄዱት የምርጫ ክርክሮች የሕዝቡን ቀልብ አሁን ድረስ የሳቡ ነበሩ ይላሉ። “እኔን አሁን ድረስ ብዙ ሰው የሚያስታውሰኝ በምርጫ 97 ነው” ሲሉም ያክላሉ።

ብዙ ሰው ያስታውሳል ይቆጫል ‘ያ ዕድል የነበረው ተስፋ በመጨናገፉ የኢህአዴግ አባላት በተለይ መሪዎች መቆጨት ያለባቸው ይመስለኛል፤ ዕድሉ ተመልሶ ባይመጣም በቀላሉ እና በማይሆን መንገድ ያ ዕድል በመበላሸቱ ሁላችንም ሊቆጨን የሚገባን ጉዳይ ነው፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ የተለየ ተስፋ ነበር የተጨናገፈው።”

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ቢሆን “የአገር ፓርላማ ይመስል የነበረው በዚያ ምርጫ በተገኘ ድምጽ እንደራሴ ሆነው በገቡ የተቃዋሚ ፓርቲ ተወካዮች ተሳትፎ ነው” ይላሉ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይደረጉ የነበሩ ክርክሮች ብዙም “የኢህአዴግን ፖሊሲ መለወጥ የሚችሉ ባይሆኑም” በሚደረግባቸው ክርክር የተነሳ “የአገር ፓርላማ ይመስል ነበር” በማለት በተወሰነ ደረጃ ያመጣውን ለውጥ ይጠቅሳሉ።

የምርጫ 97 “ተጨናግፎም ቢሆን፣ ተሰርቆም ቢሆን” አብዛኛው የቅንጅት ፓርቲ ተመራጭ ወደ ምክር ቤት አልገባም ብሎ እስር ቤት ቢገባም የተወሰኑ አባላቱ እና የሕብረት ተወካዮች ገብተው “ፓርላማው የኢትዮጵያ ፓርላማ” እንዲመስል አድርገውታል ይላሉ።

በምክር ቤቱ በሥራ አጥነት፣ በአገር ምጣኔ ኃብት፣ በደኅንነት ዙሪያ የሚደረጉ ክርክሮች ያኔ ብቻ ሳይሆን አሁን ድረስ መለስ ብሎ ለሚሰማቸው የምርጫ 97 የፈጠረውን የፖለቲካ ተሳትፎ መነቃቃት የሚያሳዩ እንደነበሩ በትዝታ ያስታውሳሉ።

በምርጫ 97 ወቅት ድምጻቸውን ለመስጠት በድምጽ መስጫ ኮሮጆው አጠገቡ  የተሰበሰቡ እናቶች

በወቅቱ የነበሩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችንም መለስ ብለው ሲያይዋቸው “ሞቅታ የሚመስሉ አንደንድ ነገሮች ነበሩ” ይላሉ።

“የተቃዋሚውንም አጠቃላይ አቅም የመገመት ልዩነት ነበር” በተለይም ደግሞ ዳያስፖራው አገር ውስጥ ያለው የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት መሸከም ከሚችለው በላይ ይጠይቅ እና ይጠብቅ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ከዚህ ባሻገር የገዢው ኢህአዴግ ፓርቲ በተለያየ መንገድ ባስቀመጣቸው እንቅፋቶች የተነሳ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “በሙሉ ልብ ወደ ምርጫ አልገቡም ነበር” ይላሉ ፕሮፌሰር መረራ።

በወቅቱ የሕብረት አባላት የነበሩ እና መቀመጫቸውን በባሕር ማዶ አድርገው የነበሩ የረዥም ጊዜ የፖለቲካ ልምድ የነበራቸው እነ መኢሶን፣ ኢህአፓ እና መድኅን አገር ውስጥ ገብተው በፖለቲካው አለመሳተፋቸውንም ያነሳሉ።

በምርጫው ላይ የተሳተፍነው በአገር ውስጥ የምንንቀሳቀስ ብቻ ነበርን ያሉት ፕሮፌሰር መረራ፣ በዲያስፖራው ግፊትም ሕብረት እና ቅንጅት እንዲለያዩ ሆነዋል ሲሉ በተቃዋሚው ላይ የነበረው ጫና እና መለያየት የምርጫው አንድ የታሪክ አካል እንደነበር ይጠቅሳሉ።

መጀመሪያ ላይ ሁሉም በሕብረት ጥላ ስር መሰባሰቡን ያስታወሱት ፕሮፌሰር መረራ “ሁላችንም በሕብረት ስር ሆነን ኢህአዴግን መፎካካር ችለን ቢሆን ኖሮ፣ ምናልባትም ሁላችን አብረን እስር ቤት እንገባለን ወይ አብረን ሁላችን ፓርላማ እንገባ ነበር።”

“በተወሰነ ደረጃ የተሻለ ዕድልም እንፈጥር ነበር’ ሲሉ የነበረውን ሁኔታ መለስ ብለው ያስታውሳሉ።

በምርጫ 97 የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደነበረው የሚጠቅሱት ፕሮፌሰሩ፣ በነበረው ግፊት የተነሳ የቅንጅት ፓርቲ መሪዎች ከሕብረት ወጥተው ቅንጅትን ለመመሥረት በቅተዋል ሲሉ ያላቸውን እምነት ይናገራሉ።

“ቅንጅት አካባቢ የተሻለ ሪሶርስ [ሀብት] ነበር” የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ ከዚያ በኋላ ለመጣው መከፋፈል እና እስር የራሱ አስተዋጽኦ አለው ብለው ያምናሉ።

ምርጫ 97 ትቶት ያለፈው ትልቅ ነገር “አምባገነን መሪዎች ባያጨናግፉት፣ ባያበላሹት የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለው የፖለቲካ ንቃት መሪዎቹን ለመምረጥ እንደሚችል” መሆኑን ፕሮፌሰር መረራ በቁጭት 97ን ያስታውሳሉ።

ሕዝቡ በሚሊዮኖች ወጥቶ ለተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ድጋፍ ያሳየበት፣ ድምጽ የሰጠበትም መሆኑ ሌላው በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተገኘ ትልቅ ትምህርት ነበር ያላሉ።

ለፖለቲካ ኃይሎች “ዕድሉ ተበላሸ እንጂ፣ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ ይቻላል፤ የሰለጠነ የምርጫ ክርክር ማድረግ ይቻላል” የሚለው ሌላው ከ20 ዓመት በፊት የተገኘ ትምህርት ነገር ግን መድገም ያልተቻለ መሆኑን ፕሮፌሰሩ ጠቅሰዋል።