የተገደሉት የእስራኤል ኤምባሲ ሰራተኞች

ከ 4 ሰአት በፊት

በአሜሪካ የሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ሰራተኞች የሆኑ ሁለት ግለሰቦች በዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው የአይሁድ ሙዚየም ደጃፍ ላይ መገደላቸውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናገሩ።

ሟቾቹ አንድ ወንድ እና አንድ ሴት፤ የተተኮሰባቸው በ’ካፒታል ጂዊሽ ሙዚየም’ ውስጥ ከተዘጋጀ አንድ ኹነት እየወጡ በነበረበት ሰዓት እንደሆነ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

ጥቃቱ የታቀደ እንደሚመስልም አክለዋል።

ከምሽቱ ሶስት ሰዓት ገደማ ላይ ግድያ የተፈጸመበት አካባቢ በርካታ የቱሪስት መስህቦች፣ ሙዚየሞች የሚገኙበት ሲሆን የኤፍቢአይ የዋሽንግተን የመስክ ቢሮን ጨምሮ ሌሎች የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ይገኙበታል።

ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ግድያው በተፈጸመበት ሰዓት በርካታ የእስራኤል ኤምባሲ ሰራተኞች ሙዚየሙ ውስጥ ኹነቱን እየታደሙ ነበር።

የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት ኃላፊ ክሪስቲ ኖውም በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ፤ “ዛሬ ምሽት ሁለት የእስራኤል ኤምባሲ ሰራተኞች በአይሁዳውያን ሙዚየም አቅራቢያ ትርጉም የለሽ በሆነ አኳኋን ተገድለዋል” ሲሉ ግድያውን አስታውቀዋል። “እባካችሁ ለሰለባዎቹ ቤተሰቦች ጸሎት አድርጎ። እነዚህን ነውረኛ አጥፊዎች ለፍትህ እናቀርባለን” ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት የእስራኤል አምባሳደር በበኩላቸው ክስተቱን “ነውረኛ ጸረ ሴማዊ ድርጊት” ሲሉ ጠርተውታል።

አምባሳደር ዳኒ ኤክስ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ “ዲፕሎማቶች እና የአይሁድ ማህበረሰብን መጉዳት ቀይ መስመር ማለፍ ነው” ብለዋል።

“የአሜሪካ ባለስልጣናት ይህንን የወንጀል ድርጊት በፈጸሙት ላይ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወስድ እንተማመናለን” ሲሉም ጽፈዋል።

በፖሊስ መኪና እና አምፑላንስ የተዘገጋ መንገድ በምሽት

ክስተቱ ፖሊስ ከፍተኛ ምላሽ እንዲሰጥ ያደረገ ሲሆን የተለያዩ የከተማዋ ዋና መንገዶች ተዘግተው ነበር። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ሰለባዎቹ ወንድ እና ሴት ተብለው እንደተለዩ የዘገቡ ሲሆን ስማቸውን ግን ይፋ አልተደረገም።

የእስራኤል ኤምባሲ ቃል አቀባይ፤ በሙዚየሙ ውስጥ ኹነት ሲታደሙ የነበሩ ሁለት ሰራተኞቻቸው “በቅርብ ርቀት” በተፈጸመ ተኩስ መገደላቸውን አረጋግጠዋል።

ቃል አቀባዩ ታል ናኒም ኮኸን፤ “የአካባቢው እና በፌደራል ደረጃ የሚገኙ ህግ አስከባሪ አካላት ተኩስ የፈጸሙትን በቁጥጥር ስር እንደሚያውሉ እና በመላው አሜሪካ ለሚገኙ የእስራኤል ተወካዮች እና የአይሁድ ማህበረሰቦች ጥበቃ እንደሚያደርጉ ሙሉ እምነት አለን” ብለዋል።

ጥቃቱ በተፈጸመበት ሰዓት የእስራኤል አምባሳደር በሙዚየሙ ውስጥ በተዘጋጀው ኹነት ላይ እንዳልነበሩ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ አሰሳ እየተደረገ ነው። ተጠርጣሪው፤ የአገጭ ፂም ያለው፣ ሰማያዊ ጅንስ እና ሰማያዊ ጃኬት ያደረገ ወንድ እንደሆነ ምንጮች በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

እንደ ሲቢኤስ ዘገባ የጆርጅታውን ዩኒቨርሲቲ ካፒቶል ካምፓስም እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር።

ከአንድ ሰዓት በላይ በካምፓዉ ህንጻ ውስጥ የተዘጋበት አንድ ተማሪ፤ “ለመውጣት ስንፈልግ ታች የነበሩት ፖሊሶች እና ደህንነቶች መውጣት እንደማንችል ነገሩን” ብሏል።

የአሜሪካ የአይሁዳውያን ኮሚቴ ኃላፊ ቴድ ድወች ባወጡት መግለጫ ጥቃቱ የተፈጸመበትን ኹነት ያዘጋጀው የሚመሩት ተቋም እንደሆነ አስታውቀዋል።

“በአዳራሹ ደጃፍ በተፈጸመው በቃላት ሊገለጽ የማይችል የአመጽ ድርጊት እጅጉን አዝነናል” ሀዘናቸውን ገልጸዋል። “በትክክል ምን እንደተፈጸመ ከፖሊስ ተጨማሪ መረጃ በምንጠብቅበት በዚህ ሰዓት፤ ትኩረት እና ልባችን ከተጎዱት እና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው” ብለዋል።

በእስራኤል የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃከቢ፤ “የእስራኤል ህዝብ ዛሬ ጠዋት እየነቃ ያለው በዚህ አሰቃቂ የሽብር ድርጊት ነው” በማለት በኤክስ ገጻቸው ጽፈዋል።

ካፒታል ጂዊሽ ሙዚየም በአሜሪካ እንደሚገኙ ሌሎች የአይሁድ ተቋማት ሁሉ እየጨመረ ባለው ጸረ ሴማዊነት ምክንያት በደህንነት ጉዳዮች ተፈትኗል።

የሙዚየሙ ዋና ዳይሬክተር ቢያትራስ ጋሮዊትዝ፤ “በከተማው በሙሉ፣ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የአይሁድ ተቋማት፤ አንዳንድ ተቋማት ባጋጠሟቸው የተወሰኑ እጅግ አስፈሪ ክስተቶች እና ባለው ጸረ ሴማዊነት ድባብ ምክንያት የደህንነት ስጋር ተፈጥሮብናል” ሲሉ ከረቡዕ ዕለቱ ጥቃት በፊት ለኤንቢሲ ኒውስ ተናግረው ነበር።