ቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ኦሮሚያ ክልሎችን የሚያሳይ ካርታ

22 ግንቦት 2025

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ጋር በሚጎራበት ቀበሌ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ስድስት ህጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 16 ሰዎች መገደላቸውን እና 14 ሰዎች መቁሰላቸውን ነዋሪዎች እና አንድ የክልሉ ምክር ቤት አባል ተናገሩ።

የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ እና ነዋሪዎች በቀበሌው ለተፈጸመው ጥቃት “ሸኔ” ሲሉ የጠሯቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች ተጠያቂ አድርገዋል።

ታጣቂዎች በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምዥጋ ወረዳ ወደሚገኘው አንገር ሜጢ ቀበሌ በመግባት ጥቃት የፈጸሙት ትናንት ረቡዕ፣ ግንቦት 13/2017 ዓ.ም. ከንጋት 12 ሰዓት ገደማ ጀምሮ መሆኑን ሁለት ነዋሪዎች እና የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ለሜሳ ኔኖ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ታጣቂዎች ወደ ቀበሌው ነዋሪዎች ቤቶች በመግባት ተኩስ መክፈታቸውን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

“ያለምንም ነገር፣ ያለምንም ግጭት 12 ሰዓት ላይ ነው መጥተው ሰው መጨፍጨፍ የጀመሩት” ብለዋል። ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ሌላ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ንጋት ላይ የጀመረው ጥቃት “ቀኑን ሙሉ” መዝለቁን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“[ታጣቂዎቹ] ጠዋት 12 ሰዓት ከቤት አውጥተው ነው የገደሉት” ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል እና በክልሉ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ለሜሳም በተመሳሳይ ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

አቶ ለሜሳ በቀበሌው በተፈጸመው ጥቃት 16 ሰዎች መገደላቸውን እና አራት ነዋሪዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

ከተገደሉት መካከል በርካታዎቹ ህጻናት እና ሴቶች መሆናቸውንም አክለዋል።

የምክር ቤት አባሉ፤ “አንድ ሙሉ ቤተሰብ ነው የጨረሱት። ሁለተኛ ቤተሰብ ደግሞ ባለቤቱ፣ ወንዱ ብቻ ነው የተረፈው፤ ሙሉ ልጆቹ ሴቶቹን ጨምሮ ጨርሰዋቸዋል” ሲሉ የደረሰውን ጥቃት ገልጸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የቀበሌው ነዋሪዎች በበኩላቸው የደረሰውን ጉዳት ከዚህም ከፍ ያደርጉታል። የተገደሉት ሰዎች ብዛት 17 መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የቆሰሉ ሰዎችን ብዛት 14 ያደርሱታል።

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ ከተገደሉት ሰዎች መካከል ስድስቱ እድሜያቸውን ከሁለት እስከ 14 የተገመቱ ህጻናት ናቸው። ከሞቱ ሰዎች መካከል ሌሎች ስድስቱ ደግሞ ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ከተገደሉት ህጻናት መካከል ሶስቱ የልጅ ልጆቻቸው እንደሆኑ፤ ቀሪዎቹ ሶስቱ ደግሞ የወንድማቸው ልጆች እንደሆኑ አስረድተዋል።

ሶስቱ የልጅ ልጆቻቸው የሁለት፣የሶስት እና የ12 ዓመት ሴት ልጆች እንደሆኑ ገልጸዋል። የወንድማቸው ባለቤት እና ልጆች መገደላቸውንም አክለዋል።

ታጣቂዎች በፈጸሙት በዚሁ ጥቃት 14 የቀበሌው ነዋሪዎች መቁሰላቸውን የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፤ትናንት አመሻሽ ላይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ አከባቢው ከገቡ በኋላ ከሁለቱ በቀር ሌሎቹ ወደ ህክምና መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

አንድ ነዋሪ፤ አንድ ሰው ለህክምና ከተወሰደ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ታጣቂዎቹ ቤቶችን እና ሞተር ሳይክሎችን ማቃጠላቸውን እንዲሁም የነዋሪዎችን እንስሳት ነድተው መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

የቀበሌዋ ነዋሪዎች ጥቃቱን በመሸሽ ጫካ ውስጥ ተጠልለው እንደሚገኙም ተናግረዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና የክልሉ ምክር ቤት አባል አቶ ለሜሳ ጥቃቱ የተፈጸመው “ሸኔ” ሲሉ በጠሯቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ታጣቂዎች መሆኑን ገልጸዋል።

ምዥጋ ወረዳ ከኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሶስት ወረዳዎች ጋር እንደሚዋሰን የሚያስረዱት የምክር ቤት አባሉ አቶ ለሜሳ፤ “ምዥጋ ወረዳ ውስጥ ካሉ 12 ቀበሌዎች አንገር ሜጢ የሚባለው ቀበሌ ኦሮሚያ ጫፍ ላይ ነው ያለችው፤ የሁለት ኪሎ ሜትር ልዩነት ነው ያለው” ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ባለፈው ሚያዝያ ወር ውስጥ ሌሎች ሁለት ጥቃቶችን ፈጽመው ነዋሪዎችን መግደላቸውን ገልጸዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም መንገሻ ጥቃቱ መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በቀበሌው የተፈጸመው “የተለመደ የታጣቂ ጥቃት” መሆኑን የተናገሩት አቶ ቢኒያም፤ “የደረሰው ጉዳት ስላልተረጋገጠ አሁን ቁጥሩን እርግጠኛ መሆን አንችልም” ብለዋል።

የደረሰውን ጉዳት ለመለየት ማጣራት እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። ጥቃቱን የፈጸሙት የትኛዎቹ ታጣቂዎች እንደሆኑ ጥያቄ የቀረበላቸው ኃላፊው፤ “የሸኔ ታጣቂ ነው” ብለዋል።

ሠላም ግንባታ እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊው በአሁኑ ሰዓት አካባቢው ላይ የጸጥታ ኃይሎች መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ቢኒያም፤ “የጸጥታ ኃይል በቦታው ደርሷል፤ አስፈላጊ ስራዎች እየተሰሩ ነው የሚገኙት። ማህበረሰቡም እየተመለሰ ነው። በግለሰብ ደረጃ ወደ ቀዬው ያልተመለሰ ሰው ካልሆነ በስተቀር አሁን አካባቢውን ደህነቱን አስጠብቀናል” ሲሉ ነዋሪዎች ሸሽተው ጫካ ውስጥ ናቸው መባሉን አስተባብለዋል።