
ከ 3 ሰአት በፊት
አሜሪካ፤ የኤር ፎርስ ዋን አካል እንዲሆን ከኳታር በስጦታ የተበረከተላትን እና በተወሰኑ የፕሬዝዳንት ትራምፕ ትላልቅ ደጋፊዎች ጭምር ትችትን ያስከተለውን አውሮፕላን ተቀበለች።
የፔንታጎን ዋና ቃል አቀባይ ሻን ፓርኔል ረቡዕ ዕለት ባወጡት መግለጫ፤ “የመከላከያ ሚኒስቴር በሁሉም የፌደራል ህጎች እና ደንቦች መሰረት ቦይንግ 474 ን ከኳታር ተቀብሏል” ብለዋል።
አውሮፕላኑ፤ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ይፋዊ አየር መጓጓዣ የሆነው ኤር ፎርስ ዋና አካል ሆኖ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ማሻሻያ ይደረግበታል።
ዋይት ሃውስ ስጦታ ህጋዊ ነው በሚለው አቋሙ ቢጸናም፤ ከሳምንት በፊት አውሮፕላኑ መሰጠቱ በተገለጸበት ወቅት ትልቅ ውዝግብ አስነስቶ ነበር።
ከኳታር ንጉሳዊ ቤተሰብ በስጦታ የተበረከተው አውሮፕላን ዋጋ 400 ሚሊዮን ዶላር ይሆናል ተብሎ ይገመታል። ዋይት ሃውስ አዲሱ አውሮፕላን በትራምፕ የስልጣን ዘመን መጨረሻ ወደ ፕሬዝዳንታዊ ቤተ መዘክር ይዘዋወራል ብሏል።
ፕሬዝዳንቱን ለማጓጓዝ የግዴታ መካተት ያለባቸውን ተጨማሪ የደንህነት ስርኣቶች ለማሟላት እና ለማሳደግ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል ተብሏል።
ከእነዚህ የደህንነት ስርዓት ማሻሻያዎች መካከል በኒውክሌር ፍንዳታ የሚመጣን ኤሌክትሮ ማግኔቲክ ኃይል ግፊት እንዲቋቋም ማድረግ እና በረራ ላይ እያለ ነዳጅ መሙላት መቻል ይገኙበታል።
‘በሴንተር ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ሲንተርናሽናል ስተዲስ’ የመከላከያ እና ደህንነት ክፍል ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት ማርክ ካንሲያኒ እነዚህን ማሻሻያዎች ማከናወኛ ወጪው በቀላሉ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ተናግረዋል።
ትራምፕ ከሳምንት በፊት የአውሮፕላኑን መምጣት በደገፉበት ንግግራቸው፤ “እየሰጡን ያለው ስጦታ ነው” ብለው ነበር። በስጦታ የተበረከተው አውሮፕላን ውድቅ ማድረግ “ሞኘነት” መሆኑንም ተናግረዋል።
የአሜሪካ ህገ መንግሥት፤ የመንግስት ኃላፊዎች ያለ ኮንግረስ ፈቃድ ከውጭ መንግስታት ስጦታ እንዳይቀበሉ የሚከለክል ‘የኢሞሊውመንት አንቀጽ’ ተብሎ የሚታወቅ ድንጋጌ አለው። የአሁኑ አውሮፕላን የኮንግረሱን ፈቃድ አላገኘም።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስጦታው መከላከያ ሚኒስቴር እንጂ ለራሳቸው ቀጥታ የተበረከተ አለመሆኑን በመጥቀስ የአውሮፕላኑ መምጣት ህጋዊ ስለመሆኑ ይከራከራሉ። ከስልጣን ከለቀቁ በኋላ እንደማይጠቀሙትም ይገልጻሉ።
አሁን በስራ ላይ ባሉት የኤር ፎስር ዋን ዝርዝር እ.አ.አ ከ1990 ጀምሮ በስራ ላይ የነበሩት ሁለት 747-200 አውሮፕላኖች እና በርካታ አነስተኛ 757 አውሮፕላኖችን ያካትታል።
ትራምፕ፤ በቀጥታ ለዋይት ሃውስ ሁለት 747-8 በራሪዎችን እንዲያቀርብ ቅጥር በተፈጸመለት አውሮፕላን አምራቹ ቦይንግ ደስተኛ እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ቡድን አባላት በፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን ጊዜ ለመረከብ ተደራድረው የነበረ ቢሆንም በተደጋጋሚ መዘግየት አጋጥሟል። ቦይንግም አውሮፕላኖቹ ለተጨማሪ ሁለት ወይም ሶስት ዓመታት ለአገልግሎት እንደማይደርሱ አስታውቋል።
ትራምፕ ሁለተኛ ስልጣን ዘመናቸው በተጀመረ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ ባለቤትነቱ የእርሳቸው በሆነው ማር-አ-ላጎ ሪዞርት አቅራቢያ በፓልም ቢች የሚገኝን የኳታር አውሮፕላን በድብቅ ጎብኝተው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ፤ አውሮፕላኑ በአጋሮች መካከል የተደረገ ቀላል ልውውጥ እንደሆነ በመግለጽ ጉዳዩ በምላሹ የሚሰጥ ምንም ነገርን እንዳላካተተ ይከራከራሉ።
“የመከላከያ ሚኒስቴር እጅግ ይፋዊ እና ነጻ በሆነ ልውውጥ ያለ ምንም ክፍያ 40 ዓመት የሞላውን ኤር ፎርስ ዋን በጊዜያዊነት የሚተካ 747 አውሮፕላን በስጦታ አግኝቷል” ሲሉ በትሩዝ ማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ጽፈዋል።
የኳታር ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሞሃመድ ቢን አብዱልራህማን ቢን ጃሲም አል ታህኒ የአውሮፕላኑ መላክ “የመንግሥት ለመንግስት ዝውውር” መሆኑን ተናግረዋል።
“በኳታርም ሆነ በአሜሪካ በኩል [ጉዳዩን] ከግላዊ ግንኙነት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም። ጉዳዩ በሁለት መከላከያ ሚኒስቴሮች መካከል ነው” ብለዋል።
እነዚህ ገለጻዎች ግን ኮንግረስ ውስጥ ከሚገኙ የትራምፕ አጋሮች እና ቀኝ ዘመም መገናኛ ብዙሃን ጭምር ስምምነቱን በተመለከተ እየተነሱ ያሉትን ትችቶት ለማብረድ እምብዛም አልተሳካላቸውም።
የኬንታኪ ግዛት የሪፐብሊካን ሴናተር ራንድ ፖል፤ “አግባብ የሌለው ሆነም አልሆነ ነገርየው እየፈጠረ ያለውን የህገወጥነት ምስል የሚያካክስ አይደለም” ሲሉ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
“[የኳታርን] የሰብአዊ መብት ታሪክ መመዘን አቅማችን በዚህ ትልቅ ስጦታ ምክንያት ይጋረድ እንደሆን አስባለሁ” ሲሉም ተደምጠዋል።
ሌላኛው የቴክሳስ ሪፐብሊካን ቴድ ክሩዝ በኩላቸው ስጦታውን መቀበል “ግዙፍ የስለላ እና የክትትል ችግር” እንደሚጋርጥ ገልጸዋል።