ካትሪን ሜንጋኒ

ከ 28 ደቂቃዎች በፊት

የ12 ዓመቷ ካትሪን ሜንጋኒ በየዓመቱ እንደምታደርገው ከቤተሰቦቿ ጋር በመሆን ለገና ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ በሄደችበት ሕይወቷን እስከ መጨረሻ የቀየረው አጋጣሚ ተፈጠረ።

ገና አፍላ ታዳጊ የነበረችው ሜንጋኒ ምንም መረጃው ሳይኖራት ወላጆቿ በአካባቢው ከምትገኝ የጤና ባለሙያ ጋር ተነጋግረው አስገረዟት።

ማሳሰቢያ፡ ይህ ታሪክ ስለ ሴት ልጅ ግርዛት በዝርዝር ይመለከታል።

በኬንያ ዋና መዲና ናይሮቢ ተወልዳ ያደገችው ካትሪን በአገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ከሚካሄዱ የባሕላዊ ድርጊቶች የተጠበቀች መሆኗን ታስብ ነበር።

ማንም እንደሚገምተው ወላጆቿ በደንብ የተማሩ፣ በከተማ የሚኖሩ እና የሚሠሩ በመሆናቸው የተለያዩ ልማዳዊ ድርጊቶች ሊፈጸምባት የሚችል ሴት አድርጋ ራሷን አትቆጥርም ነበር።

ነገር ግን ከ30 ዓመታት በፊት ያጋጠማት ያ ነው።

“ከናይሮቢ ወደ ገጠር ቤታችን ስንጓዝ እዚያ እስክንደርስ ድረስ ይህ እንደሚሆን አላውቅም ነበር። ነገር ግን ድግስ እየተዘጋጀ ነው ተብሎ ወሬ እንደነበር አስታውሳለሁ።”

የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) እንዳስታወቀው በዓለም ላይ ከ230 ሚሊየን በላይ ልጃገረዶች እና ሴቶች ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል።

ድርጊቱ በአፍሪካ እና በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ 30 አገራት ላይ ያተኮረ ቢሆንም በአንዳንድ የእስያ እና የላቲን አሜሪካ አገራት እንዲሁም በምዕራብ አውሮፓ፣ በሰሜን አሜሪካ፣ በአውስትራሊያ እና በኒውዚላንድ በሚኖሩ ስደተኞች መካከልም እንደሚተገበር የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።

“በሕክምና የተደረገ የሴት ልጅ ግርዛት” እየተባለ የሚጠራው በሕክምና ወይም በጤና ባለሙያ የሚደረገው ግርዛት ሆን ተብሎ የሴትን ውጫዊ ብልት መቁረጥ ወይም ማስወገድን ያመለክታል።

ብዙውን ጊዜ የብልት ከንፈር እና ቂንጥርን በአጠቃላይ ወይም በከፊል ማስወገድ ወይም መቁረጥን የሚያካትት ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ደግሞ “ከሕክምና ውጭ በሆኑ ምክንያቶች የሴት ብልት አካላትን የሚጎዳ ማንኛውም አሰራር” ሲል ይገልፀዋል።

“በሕክምና የሚደረግ የሴት ልጅ ግርዛት” በሴት ልጅ አካላዊ፣ ሥነልቡናዊ እና ጾታዊ ጤና ላይ አደጋ ቢያስከትልም ልማዱን ለመጠበቅ እንደ አስተማማኝ መንገድ ይታያል።

ግርዛቱ በሕክምና ባለሙያ የሚከናወን ቢሆንም የቀዶ ጥገና መሳሪያዎችን መጠቀም የበለጠ ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።

በዓለም ላይ በሕክምና ባለሙያዎች የሚፈጸም ግርዛት

• ግብፅ (38 በመቶ)፣ ሱዳን (67 በመቶ)፣ ጊኒ (15 በመቶ)፣ ኬንያ (15 በመቶ) እና ናይጄሪያ (13 በመቶ) ግርዛቶች በሕክምና ባለሙያዎች የፈጸማሉ

• በአፍሪካ ከ144 ሚሊዮን በላይ ሴቶች በሕክምና ባለሙያዎች የተገረዙ ናቸው

• በእስያ ከ80 ሚሊዮን በላይ ሴቶች፣ ስድስት ሚሊዮን ደግሞ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ ሴቶች በሕክምና ባለሙያዎች ተገርዘዋል

• ሌሎች ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ሴቶች በተቀረው ዓለም አነስተኛ ቁጥር ባላቸው የማኅበረሰብ አባላት እና በስደተኞች መዳረሻ አገሮች ተጠቂ ናቸው

የካትሪን ወላጆች በሕክምና የተደረገ የሴት ልጅ ግርዛት ሂደትን በመምረጥ በአካባቢው ያለ የጤና እንክብካቤ ሠራተኛ እንዲገርዛት አድርገዋል።

አሁን ነርስ የሆነችው የ42 ዓመቷ ካትሪን “በ12 ዓመቴ ራሴን በሚገባ ስለማውቅ ስለ ጉዳዩ በርትቶ ለመናገር በጣም ረጅም ጊዜ ፈጅቶብኛል።”

ግርዛቱ ከመፈጸሙ ከቀናት በፊት ካትሪን “መገረዝ” እንዳለባት ሲወራ ሰማች። ምን ማለት እንደሆነ ግን አልገባትም።

“ለጓደኞቻቸው፣ ለቤተሰባቸው በሥነ ሥርዓት ላይ እንዲገኙ ይጠሩ ነበር” በማለት ታስታውሳለች።

“ቅልጥ ያለ ክብረ በዓል ነበር።”

ከጥቂት ቀናት በኋላ የጤና ባለሙያዋ ቤታቸው መጣች።

” በዙሪያዬ የነበሩትን ሴቶች አይቻለሁ’ እየዘፈኑ ነበር ደግሞም በጣም ደስተኞች ነበሩ” ትላለች።

“ከዚያም እንዲቀመጡ ተገደዱ፤ የጤና ባለሙያዋ ጓንት ካደረገች በኋላ ሌሎች ሴቶች ሲይዙኝ የቀዶ ጥገና ምላጭ አወጣች።

“አስታውሳለሁ በጣም ነበር የምደማው፤ ከተለያዩ ነገሮች የተጠመቀ መጠጥ ደሜ እንዲቆምልኝ በማለት ይሰጡኝ ነበር”

ከዚያ በኋላ ካትሪን በግራ መጋባት እና “በድንጋጤ” ውስጥ መሆኗን በቻ ነው የምታስታውሰው።

“አእምሮዬ ላይ ያደረሰው ጠባሳ አሁንም እንዳለ ነው። ከምንም ግዜውም በላይ የከፋም ነው።”

“አውቃታለሁ፤ እናም እጠላታለሁ”

ካትሪን ነርስ ስትሆን በደቡብ ምዕራብ ኬንያ በምትኖርበት የሚጎር ማኅበረሰብ ውስጥ በሴቶች እና ልጃገረዶች ላይ በጎ ተጽዕኖ ለማሳረፍ ትሰራለች።

ላለፉት 20 ዓመታት በነርስ ሙያ ውስጥ የቆየችው ካትሪን፣ ግርዛትን ጨምሮ ጾታን መሰረት አድርጎ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ከማኅበረሰቡ ጋር በቅርበት ትሠራለች።

“በማኅበረሰቤ ውስጥ የማየውን ነገር ለመግታት እንደምችል ተሰማኝ። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ በርካታ ነፍሰ ጡሮች ነበሩ፤ በጣም ትናንሽ ልጃገረዶች ‘ተገርዘዋል አሁን ዝግጁ ናቸው’ ስለሚባል አርግዘዋል።”

ለብዙ ዓመታት ካትሪን በዚያው ከተማ እርሷን የገረዘቻት የሕክምና ባለሙያ ተመሳሳይ ተግባር ስትፈጽም ተመልክታለች።

“የማውቃት ሴት ነች እና ለብዙ ዓመታት ጠልቻት ቆየሁ። በከተማው ውስጥ ክሊኒክ ነበራት። ለእኔ፣ አንተ ጠባቂዬ ነህ። ነገር ግን የምትጎዳኝም አንተው ነህ፤ እና ይህ ለጤንነቴ ምንም ጥቅም እንደሌለው ጠንቅቀህ ታውቃለህ። ነገር ግን ግድ ሳይሰጥህ አደረግከው”

አክላም “ከእሷ ጋር ለመጋፈጥ የፈለግኩበት ጊዜ ነበር፣ ከጊዜ በኋላ ግን በራሴ ውስጥ ፈውስ መፈለግ እንዳለብኝ ተገነዘብኩ።

ካትሪን (በስተግራ ) ከእናቷ ጋር

ካትሪን ስላጋጠሟት ነገር ከወላጆቿ ጋር አልተወያየችም።

“ምክንያቱም ያለፈውን ታሪክ መዝዤ ጥፋተኛነት ማምጣት አልፈለግኩም።”

የካትሪን እናት አሁን ልጃገረዶች እና ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለመከላከል ልጃቸው ለምትሰራው ስራ ትልቅ ደጋፊ ከሆኑት መካከል አንዷ ናቸው።

ኬንያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2001 የሴት ልጅ ግርዛትን በከፊል ያገደች ሲሆን፣ በ2011 ደግሞ ሙሉ በሙሉ ከልክላለች።

ሆኖም በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ማኅበራዊ እና ባህላዊ ደንቦች ውስጥ ተቀባይነት ያለው የሴት ልጅ ግርዛት አሁንም ይፈጸማል።

ካትሪን የሴት ልጅ ግርዛትን መፈጸም በወቅቱ ሕገወጥ ስላልነበረ በገራዧ የሕክምና ባለሙያ ወይም በወላጆቿ ላይ የሕግ ቅጣት ሊጣል እንደሚችል አታምንም።

በሴት ልጅ ግርዛት ዙሪያ ከተስፋፉ የተሳሳቱ እምነቶች መካከል ጥቂቶቹ ለትዳር እንደ መዘጋጃ መታሰቡ ነው።

​​ወደ ሴትነት መግባትን የሚያመለክት እና እንዲሁም በኅብረተሰቡ ዘንድ የንፅህና ምልክት ተደርጎ መቆጠሩ ነው።

ካትሪን በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ሁለት ሴት ልጆች ያሏት ሲሆን፣ ከእነርሱ ጋር ስለ ግርዛት ግልጽ ውይይት ታደርጋለች።

“አሁንም የጤና ባለሙያዎች አሉ . . . ‘ካትሪን ሴት ልጆችሽን ካላስገረዝዥ እኛ እንገርዛቸዋለን፤ ባህላችን ነው’ የሚሉ’

“ትልቋ ልጄ 18 ዓመቷ ታናሿ ደግሞ 16 ዓመት ሆኗታል። አለመገረዛቸው በትልቁ የምኮራበት ነው”

“እንዳገባሁ በተደጋጋሚ ተናግረውኝ ነበር። ሰዎች ‘ልጆችሽ መገረዝ አለባቸው’ ይሉ ነበር። ብዙ ጊዜ ስድብ ሁሉ ነበረው”።

“መገረዜን ነገርኳቸው፣ እና አሁን ድረስ በአእምሮዬ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል፤… አንዳንድ ጊዜ፣ የሽንት ቱቦዎች ኢንፌክሽን ያጋጥመኛል።”

‘በሕክምና ባለሙያዎች ስለ ሚፈጸም ግርዛት አይወራም”

በደቡብ ምዕራብ ኬንያ የሚጎሪ ካውንቲ መንገድ

በኬንያ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 የሆኑ ልጃገረዶች ላይ የሚፈጸም ግርዛት ባለፉት 30 ዓመታት በግማሽ ቀንሷል።

የኬንያ መንግሥት የሴት ልጅ ግርዛትን ለማስቀረት በርካታ ሥራዎችን በሰራ ቁጥር፣ ካትሪን ገራዦች በሕግ እንዳይጠየቁ አንዳንድ አሳሳቢ ተግባራት ውስጥ መግባታቸውን ትናገራለች።

በተለምዶ፣ ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 12 ለሆኑ ታዳጊዎች የሚፈጸም የግርዛት ሥነ-ሥርዓቶች የሚከናወኑት በማለዳ ነው።

አሁን በመንግሥት ዓይን ውስጥ ላለመግባት ከስድስት ዓመት በታች ያሉ ልጃገረዶችም ላይ ግርዛት ሲፈጸም ይስተዋላል።

“በሕክምና ባለሙያዎች የሚፈጸም ግርዛት አይወራም” ስትል ታስረዳለች። ሰዎች ስለ ጉዳዩ መናገር ስለማይፈልጉ መረጃው እየተገኘ አይደለም።

“ይገርዛሉ፤ ይደብቃሉ” ስትል አክላለች።

“ግርዛትን የሚፈጽሙ ማኅበረሰቦችን ለመሸፈን ብዙ ርቀት ይሄዳሉ። አሁንም ሴት ልጆችን ይገርዛሉ፤ ግን ወንድ ልጅ አስመስለው እያለበሱ ነው።

“እንዳይያዙ በፍጥነት ያከናውኑታል ስለዚህ ብዙ ጉዳት ያደርሳሉ። ልጃገረዶቹ ያለ አግባብ ይገረዛሉ፣ ስለዚህ ወደ ሕክምና ተቋም መጥተው ሲመረመሩ የሆነ ሰው በችኮላ እንደፈጸመው ያስታውቃል።”

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2020 በግምት 52 ሚሊዮን የሚሆኑ ልጃገረዶች እና ሴቶች በዓለም ዙሪያ በጤና ባለሙያዎች ግርዛት ተፈጽሞባቸዋል።

ይህም ከአራት ግርዛቶች ውስጥ አንዱ ማለት ነው ይላል ዩኒሴፍ።

የዓለም ጤና ድርጅት በሚያዝያ ወር፣ በሕክምና ባለሙያዎች የሚፈጸም የሴቶች ግርዛት ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎ መመሪያዎችን አሻሽሏል።

አንዳንድ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በጤና ባለሙያዎች የሚፈጸሙ ግርዛቶች ከባድ እና ጥልቅ የሆነ መቆረጥን ስለሚያስከትሉ የበለጠ አደገኛ ይሆናሉ ሲል የዓለም ጤና ድርጅት ገልጿል።

“በሕክምና ባለሙያዎች የሚፈጸም” እየተባለ ስለሚጠራ ድርጊቱን ሕጋዊ የማስመሰል አደጋ መደቀኑም ተገልጿል።

“የሕክምና ባለሙያዎች በዘፈቀደ ነው የሚያከናውኑት”

የምክክር ባለሙያ ሴቶችን ስታነጋግር

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2008 ግብፅ የሴት ልጅ ግርዛትን በይፋ አግዳለች።

ነገር ግን አሁንም በዓለም ላይ ካሉት ከፍተኛ የሴት ልጅ ግርዛቶች መካከል መሆኑን፣ 87 በመቶ ዩኒሴፍ ይገልጻል።

ግብፅ እንዲሁ “በሕክምና ባለሙያዎች” የሚፈፀም የሴት ልጅ ግርዛት ያለባት አገር ነች።

ዶክተር ሬሃም አዋድ “የሴት ልጅ ግርዛትን እንዴት ማከናወን እንደሚቻል የሰለጠነ ማንም የለም፤ ስለዚህ ለሴት ልጆች እና ለወጣት ሴቶች ጎጂ አይደለም የሚለው የተሳሳተ አመለካከት እውነት አይደለም” ብለዋል።

“እያንዳንዱ ዶክተር በተለየ መንገድ ነው የሚሰራው እና ለዚያም ነው የተለያዩ ችግሮች ተከስተው የምናየው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካትሪን እና ዶ/ር አዋድ ለጤና ባለሙያዎች ግርዛቱን እንዲያከናውኑ ዋናው ማበረታቻ ገንዘብ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ የሆነ ባህላዊ እና ማኅበረሰባዊ አመለካከትመሆኑን ያምናሉ።

ዶ/ር አዋድ የሴት ልጅ ግርዛት በተከበሩ የማኅበረሰቡ አባላት፣ በሕክምና ባለሙያዎች መፈጸሙ ሕጋዊ ያስመስለዋል በሚለው የዓለም ጤና ድርጅት አቋም ይስማማሉ።

“በሕክምና ባለሙያዎች የሚፈጸም የሴት ልጅ ግርዛት በጣም አደገኛ የሆነው የሚቆረጠው ጥልቅ መሆኑ ብቻ አይደለም። . . . ጉዳቱ የሚመጣው እነዚህ ሴቶች ዶክተሮችን ስለሚያምኑ በትክክል ይሰራሉ ​​ወይም ያነሰ ጉዳት ነው ብለው ስለሚያምኑ ጭምር ነው።’ እውነታው ግን ያ አይደለም።

“የሴት ልጅ ግርዛትን እንዴት ማከናወን እንደሚቻል ምንም ዓይነት ስልጠና የለም፤ ስለዚህ ሁሉም ሐኪም በዘፈቀደ ነው የሚያከናውነው “

ካትሪን የአገሯ ሴቶች ተስፋ እንዳላቸው ታምናለች።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚፈጸምባቸው አንዳንድ አካባቢዎች ቢኖሩም፣ አዝጋሚ ቢሆንም ቀስ በቀስ ለውጥ እያየች ነው።

ዩኒሴፍ በኬንያ ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ዕድሜያቸው ከ15 እስከ 19 ዓመት በሆናቸው ልጃገረዶች መካከል የሴት ልጅ ግርዛት ከ26 በመቶ ወደ 9 በመቶ፣ ከግማሽ በላይ ቀንሷል ብሏል።