
22 ግንቦት 2025, 11:23 EAT
ተሻሽሏል ከ 58 ደቂቃዎች በፊት
ከሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ የታሰሩ የጤና ባለሙያዎችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እንዲፈቱ የመብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ጠየቀ።
በአዲስ አበባ ብቻ ቢያንስ ከ20 በላይ የጤና ባለሙያዎች በዋናው ፖሊስ ጣቢያ ታስረው እንደሚገኙ የገለጸው ተቋሙ መብታቸውን ብቻ በመጠየቃቸው መታሰር እንደማይገባቸው ረቡዕ፣ ግንቦት 13/ 2017 ዓ.ም በኤክስ ገጹ አሳስቧል።
በተጨማሪም ባለሥልጣናቱ በሰላማዊ መንገድ እየተቃወሙ ያሉ ግለሰቦች ላይ እያደረሱ ያሉትን ወከባ እንዲያቆሙ ተቋሙ ባወጣው መግለጫ አጽንኦት ሰጥቷል።
ከሰሞኑ ‘የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ’ በሚል ስያሜ የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ጨምሮ የጤና ሥርዓቱን ያስተካክላሉ ያሏቸው 12 ጥያቄዎች ይመለስ በሚል ካነሱት የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ከ80 በላይ የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸውን የንቅናቄው አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይም በትላልቅ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚያገለግሉ በርካታ የጤና ባለሙያዎችን እያሰሩ እና እያዋከቡ መሆኑን አንድ የንቅናቄው አስተባባሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከዚሁ አድማ ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ የሚገኙትን ጥቁር አንበሳ እና ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታሎችን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች በርካታ የጤና ባለሙያዎች ከሆስፒታል እና ከቤታቸው በፀጥታ ኃይሎች እየተወሰዱ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
የጤና ባለሙያዎች እያደረጉት ላለው እንቅስቃሴ ድጋፋቸውን በመግለጻቸው ግንቦት 3/2017 ዓ.ም ለእስር ተዳርገው የነበሩት የጤና ባለሙያዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ መፈታታቸውን አምነስቲ ገልጾ፤ አጠቃላይ ሁኔታውን አሳሳቢ ብሎታል።
በጤና ባለሙያዎቹ ላይ ሁከትን መቀስቀስ ጨምሮ የቀረበባቸው ክስ፤ አምነስቲ “ባለሥልጣናቱ የዘፈቀደ እስርን እንደ ማፈኛ መሳሪያ መጠቀማቸውን ማሳያ ሌላኛው ምሳሌ ነው” ሲል ተችቶታል።
የጤና ባለሙያዎቹ የተያዙበትም ሆነ የታሰሩበት ምክንያት እንዳልተገለጸላቸው አምነስቲ በዚሁ መግለጫው አስፍሯል።
“መኖሪያ ቤቶች መሳሪያ እና ፈንጂ ፍለጋ በሚል ሽፋን ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ድንገተኛ ፍተሻ ተደርጎባቸዋል። በዚህ ወቅት የተወሰዱባቸው ብቸኛ ዕቃዎች የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቻቸው ነው” ብሏል።
የሥራ ማቆም አድማውን ተከትሎ ፖሊስ የሕክምና ባለሙያዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ረቡዕ፣ ግንቦት 13/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አትቷል።
ኢሰመኮ ፖሊስ “በማህበራዊ ሚዲያዎች ቅስቀሳ አድርገዋል እንዲሁም በሌሎች በሥራ ላይ ባልተገኙ ባልደረቦቻቸው ላይ ዛቻ እና ማስፈራራት አድርሰዋል” በሚል የጤና ባለሙያዎቹን ለእስር እንደዳረጋቸው አትቷል።
“በሕክምና ተቋማት በመካሄድ ላይ ያሉ የሥራ ማቆም አድማዎች እንዲሁም ይህንን ተከትሎ በመንግሥት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎች ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች በር እንዳይከፍቱ ትኩረት ሊሰጣቸው እና ዘላቂ መፍትሔ እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል” ሲል ኢሰመኮ በትናንትናው መግለጫው አትቷል።

የሥራ ማቆም አድማውን ተከትሎ የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ደረጃ ዱጉማ የጤና ባለሙያዎች ወደ ሥራ ገበታቸው ካልተመለሱ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚወሰድባቸው ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።
የጤና ባለሙያዎች ጥያቄ አሁን የመጣ ሳይሆን ለዓመታት ሲንከባለል የቆየ መሆኑን በብሔራዊ ቴሌዥን ግንቦት 12/ 2017 ዓ.ም በቀረቡበት ወቅት የተናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው የጤና አገልግሎት እንዲቋረጥ ማድረግ ፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
ሚኒስትር ዲኤታው ወደ ሥራ ገበታቸው ባልተመለሱ የጤና ባለሙያዎች ላይ መንግሥታቸው ይወስደዋል ብለው ካቀረቧቸው እርምጃዎች አንዱ የጤና የሙያ ፈቃዳቸውን መንጠቅ እንደሆነ ተናግረዋል።
“ወደ ሥራ ካልተመለሱ በስተቀር ሙያዊ ፈቃዳቸውን ይዘው መቀጠል” እንደማይችሉ አስጠንቅቀዋል።
የሕክምና ባለሙያዎቹ ከተመጣኝ ደመወዝ፣ ጥቅማጥቅም፣ የሙያ ዕድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎችን ለጤና ሚኒስትር ሚያዝያ 3/ 2017 ዓ.ም ማቅረባቸው ይታወሳል።
መንግሥት አነዚህን ጥያቄዎች በተሰጠው 30 ቀናት ምላሽ ባለመስጠቱ ከግንቦት 5 ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ መገደዳቸውን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።
ኢሰመኮ በተጨማሪ ከፊል እና ሙሉ የሥራ ማቆም አድማ ተከትሎ በአዲስ አበባ ክትትል ባደረገባቸው አንዳንድ የሕክምና ተቋማት በጽኑ ህሙማን ማዕከል የሚገኙ ታማሚዎችን ጨምሮ በሐኪሞች እጥረት ተገቢውን ሕክምና ማግኘት አለመቻላቸውን ገልጿል።
ከተለያዩ ክልል ከተሞች ረዥም ቀጠሮ ጠብቀው ለሕክምና የመጡ ሕሙማን መንገላታታቸውን፣ በባለሙያዎች እጥረት ምክንያት አንዳንድ የሕክምና ተቋማት ባለሙያዎችን ለረዥም ፈረቃዎች እንዲሰሩ ለመመደብ መገደዳቸውንም በዚሁ መግለጫ አስፍሯል።
ኢሰመኮ ክትትል ካደረገባቸው መካከል ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ እና ዳግማዊ ሚኒልክ ሆስፒታሎች ይገኙበታል ።
ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ከአጋሮ፣ ከአርባ ምንጭ፣ ከባህርዳር፣ ከፍቼ፣ ጎባ፣ ሐዋሳ እና ጅማ ከተሞች መረጃ ማሰባሰቡን አትቷል።
“በጤናው ዘርፍ የሚደረግ የሥራ ማቆም አድማ በማኅበረሰቡ የጤና እና በሕይወት የመኖርመብት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል የሚችል በመሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ ግልጽ እና አሳታፊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲያመቻች እንዲሁም የሕክምና ባለሙያዎችም የኅብረተሰቡን የጤና እና በሕይወት የመኖር መብቶችን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ ጥያቄዎቻቸውን እንዲያቀርቡ” የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ጥሪ ማቅረባቸው በዚሁ መግለጫ ላይ ሰፍሯል።