የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር

21 ግንቦት 2025, 15:02 EAT

245 ሚሊዮን ዶላር የመዘበሩት የቀድሞው የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር በሙስና ወንጀል 10 ዓመት ከባድ የግዳጅ የጉልበት ስራ ተፈረደባቸው።

አውግስቲን ማታታ ፖንዮ 245 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የህዝብ ገንዘብ በመመዝበር የአገሪቱ ህገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ሆነው ስላገኛቸው ነው ይህ ብይን የተላለፈው።

ከሳቸው በተጨማሪ የዲሞክራቲክ ኮንጎ ማዕከላዊ ባንክ ገዢ የነበሩት ዲኦግራቲያስ ሙቶምቦም በዚህ ምዝበራ በመሳተፍ ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተዋል።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጠበቃ ውሳኔው ኢፍትሃዊ እንዲሁም ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው ሲሉ ወቅሰው ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ተመዝብሯል ከተባለው ገንዘብ መካከል የተወሰነው የተወሰደው የአገሪቱን ስር የሰደደ የምግብ እጥረት ለመቅረፍ ከታቀደው ትልቅ የግብርና ልማት ነው።

ማታታ ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2016 የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ወቅት የአመራር እና አስተዳደር ለልማት (ኤልጂዲ) የተሰኘ ፓርቲ እየመሩ ይገኛሉ።

ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ስልጣን ከመምጣታቸው በፊት የአገሪቱ የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፤ በወቅቱም የአገሪቱን ምጣኔ ኃብት በማረጋጋት ረገድ ለተጫወቱት ሚና ከአለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) አድናቆትን አግኝተው ነበር።

የማዕከላዊ ባንክ ገዥ የነበሩት ዲዮግራቲያስ ሙቶምቦ በተመሳሳይ የክስ መዝገብ ለአምስት ዓመታት የግዳጅ የጉልበት ስራ ቢፈረድባቸውም በውሳኔው ላይ በይፋ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለወንጀል ቅጣት የግዳጅ የጉልበት ስራ ፍርድ ህጋዊ መሆኑን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

ሁለቱም ግለሰቦች የግዳጅ የጉልበት ስራ ዘመናቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ለአምስት ዓመታት ያህል ከህዝብ አገልግሎት መታገዳቸውን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

ከሁለት ዓመት በፊት የአሁኑን የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ትሺሴኪዲን ተቃርነው የምርጫ ቅስቀሳ ያደረጉት ማታታ ክሱን ውድቅ አድርገዋል።

የአገሪቱ የፋይናንስ ኢንስፔክተር ጄኔራል ከቡካንጋ ሎንኦ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ ስርቆት መፈጸሙን ሪፖርት ያደረገው በአውሮፓውያኑ 2020 ሲሆን ፍርዱም ከአራት ዓመታት በላይ ቆይቷል።

ፓርኩ ከአፍሪካ ትልቁ የግብርና ኢንቨስትመንቶች አንዱ መሆኑን ሮይተርስ የዘገበ ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ ለ22 ሺህ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራል ብሎ ያምን ነበር።

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለአስከፊ የምግብ እጥረት ለተጋለጡ በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች እፎይታን ለመስጠት ያለመ ነበር።