አንጎል

ከ 4 ሰአት በፊት

ኮሊን የተባለው ንጥረ ነገር ለሰውነት ጠቃሚ ከሆኑ ንጥረ ነገሮች መካከል በዋናነት ይጠቀሳል።

ኮሊን (Choline) ቫይታሚንም ሚኒራልም አይደለም። ነገር ግን የሰው ልጆች አእምሮ በአግባቡ እንዲሠራ ይረዳል።

የማሰላሰል ብቃትን በማሻሻል ከአእምሮ ዕድገት ጋር የተያያዙ ህመሞችን በመከላከልም እንደሚረዳ ጥናቶች ያሳያሉ።

ከዚህም አንጻር እንደ ኤዲኤችዲ (ADHD) እና ዲስሌክስያ (dyslexia) የመሳሰሉ የአእምሮ ዕድገት ውስንነቶችን እንደሚከላከልም ይገለጻል።

በብሩክሊን ኮሌጅ የሥነ ምግብ ተመራማሪ ዢያን ጂያንግ እንደሚለው፣ በዚህም የተነሳ ሳይንቲስቶች ኮሊንን ‘ተዓምረኛው ንጥረ ነገር’ ይሉታል። በሰውነታችን ውስጥ ያለ ሁሉም ሕዋስ ኮሊን በውስጡ ይገኛል።

ለጤናችን ጠቃሚ የሆነውን ኮሊን ሰውነታችን በበቂ ሁኔታ አያመርትም። ስለዚህ ከምግብ በምናገኘው ንጥረ ነገር እናካክሳለን።

ከቫይታሚን ቢ ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው ንጥረ ነገር ተደርጎ ቢወሰድም የሚቀርበው ግን ለኦሜጋ 3 ፋቲ አሲድ መሆኑን በኒውትሪሽናል ኢንሳይት የምታማክረው የሳይንስ ፀሐፊ ኤማ ደርቢሻይር ትናገራለች።

ይህ ንጥረ ነገር በበሬ እና በዶሮ ሥጋ፣ ዓሣ፣ እንቁላል እና ብሮክሊ ውስጥ ይገኛል። በብዛት የሚገኘው ሥጋ ነክ በሆኑ ምግቦች ውስጥ ነው።

እንቁላል
የምስሉ መግለጫ,ንጥረ ነገሩ ከሚገኝባቸው ምግቦች መካከል አንዱ እንቁላል

በተጨማሪም ኮሊን “ጉበት ውስጥ ስብ እንዲዘዋወር ይረዳል። የኮሊን እጥረት ከተከሰተ ጉበት በስብ ይሞላል” ይላል ዢያን።

ኮሊን የተባለው ንጥረ ነገር ሰውነታችን ውስጥ ካነሰ ሕዋሳት እንዲባዙ የሚያደርገው ዘረ መል የሚመረትበት አቅም ይቀንሳል።

በማህጸን ውስጥ ያለ ጽንስ የኮሊን እጥረት ከገጠመው በጭንቅላቱ ውስጥ የሚገኙ ሕዋሳት በተገቢው መንገድ ሥራቸውን አያከናውኑም።

ኮሊን “የጭንቅላት ንጥረ ነገር” ተብሎ የሚጠራው ጥቅሙ በዋናነት ከአንጎል ጋር የተሳሰረ ስለሆነ ነው።

አእምሮ የሚያስተላልፈውን መልዕክት ወደ ሰውነታችን ለማድረስ የሚረዳው ኬሚካል (acetylcholine) እንዲመረት የሚያደርገው ኮሊን ነው።

ዕድሜያቸው ከ36 እስከ 83 የሆኑ 1,400 ሰዎች በተሳተፉበት ጥናት እንደታየው ከፍተኛ የኮሊን ንጥረ ነገር ወደ ሰውነት ሲገባ የተሻለ የማስታወስ ብቃት ይፈጠራል።

በዕድሜ እኩሌታ አካባቢ የኮሊን ንጥረ መጠን በሰውነት ውስጥ እንዲጨምር በማድረግ የአንጎልን ጤና ይጠብቃል።

የመማር እና ማስታወስ ብቃትን ያሻሽላሉ በሚል ከሚሸጡ ንጥረ ነገሮች መካከል ኮሊን ይጠቀሳል።

የለውዝ ቅቤ
የምስሉ መግለጫ,ኮሊን ከለውዝ ቅቤ ሊገኝ ይችላል

የኮሊን እጥረት ከአልዛይመርስ እና ፓርኪንሰንስ እክሎች ጋር እንደሚያያዝ ይገለጻል። የኮሊን መጠን ከፍ ሲል የጭንቀት መጠን እና ድባቴ እንደሚቀንስም ጥናት ያሳያል።

በአይጦች ላይ የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው ኮሊን በሰውነት ውስጥ ሲኖር የልብ ድካም ችግርን የሚያስከትለው አሚኖ አሲድ ሆሞሲስቲን እንዲቀንስ ይረዳል።

በኖርዌይ ማሪን ሪሰርች ባለሙያ የሆነው ኦይን ጃኒክ እንደሚለው ንጥረ ነገሩ ለአጥንት ጥንካሬ ይረዳል።

በሕጻናት ዕድገት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ዓመታት ከፍተኛ ሚና አላቸው። እናት በእርግዝና ወቅት እና ጡት ስታጠባ የምትመገው ምግብ በዚህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል።

ለልጆች ዕድገት ከፍተኛ ሚና ያለው ንጥረ ነገር ሲሆን፣ ጨቅላዎች ሲወለዱ የንጥረ ነገሩን ሦስት እጥፍ መጠን ይዘው ነው። ምን ያህል ለዕድገታቸው ጠቃሚ እንደሆነ ያሳያል።

ሕጻናት በማህጸን ውስጥ ሳሉ እና ከተወለዱ በኋላ ባሉት ዓመታትም ንጥረ ነገሩ ከፍተኛ ጥቅም አለው።

ከ13ኛ እስከ 28ኛ የእርግዝና ሳምንት ውስጥ ሳሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ኮሊን ያገኙ እናቶች የወለዷቸው ልጆች የአጭር ጊዜ እና የረዥም ጊዜ የማስታወስ ችሎታቸው ከፍተኛ ሆኖ ተገኝቷል።

የኮሊን እጥረት ከአእምሮ ዕድገት ውስንነት ጋር ከተያያዙ እክሎች ጋርም ይተሳሰራል።

“ብዙ ኤዲኤችዲ እና ዲስሌክሲያ ያለባቸው ልጆች በትምህርት ቤቶች ይገጥሙናል። አንዳንዱ በዘር የተወረሰ ነው። ጨቅላ ሕጻናት በማህጸን ውስጥ ሳሉ ማግኘት ያለባቸውን ንጥረ ነገር ስላላገኙም ሊሆን ይችላል” ስትል የሳይንስ ፀሐፊዋ ኤማ ታስረዳለች።

የሥነ ምግብ ተመራማሪ ዢያን እንደሚለው የተሻለ ኮሊን በሰውነታቸው ውስጥ ካለ እናቶች የሚወለዱ ልጆች የኮሊን መጠናቸው ከፍ ያለ ነው።

ቦሎቄ
የምስሉ መግለጫ,ቦሎቆም ንጥረ ነገሩ ከሚገኝባቸው የምግብ እህሎች አንዱ ነው

በቂ ኮሊን እያገኘን ነው?

የአውሮፓ ምግብ ተቆጣጣሪ ተቋም እንደሚለው፣ በቀን ውስጥ አዋቂ ወንዶች 400 ሚሊ ግራም ኮሊን ማግኘት አለባቸው።

አዋቂ ሴቶች 425 ሚሊ ግራም ኮሊን፣ ነፍሰ ጡር እናቶች 450 ሚሊ ግራምና ጡት የሚያጠቡ እናቶች 550 ሚሊ ግራም ኮሊን ማግኘት ይገባቸዋል።

አንድ እንቁላል 150 ሚሊ ግራም ኮሊን ሲኖረው የዶሮ ሥጋ 72 ሚሊ ግራም ኮሊን እና ለውዝ 24 ሚሊ ግራም ኮሊን አላቸው።

በ38 እንስሳት እና 16 ሰዎች ላይ የተሠራው እና በአውሮፓውያኑ 2020 የወጣው ጥናት እንደሚጠቁመው፣ ኮሊን ለአእምሮ እድገት ሚና አለው።

ሰዎች በቀን እስከ 930 ሚሊ ግራም ኮሊን ንጥረ ነገር ሊያገኙ እንደሚችሉም ያሳያል።

የኦስትሮጂን መጠናቸው አነስተኛ የሆነና ጉበታቸው በስብ የተሞላ ሰዎች የበለጠ ኮሊን ማግኘት አለባቸው።

የተለያየ ዘረ መል ያላቸው ሰዎች የተለያየ የኮሊን መጠን ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ባለሙያዎች ይናገራሉ።

ከምግብ ኮሊን ስናገኝ ንጥረ ነገሩ ወደ ደም ሥራችን ለመግባት ጊዜ አይወስድበትም። በዋናነት እንቁላል መመገብ የንጥረ ነገሩን መጠን ይጨምራል።

አትክልት ብቻ የሚመገቡ ሰዎች ከቶፉ 28 ሚሊ ግራም ኮሊን፣ ከለውዝ 66 ሚሊ ግራም ኮሊን እና ከቦሎቄ 120 ሚሊግራም ኮሊን ያገኛሉ።

ኮሊን ንጥረ ነገር እንዴት ለአእምሮ ከፍተኛ ጥቅም ያለው እንደሆነ በቀጥታ ግንዛቤ ለማግኘት ተጨማሪ ጥናቶች መሠራት እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

የበለጠ ስለ ኮሊን ንጥረ ነገሩ ጠቀሜታ ያለው መረዳት ከጨመረ ሰዎች ንጥረ ነገሩን ያያዙ ምግቦችን በብዛት በመመገብ ለጤናቸው አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ እንደሚረዳም ይናገራሉ።