May 21, 2025

በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የሚገኙ ዳኞች በትላንትናው ዕለት የጀመሩትን የስራ ማቆም ዛሬም በመቀጠላቸው በከተማይቱ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ተዘግተው ዋሉ። ዳኞቹ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረቧቸው ጥያቄዎች እስኪፈቱ ድረስ የስራ ማቆማቸውን እንደሚቀጥሉ የትግራይ ዳኞች ማህበር ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጿል።
በመቐለ ከተማ የሚገኙ ዳኞች ስራቸውን ለማቆማቸው በዋነኛነት የጠቀሱት ምክንያት “የደህንነት ችግር አለብን” የሚል ነው። የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በትላንትናው ዕለት ባወጣው መግለጫም፤ በመቐለ ሰባት ክፍለ ከተሞች ባሉ ፍርድ ቤቶች እና በከተማይቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚሰሩ ዳኞች “በደህንነት ስጋት” ምክንያት ስራ እንዳቆሙ ማሳወቃቸውን አረጋግጧል።
የትግራይ ዳኞች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ዳዊት ሃይለስላሴ፤ ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረቧቸው አምስት ጥያቄዎች ከዳኞች ደህንነት ጋር የተያያዙ መሆናቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የዳኞቹ የመጀመሪያ ጥያቄ በችሎት የሚመደቡ የጸጥታ አስከባሪዎችን የሚመለከት ነው።

“በችሎት ጊዜ ሁለት ፖሊሶች ብቻ ናቸው ፍርድ ቤቱን የሚጠብቁት” የሚሉት አቶ ዳዊት፤ በአሁኑ ጊዜ በመቐለ ከተማ ባለው የጸጥታ ችግር “ይህ በቂ እንዳልሆነ” ያስረዳሉ። በዚህም ምክንያት ቁጥራቸው ከፍ ያለ “የታጠቁ የጸጥታ ኃይሎች” ፍርድ ቤቶችን እንዲጠብቁ እንዲደረግ ማህበሩ ጥያቄን ማቅረቡን ፕሬዝዳንቱ አብራርተዋል።
የከተማይቱ ዳኞች በሁለተኛነት ያነሱት ጥያቄ፤ በነጻነት የዳኝነት ስራቸውን ለማከናወን እንዲችሉ “ራሳቸውን መጠበቅ የሚችሉበት ሁኔታ ይመቻች” የሚል እንደሆነ አቶ ዳዊት አመልክተዋል። ይህ ጥያቄ የቀረበው፤ የተከሳሽ ቤተሰቦች ዳኞችን በመንገድ ላይ ሲያገኟቸው “እስከ መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ጭምር እየተከታተሉ ስለሚያስፈራሩ” እንደሆነ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ገልጸዋል።
ዳኞች በህዝብ ትራንስፖርት በሚመላለሱበት ጊዜ “ማስፈራራት እና ድብደባ እየደረሰባቸው” መሆኑን በተጨማሪነት የሚያነሱት አቶ ዳዊት፤ ይህን ችግር ለመፍታት “ለዳኞች ትራንስፖርት እንዲዘጋጅ” ማህበሩ መጠየቁንም አክለዋል። አራተኛው የማህበሩ ጥያቄ እንደ ትራንስፖርቱ ሁሉ ለዳኞች የመኖሪያ ቤት አቅርቦት እንዲመቻች የሚጠይቅ ነው።

ዳኞች በስራቸው ጸባይ ምክንያት “እስከ ሞት ቅጣት” የሚደርስ ውሳኔ የሚያስተላልፉ መሆኑን ያስታወሱት የማህበሩ ፕሬዝዳንት፤ በችሎት የሚሰጧቸውን ውሳኔዎች ተከትሎ ከሚኖሩባቸው ቤቶች እንዲለቅቁ የሚያስገድዷቸው አከራዮች እንዳሉ ጠቁመዋል።
ማህበሩ በአምስተኛነት ለክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ያቀረበው ጥያቄ የመንግስት ከፍተኛ ኃላፊዎችን የሚመለከት ነው። ዳኞች ጉዳዮችን በፍርድ ቤት በሚመለከቱበት ወቅት “ችሎት የደፈሩ” “በመንግስት ከፍተኛ ስልጣን የያዙ” ኃላፊዎች እንዳሉ የገለጹት አቶ ዳዊት፤ እነዚህ ግለሰቦች “በህግ እንዲጠየቁ” በማህበሩ አማካኝነት ጥያቄ መቅረቡን አክለዋል።
ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የቀረቡ እና ለዳኞች ስራ ማቆም ምክንያት የሆኑ “እነዚህ ጥያቄዎች ሲፈቱ ነው ወደ ስራ የምንመለሰው” ሲሉ የማህበሩ ፕሬዝዳንት ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። ሆኖም የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ትላንት ማክሰኞ ግንቦት 12፤ 2017 ባወጣው መግለጫ፤ ለዳኞች ስራ ማቆም ምክንያት ነው ሲል የጠቀሰው፤ ባለፈው ሳምንት በመቐለ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተፈጠረ ያለውን “ግርግር” ነው።

ፍርድ ቤቱ ባለፈው ሳምንት አርብ የነበረው የችሎት ሂደት የተቋረጠው፤ በነሐሴ 2015 ዓ.ም ግድያ የተፈጸመባትን የዘውዱ ሃፍቱን ጉዳይ እየተመለከተ በነበረበት ወቅት እንደሆነ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መግለጫ አስታውሷል። ይህን ችሎት በስፍራው ሆነው የተከታተሉ አንድ ታዳሚ፤ ጉዳዩ በሚታይበት ወቅት ተከሳሾች እና የተከሳሽ ቤተሰቦች ዳኞቹ ላይ “አንድ ሳምንት ብቻ ነው የቀራችሁ” እያሉ ሲዝቱ እና በጩኸት ሂደቱን ሲያውኩ እንደነበር እማኝነታቸውን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ሰጥተዋል።
እንዲህ አይነት የፍርድ ሂደትን የሚያውክ አካሄድ “የመንጋ ተግባር ነው” ያለው የትላንቱ የጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ፤ በችሎት ውስጥ የሚፈጠር ረብሻ “በማንኛውም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም” ሲል ኮንኗል። ድርጊቱ በትግራይ የፍትህ እና የዳኝነት ስርዓት ላይ የተፈጸመ “ግልጽ ጥቃት ነው” ሲልም አጽንኦት ሰጥቷል።
“ይህ አካሄድ ህግን እና ስርዓትን የሚያቀል፤ ጉልበተኛ እንደፈለገ እንዲሆን የሚያደርግ አደገኛ ተግባር ነው” ያለው ጊዜያዊ አስተዳደሩ፤ በዕለቱ የተፈጠረውን ክስተት በተመለከተ የማጣራት ስራ እንደሚከናወን እና በችግር ፈጣሪዎች ላይም ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስታውቋል። የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር፤ ዳኞች እና የህግ ባለሙያዎች “ዋስትናቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ” የሚያስችሉ ስራዎችን እንደሚያከናውንም ገልጿል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ቢልም፤ የ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘጋቢ በትላንትናው እና በዛሬው ዕለት ተዘዋውሮ የተመለከታቸው በመቐለ ከተማ የሚገኙ ፍርድ ቤቶች ዝግ ሆነው ውለዋል። በፍርድ ቤቶቹ መግቢያዎች ላይ “በዳኞች ላይ ባጋጠመ የደህንነት ስጋት ምክንያት የዳኝነት አገልግሎት አቁመናል” የሚል ማስታወቂያ ተለጥፎ ተመልክቷል። ፍርድ ቤቶቹ ስራ በማቆማቸው ባለጉዳዮችም ሆነ ሌሎች ሰዎች “ወደ ውስጥ መግባት እንደማይፈቀድላቸው” የጥበቃ ሰራተኞች ሲናገሩም አድምጧል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)