ምግብ

22 ግንቦት 2025

የርካሽ ምግቦች ዘመን ያለፈ ይመስላል። በጥቂት ብር ዘንቢል ሙሉ የምግብ ሸቀጥ መግዛት፣ አልያም ሁለት ሦስት ምግብ አዝዞ መብላት ከቀረ ከራረመ።

ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሌሎች የዓለም ክፍሎች ጎልቶ የሚታይ የሸማችን ኪስ የፈተነ ጉዳይ ነው።

በብራዚል የቡና አፍቃሪዎች “የቡና ጣዕም ወዳለው ለስላሳ መጠጥ” ፊታቸውን ካዞሩ ቆይተዋል።

በአሜሪካ የእንቁላል ዋጋ ንረት የምግብ ቤቶች ወጪን ተፈታትኖታል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ከምግብ ዘይት እስከ ፍራፍሬ ጭማቂ ድረስ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ተስተውሏል።

ሩሲያ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2022 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ የዓለም የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጭማሪ አሳይቷል።

ባለፉት ስድስት አስር ዓመታት ከታየው የዋጋ ንረት አንጻር አሁን ያለው ሲሰላ ምንም እንኳ መጠነኛ ቅናሽ ያሳዩ ቢሆንም ከፍተኛ ነው።

በዓለም አቀፉ የምግብ ፖሊሲ እና ጥናት ተቋም ውስጥ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ሮብ ቮስ “የርካሽ ምግብ ጊዜ አክትሟል። ዓለም ከአዲሱ እውነታ ጋር መላመድ አለበት” ይላሉ።

ምግብ ምን ያህል ተወዷል?

የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና የእርሻ ድርጅት (ፋኦ) ሰነድ እንደሚያሳየው ሩሲያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 ዩክሬንን ከወረረች ወዲህ የምግብ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ንሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት መረጃ በአትክልት ዘይት፣ በጥራጥሬ፣ በሥጋ፣ በስኳር እና በወተት ተዋጽኦዎች ላይ ያለውን የዋጋ ጭማሪ ተመልክቷል።

በዚህ መረጃ መሠረት የእነዚህ ምግቦች ዋጋ በተናጠልም ሆነ በጥቅል በመጋቢት 2022 ከፍተኛ ጭማሪ አሳይተዋል።

በ2023 ዳግም ቅናሽ ቢያሳዩም ቀስ እያለ መጨመራቸው ተገልጿል።

የሕዝብ ቆጠራ እና የምጣኔ ኃብት ባለሙያው ሆዜ ኡስታኬ ዲኒዝ ያለፉትን 100 ዓመታት መለስ ብለን የምንመለከት ከሆነ የምግብ ዋጋ ጭማሪ መታየት ከጀመረ አስር ዓመታት ማሳለፉን ይናገራሉ።

ዲኒዝ ይህ ጉዳይ ለዓለም የምግብ ዋስትና “አደገኛ” አካሄድ መሆኑን ይገልጻሉ።

ከዚህ በፊት በዓለም ላይ የምግብ ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየው እአአ በ1973 የተከሰተውን የነዳጅ ዘይት ቀውስ ተከትሎ በ1974 እና 1975 ነበር።

በወቅቱ የነዳጅ ዘይት ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ በርካታ የምግብ እና የመጓጓዣ ኢንዲስትሪዎች ሳይቀሩ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ነበር።

ሥጋ

ጦርነት እና የአፈር ማዳበሪያ

ሩሲያ እና ዩክሬን የዓለማችን ዋነኛ የስንዴ እና የሱፍ ዘይት ላኪዎች መሆናቸውን ተከትሎ በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት የዓለም የምግብ ገበያን አውኳል።

ከዚህ በተጨማሪም ዩክሬን ከዓለማችን በቆሎ አምራች አገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት።

በ2022 የመጀመሪያ ወራት ሩሲያ የዩክሬንን ወደቦች መዝጋቷን ተከትሎ የታዩ የዋጋ ጭማሪዎች ቢኖሩም በኋላ ላይ በሁለቱ ተዋጊ አገራት መካከል በተደረገ ስምምነት እና ዩክሬን ሌላ የመርከብ ጉዞ አቅጣጫን ተጠቅማ ምርቶችን መላክ በመጀመሯ ቅናሽ ታይቶ ነበር።

በዓለም ምግብ እና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ውስጥ ከፍተኛ ኢኮኖሚስት የሆነችው ሞኒካ ቶቶቫ ተጽዕኖው ብዙዎች ፈርተውት እንደነበረው አልነበረም ትላለች።

ይኹን እንጂ ግጭቱ ለአርሶ አደሮች ሌላ ስጋትን ደቅኗል፤ የማዳበሪያ ዋጋ መናር።

ለማዳበሪያ ምርት የተፈጥሮ ጋዛ ቁልፍ ግብዓት ነው።

ከዚህ በፊትም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም ከ2022 የዩክሬን ጦርነት መቀስቀስ በኋላ የጋዝ ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ ዋጋው አሻቅቧል።

ምርት፣ የአመጋገብ ባሕል እና ፍላጎት

በዓለም አቀፍ ደረጃ የምግብ ዋጋ ዝቅተኛ የነበረበት ምክንያት ትርፍ ማምረት ተችሎ ስለነበር መሆኑን ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የዓለም አቀፍ የምግብ ፖሊሲ ​​ጥናት እና ምርምር ኢንስቲትዩት ባልደረባው ቮስ “ከ1970ዎቹ ጀምሮ ዝቅተኛ የምግብ ዋጋ የታየበት ዘመን የመጣው በግብርና ምርታማነት ከፍተኛ ዕድገት ላይ በተመዘገበው ውጤት ነው” ይላል።

በዚህ ወቅት “አረንጓዴ አብዮት” ታይቷል።

በወቅቱ ከፍተኛ ምርት በሚሰጡ የእጽዋት ዝርያዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ የነበረ ሲሆን የተሻሻለ የእርሻ ቴክኒኮች ሽግግርም ማድረግ ተችሎ ነበር።

ነገር ግን ይህ የምርታማነት ዕድገት አሁን አዝጋሚ ሆኗል። የምግብ ፍላጎት እየጨመረ በሄደ ቁጥር ዋጋው በአማካይ ጨምሯል።

በተለይ በማደግ ላይ ባሉ አገራት ውስጥ የሕዝብ ብዛት እየጨመረ እንዲሁም የአመጋገብ ባሕል እየተቀየረ በመሆኑ ፍላጎት እያደገ ነው።

ዲኒዝ “ሰዎች ሥጋ፣ የወተት ተዋጽኦዎች፣ ፍራፍሬ እና አትክልቶች በብዛት ይመገባሉ” ብለዋል።

ነገር ግን በእነዚህ ዘርፎች ያለው ምርታማነት ከፍላጎት ጋር ባለመመጣጠኑ ምግብ ተወድዷል።

የተለያዩ ሰዎች ምግብ ሲያነሱ

የአየር ንብረት ለውጥ

ለምግብ ዋጋ መጨመር የአየር ንብረት ለውጥ የራሱ አስተዋጽኦ አለው።

የዓለም ሙቀት መጨመር እአአ በ2035 የምግብ ዋጋ ግሽበትን በ3.2 በመቶ እንደሚጨምረው የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ እና ፖትስዳም ኢንስቲትዩት ባለፈው ዓመት ይፋ አድርገዋል።

የዓለም ባንክ በ2022 ባወጣው ሪፖርት ባለፉት 60 ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ የግብርና ምርታማነትን አዝጋሚ አድርጎታል።

አብዛኞቹ የግብርና ምርቶች በአየር ንብረት ላይ ጥገኛ የሆኑ ናቸው የሚሉት ቶቶቫ፣ “በጣም እርግጠኛ የማይኮንበት መስክ ነው” ብለዋል።

እንደ የወይራ ዘይት፣ ቡና፣ ካካዋ ያሉ ምርቶች ቋሚ ከሆነ ዛፍ ላይ ምርታቸው ስለሚሰበሰብ እና በጥቂት አገራት ላይ ብቻ ስለሚበቅሉ የበለጠ ተጋላጭ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የቡና ምርት በከባድ የአየር ሁኔታ ምክንያት በቀላሉ ሊጎዳ ይችላል።

በየካቲት ወር በብራዚል ለሁለት ዓመት የዘለቀውን ድርቅ ተከትሎ የአረቢካ ቡና ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል።

ተባይ እና በሽታዎች

በአሜሪካ የተከሰተው የኤቪየን ኢንፉሉዌንዛ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዶሮዎች እንዲሞቱ አድርጓል።

ከ2021 ጀምሮ የእንቁላል ዋጋ ከሦስት እጥፍ በላይ ጭማሪ አሳይቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ለዋጋ መጨመሩ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ፖሊሲዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

የተወሰኑ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ሕግ አውጪዎች እና የወትዋች ቡድን አባላት ደግሞ የእንቁላል አምራቾች ሰው ሠራሽ የሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገው ሊሆን የሚችል ስጋት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በተከሰተ የወፍ ጉንፋን (በርድ ፍሉ) የተነሳ በደቡብ አፍሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በጃፓን ከአገር አገር ያለው ተጽዕኖ ቢለያይም የዋጋ ጭማሪ ታይቷል።

በቅርቡ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ካሳዩ የምግብ እህሎች መካከል የብርቱካን ጭማቂ አንዱ ነው። ጭማሪው ባለፈው መስከረም ወር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር።

በብራዚል እና በአሜሪካ የተከሰተው የብርቱካን ተክል በሽታ ብርቱካኑ እንዲመር የሚያደርግ ሲሆን፣ ቀስ በቀስ ደግሞ ተክሉን ያደርቀዋል።

በብራዚል የተከሰተው ድርቅ እና በፍሎሪዳ የነበረው ከውቅያኖስ ላይ የሚነሳ ማዕበል የምርት መቀነስ አስከትሏል።

በእርግጥ አሁን ዋጋው መቀነስ አሳይቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ የተጣለባቸውን አገራት ዝርዝር ይዘው
የምስሉ መግለጫ,ዶናልድ ትራምፕ ታሪፍ የተጣለባቸውን አገራት ዝርዝር ይፋ ባደረጉበት ጊዜ

ታሪፍ እና የንግድ አለመረጋጋቶች

የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ አገራቸው በሚገቡ ምርቶች ላይ የጣሉት ታሪፍ የምግብ ዋጋን በከፍተኛ ደረጃ እንዲንር ምክንያት ከሆኑ ነገሮች መካከል ይጠቀሳል።

ለአርሶ አደሮች የማይገመቱ ነገሮች ችግር ማስከተላቸው አይቀርም።

“የንግድ ጦርነት ከተቀሰቀሰ እና ታሪፎች የሚጣሉ ከሆነ” ይላሉ ቶቶቫ፣ “ቁልፍ የውጪ ገበያን ያጣሉ፤ በግብርና መካከል እያሉ ምርታቸውን እንዲቃኙ ያስገድዳቸዋል።”

ከዚህ ባሻገር ቀጥተኛ ያልሆነ ተጽዕኖም አላቸው።

ቻይና በትራምፕ አስተዳደር የተጣለባትን ታሪፍ ተከትሎ በአሜሪካ አኩሪ አተር ላይ ተጨማሪ ታሪፍ ስትጥል የቻይና አስመጪዎች በብራዚል የሚገኙ አቅራቢዎችን ያማትራሉ።

የዓለም ንግድ ድርጅት በቅርቡ ባወጣው መረጃ መሠረት ይህ ፍላጎታቸውን ስለማያሟላ የዋጋ ጭማሪ ማስከተሉ አይቀርም ብሏል።

ቮስ አሜሪካ የጣለችው ታሪፍ የዓለም ምግብ ዋጋን በማናር ላይ ያለው ጫና ወይንም የምጣኔ ኃብት ዕድገት እንዲያዘግም በማድረግ ላይ ያለው ተጽዕኖ ግልጽ አይደለም ይላሉ።

ባለሙያው ምንም እንኳ የምጣኔ ኃብት ዕድገት አዝጋሚ ቢሆንም በዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገራት የምግብ ዋጋ ግሽበት አይቀርም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።

ምክንያቱም የእነዚያ አገራት የራሳቸው የወጪ ንግድ ፍላጎት ማሽቆልቆሉ ገንዘባቸውን ሊያዳክም ስለሚችል፣ ምግብን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት በጣም ውድ ያደርግባቸዋል ሲል ያስረዳል።

“ነገሮች በትክክል እንዴት እንደሚሄዱ እርግጠኝነት የለም” ብለዋል፤ “በአጠቃላይ ግን በአድማሱ ላይ ያለው መልካም ዜና ትንሽ ነው” ብለዋል ።

የእያንዳንዱን ኪስ የሚነካው ዋጋ

እአአ ከ2022 ጀምሮ የምግብ ዋጋ በዓለም ገበያ ላይ ቢቀንስም፣ ይህ ማለት ግን ሸማቾች በየሱቁ የሚከፍለው ዋጋ ዝቅ ያለ ነው ማለት አይደለም።

በዓለም ባንክ ከፍተኛ የምጣኔ ኃብት ባለሙያ የሆኑት ዳዊት መኮንን የምግብ ዋጋ በበርካታ አገራት የዛሬ አራት ዓመት ከነበረው ከፍ ያለ ነው። ይህ ደግሞ “የምግብ የማግኘት አቅምን በከፍተኛ ሁኔታ ይሸረሽራል።”

በምግብ እጥረት የሚጎዱ ሰዎች ቁጥር በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጨመረ ነው።

በ2017 እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር 7.1 በመቶ የነበረው አሁን 9.1 በመቶ መድረሱን የዓለም ምግብ ድርጅት መረጃ ያሳያል።

የዓለም ምግብ ድርጅት በቅርቡ ባደረገው ዳሰሳ የዓለም አንድ ሦስተኛ ሕዝብ፣ ከአፍሪካ ደግሞ ሁለት ሦስተኛው ጤናማ አመጋገብ የለውም።

አንዳንድ የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች በሚቀጥሉት 12 ወራት እየቀነሰ ይሄዳል ብለው ቢገምቱም፣ በርካታ ባለሙያዎች ግን በሚመጡት ጊዜያት እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል ይናገራሉ።

“ዋጋ እንዲጨምር ከሚያደርጉ ገፊ ምክንያቶች መካከል ምርትን ለማምረት የሚወጡ ወጪዎች፣ የአቅርቦት ሰንሰለት መረበሽ፣ የአየር ንብረት ለውጥ እንዲሀም የንግድ ፖሊሲዎች ባሉበት ይቆያሉ” ሲሉ ቮስ ያስጠነቅቃሉ።