
ከ 4 ሰአት በፊት
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ ነጮችን እያሳደደች ነው ሲሉ የአገሪቱን ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳን በዋይት ሃውስ በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ አፋጠጡ።
ደቡብ አፍሪካ ለዘመናት የቆየ የመሬት ኢ-ፍትሃዊነትን ለመቅረፍ አልሟል ያለችውን የመሬት ፖሊሲ ማውጣቷን ተከትሎ ከአሜሪካ ጋር እየተወዛገበች ትገኛለች።
የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለማሻሻል ወደ አሜሪካ ያቀኑት ሲሪል ራማፎሳ ፤ በደቡብ አፍሪካ ነጮች አርሶ አደሮች እየተገደሉ እንዲሁም እየተሳደዱ ነው በሚል ትራምፕ በጋራ ጋዜጣ መግለጫቸው ላይ ሊያፋጥጧቸው ሞክረዋል።
በዚህ ሳምንት ረቡዕ አሜሪካ ወደ 60 ለሚጠጉ ‘አፍሪካነርስ’ ተብለው ለሚጠሩት የደቡብ አፍሪካ ነጮች ጥገኝነት ከሰጠች ከሳምንት በኋላ ነው ራማፎሳ የሁለቱን አገራት ግንኙነት ለማደስ ወደ ዋይት ሃውስ ያቀኑት።
ነገር ግን ፕሬዚዳንት ትራምፕ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በደቡብ አፍሪካ ውስጥ “በነጮች ላይ የዘር ፍጅት” እየተፈጸመ ነው በሚል በመሪዎቹ የጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ማስረጃ ያሉትን ቪዲዮ እንዲታይ አድርገዋል።
በደቡብ አፍሪካ አብዛኛውን የአገሪቱን የእርሻ መሬቶች የሚቆጣጠሩት አናሳ ነጮች የዘር ጭፍጨፋ ይፈጸምባቸዋል የሚለው በበርካቶች ዘንድ ተቀባይነት ያጣና ከእውነት የራቀ እንደሆነ ይነገራል።
ትራምፕ የተገደሉ ነጭ ገበሬዎች መካነ መቃብር ነው የተባለ በርካታ መስቀል የተደረደበት ምስልን ጨምሮ ሌሎች ተቃውሞዎች ሲሰሙ የሚያሳይ ቪዲዮ አጫውተዋል።
ትራምፕ በደቡብ አፍሪካ የት እንደቀረጸ አላውቅም ብለዋል።
ሆኖም መስቀሎቹ ያለበት ስፍራዎች እንደተባለው መቃብሮች ሳይሆኑ ሳይሆኑ ከአምስት ዓመት በፊት በክዋዙሉ ናታል የተገደሉ ሁለት አርሶ አደሮች መገደላቸውን ተከትሎ ለአውደ ርዕይ የቀረቡ ፎቶዎች ናቸው።
አዘጋጆቹ እነዚህ መስቀል ያለባቸው ስፍራ ለዓመታት የተገደሉ አርሶ አደሮችን የሚወክል አውደርዕይ ነው ብለው ነበር።
ከረቡዕ የዋይት ሃውስ ስብሰባ በፊት ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ከአሜሪካው ጋር ያለውን የንግድ ግንኙነት ማሻሻል ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ነበር።
አሜሪካ ከደቡብ አፍሪካ በሚገቡ ምርቶች ላይ 30 በመቶ ቀረጥ ጥላላች።
ራማፎሳ በዚህ ውይይት ወቅት ትራምፕን ለማስደሰት ተስፋ በማደረግ ሁለት ታዋቂ የደቡብ አፍሪካ ጎልፍ ተጫዎችችን በማምጣት እንዲሁም የአገራቸውን የጎልፍ ታሪክ የሚያሳይ ትልቅ መጽሐፍ በስጦታ አበርክተውላቸው ነበር።
ሁለቱ መሪዎች በኦቫል ቢሮ ያደረጉት ስብሰባ በአክብሮት ተጀምሮ ነበር፤ ሆኖም ትራምፕ ቪዲዮውን ለማሳየት መብራቱ እንዲደበዝዝ መጠየቃቸውን ተከትሎ የውይይቱ ስሜት ጥላ አጥልቶበታል።
በቪዲዮው ላይ የደቡብ አፍሪካ ዋነኛ ተቃዋሚ ጁልየስ ማሌማ አገሪቱ ጨቋኙን የአፓርታይድ ስርዓት ለመገርሰስ በነበረው ትግል ታዋቂ የነበረውን ” ቦየር (አፍሪካነር) ላይ ተኩሱ” የሚለውን ዝማሬ ሲዘፍን ይደመጣል።
ከዚያም በመቀጠል መስቀሎች የተተከሉበት ሜዳ የታየ ሲሆን በመሃልም ትራምፕም ይህ የነጭ አርሶ አደሮች የቀብር ስፍራ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ራማፎሳ በበኩላቸው በቪዲዮው ላይ የተሰሙት ምልክቶች እና ንግግሮች የመንግሥት ፖሊሲ አይደለም በደቡብ አፍሪካ የተዘረጋው መድብለ ፓርቲ ዲሞክራሲ ሰዎች በነጻ ሃሳባቸውን እንዲገልጹ የሚያደርግ ነው” ሲሉ ተከራክረዋል።
ትራምፕ ስልጣን መረከባቸውን ተከትሎ በአሜሪካ እና በደቡብ አፍሪካ መካከል ያለው ግንኙነት ውጥረት የተሞላበት ሆኗል።
ትራምፕ ደቡብ አፍሪካ በቅርቡ ያጸደቀችው የመሬት ፖሊሲ በተወሰኑ “ማኅበሰረሰቦች” ላይ ያነጣጠረ ነው በሚል ለአገሪቱ የሚደረገውን የገንዘብ ድጋፍ አቋርጠዋል።
ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል። የአሜሪካ መንግሥት በደቡብ አፍሪካ አናሳ ነጮች ኢ-ፍትሃዊነት እየተፈጸመባቸው ነው ሲል ከሷል።
ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።