
ከ 4 ሰአት በፊት
የትራምፕ አስተዳደር ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ያገደ ሲሆን ይህም ከአሜሪካ አንጋፋው ዩኒቨርስቲ ጋር ያለውን አለመግባባት አባብሶታል።
የአገር ውስጥ ደህንነት መስርያ ቤት ኃላፊ ክሪስቲ ኖኤም በኤክስ ገጻቸው ላይ እንደጻፉት አስተዳደሩ ሀርቫርድ “ተማሪዎች እና ስደተኛ ያልሆኑ ተማሪዎችን መቀበል የሚያስችለውን ዕድል (Student and Exchange Visitor Program certification) ሕግን ማክበር ባለመቻሉ ምክንያት ተሰርዟል” ብለዋል።
“ይህ በመላው አገሪቱ ለሚገኙ ሁሉም ዩኒቨርስቲዎች እና የትምህርት ተቋማት እንደ ማስጠንቀቅያ ይሁናቸው” ሲሉ ሐሙስ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ልጥፍ ላይ ጽፈዋል።
ሀርቫርድ ውሳኔውን “ሕገ ወጥ” ሲል በመግለጫው አውግዞታል።
“ከ140 በላይ አገራት የመጡ እና ዩኒቨርሲቲውን እና ይህችን አገር በማይተመን መልኩ የሚያበለጽጉትን ዓለም አቀፍ ተማሪዎቻችንን እና ምሁራኖቻችንን ለማስተናገድ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኞች ነን” ሲል ዩኒቨርሲቲው በመግለጫው ላይ ምላሽ ሰጥቷል።
“ለዩኒቨርስቲ ማኅበረሰቡ አባላት መመሪያ እና ድጋፍ ለመስጠት በፍጥነት እየሰራን ነው።ይህ አጸፋዊ እርምጃ በሀርቫርድ ማኅበረሰብ እና በአገራችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል እንዲሁም የሀርቫርድ የአካዳሚክ እና የምርምር ተልእኮውን ያዳክማል።”
የትራምፕ አስተዳደር ውሳኔ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ሊጎዳ ይችላል።
ባለፈው የትምህርት ዘመን ከ6,700 በላይ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች በተቋሙ ተመዝግበው እንደነበር የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያሳያል።
ይህም ዩኒቨርስቲው ካሉት የተማሪዎች ብዛት መካከል 27 በመቶውን ይሸፍናል።
ሐሙስ ዕለት ዜናው በዩኒቨርስቲው ውስጥ በሚገኙ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ በፍጥነት ተሰራጭቷል፤ ይህም የወደፊት እጣ ፈንታቸው በድንገት ቅርቃር ውስጥ ለገባው በሺዎች በሚቆጠሩ ተማሪዎች ዘንድ ፍርሃት እና ብስጭት ፈጥሯል።
በዩኒቨርስቲው የድህረ ምረቃ ዲግሪ ተማሪ የሆነችው አውስትራሊያዊት ሳራ ዴቪስ፣ “በጉዳዩ ላይ ብዙ ግራ መጋባት ተፈጥሯል” ስትል ለቢቢሲ ኒውስአወር ተናግራለች።
በሀርቫርድ ኬኔዲ ትምህርት ቤት የአውስትራሊያ እና የኒውዚላንድ ተማሪዎች ፕሬዝዳንት የሆነችው ዴቪስ “ዜናው የተሰማው ብዙዎቻችን ለመመረቅ አምስት ቀናት ሲቀረን ነው፤ ይህ በግልጽ አሜሪካ ውስጥ ለመቆየት እና ለመስራት መቻላችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል” ብላለች።
“ሁላችንም ቀጣዩ እርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል ከዩኒቨርሲቲው መረጃ እስኪመጣ ድረስ ዝም ብለን እየጠበቅን ነው።”
ስውዲናዊው ሊዮ ጌርዴን የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪ ሲሆን ሀርቫርድ ዩኒቨርስቲ እንደተቀበለው የሚገልጽ ደብዳቤ የተቀበለበት ቀን በሕይወቱ ምርጥ ቀን መሆኑን ያስታውሳል።
ሊመረቅ አንድ ሳምንት ያልሞላ ጊዜ የቀረው ጌርዴን የዩኒቨርስቲ ቆይታው በዚህ መልኩ ይጠናቀቃል ብሎ አላሰበም።
ጌርዴን “በዋይት ሐውስ እና በሀርቫርድ መካከል በሚደረገው ጦርነት ዓለም አቀፍ ተማሪዎች እንደ ጠጠር ሆነው እያገለገሉ ነው” ሲል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
“በሚገርም ሁኔታ ሰብዓዊነት የጎደለው ነው” ሲልም አክሏል።
አስተዳደሩ በመላው አገሪት በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ምርመራ ማድረግ ጀምሯል።
በሚያዝያ ወር የትራምፕ አስተዳደር ለሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ማድረግ ያለባቸው ነገሮች ዝርዝር ቢሰጥም ዩኒቨርስቲው አልፈቀደም።
ዩኒቨርስቲው የትራምፕ አስተዳደር ጥያቄን ተቃውሞ ክስ እንደሚመሰርት ማስታወቁን ተከትሎ ነገሮች ተካርረዋል።
ዋይት ሐውስ ለሀርቫርድ የተላኩት ዝርዝሮች በስህተት ነው ብሏል።
የትራምፕ አስተዳደር ለዩኒቨርስቲው መሟላት አለበት ብሎ የላካቸው ዝርዝሮች በግቢው ውስጥ ፀረ ሴማዊነት ለመዋጋት እንዲረዳው ሃርቫርድ የቅጥር፣ የቅበላ እና የማስተማር አሰራሩን እንዲቀይር ይጠይቃል።
ዩኒቨርሲቲው የተጠየቀውን ለማሟላት አሻፈረኝ በማለቱ ከቀረጥ ነፃ ተጠቃሚነቱን እንደሚሰረዝ ማስጠንቀቅያ የደረሰው ሲሆን የሚያገኘው 2.2 ቢሊዮን ዶላር ድጎማና 60 ሚሊዮን ዶላር የኮንትራት ገንዘብ ተቋርጧል።
ትራምፕ ወደ 256 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን የሀርቫርድን ድጎማ እና በየዓመቱ የሚመደበውን 8.7 ቢሊዮን ዶላር በድጋሚ እንደሚያጤኑ መግለጻቸው ይታወሳል።
ሀርቫርድ ከፌደራል መንግሥቱ በጀት ለማግኘት እንዲችል ከዋይት ሀውስ ከተሰጡት 10 ማሻሻያዎች መካከል አንደኛው ለአሜሪካ “አደገኛ” የሆኑ ተማሪዎችን መጠቆም ነው።
“ፀረ ሴማዊነትን የሚያባብሱ” የተባሉ የትምህርት ክፍሎችን አሠራር በገለልተኛ ባለሙያዎች ማስፈተሽም ይገኝበታል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተቃውሞ ያደረጉ ተማሪዎችን መቅጣትም ተካቷል።
ሀርቫርድ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ፀረ ሴማዊነት ለመቅረፍ ብዙ እርምጃዎችን ወስጃለሁ ያለ ሲሆን፣ ከመንግሥት የቀረቡት ጥያቄዎች የዩኒቨርሲቲውን “ምሁራዊ ነጻነት” ለመቆጣጠር የተደረገ ጥረት ነው ሲል ኮንኖታል።
ግጭቱ ተባብሶ ቀጥሏል።
በሚያዝያ ወር ኃላፊዋ አስተዳደሩ ዩኒቨርስቲው እንዲያቀርብ የጠየቀውን የዓለም አቀፍ ተማሪዎች ዝርዝር የማያቀርብ ከሆነ ዩኒቨርስቲው ለተማሪዎች የተሰጠውን የቪዛ ፕሮግራም ዕድል እንደሚሰረዝ አስጠንቅቀው ነበር።
በሐሙስ ደብዳቤ ላይ ኖኤም ሀርቫርድ የዓለም አቀፍ ተማሪዎችን የመቀበል “ዕድሉን” መልሶ ለማግኘት የተጠየቀውን ማሟላት አለበት ብለዋል።
ይህም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀርቫርድ የተመዘገቡ ስደተኛ ያልሆኑ ተማሪዎች የሥነ ምግባር ጥሰት የተመዘገበበት መዝገብ መስጠትን ይጨምራል።
በተጨማሪም ኖኤም በግቢው ውስጥ በ”ሕገወጥ” እና “አደገኛ ወይም አመጽ” ላይ የተሳተፉ ስደተኛ ያልሆኑ ተማሪዎችን የኤሌክትሮኒክስ መዝገቦችን፣ ቪዲዮዎችን ወይም ድምጾችን እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
ደብዳቤው ሀርቫርድ የተጠየቀውን እንዲፈጽም 72 ሰዓታት ሰጥቷል።
ኖኤም በኤክስ ገጻቸው ላይ በለጠፉት ጽሑፍ እርምጃው “በአገሪቱ ውስጥ ላሉት ዩኒቨርስቲዎች እና የትምህርት ተቋማት ሁሉ እንደ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ሊያገለግል ይገባል” በማለት አስጠንቅቀዋል።
የትራምፕ አስተዳደር ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች የሚሰጥ ቪዛን ለመገደብ ሞክሯል።
ይህ ውሳኔ በአሜሪካ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ ግራ መጋባትን የፈጠረ ሲሆን ወደ ክስ ያመሩም አሉ።
በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ ክልከላው በፖለቲካ ተቃውሞ ውስጥ የተሳተፉትን ወይም መኪና ሲያሽከረክሩ ጥፋት የፈጸሙ የውጭ ተማሪዎችን ሁሉ የሚመለከት ይመስላል።
ሐሙስ ዕለት በነበረ ሌላ የፍርድ ቤት ክስ በካሊፎርኒያ የሚገኝ የፌደራል ዳኛ የትራምፕ አስተዳደር በመላው አሜሪካ የሚገኙ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ሕጋዊ ሁኔታ እንዳይሰርዝ አግዶታል።
አስተዳደሩ ባስቀመጠው ፖሊሲ ላይ በፍርድ ቤት ክሶች እና እገዳዎች እየገጠሙት ነው።
“እዚህ የመጣንበት ምክንያት አሜሪካ የቆመችለት የመናገር ነፃነት፣ የአካዳሚክ ነፃነት፣ የነቃ ምሁራዊ ማኅበረሰብ መፍጠር ስለሆነ ነው” ሲል ጌርደን ለዓለም አቀፍ ተማሪዎች ጓደኞቹ ተናግሯል።
“አሁን ደግሞ ትራምፕ እነዚህን ሁሉ እሴቶች አደጋ ላይ ለመጣል እያስፈራሩ ነው፤ ያለ ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሀርቫርድ በቀላሉ ሃርቫርድ አይሆነም” ብሏል።
ከዚህ ቀደም የኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ 400 ሚሊዮን ዶላር የፌደራል ፈንድ መቋረጡ አይዘነጋም።
ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ብዙም ሳይቆይ ዋይት ሀውስ ያቀረባቸውን የማሻሻያ ሐሳቦች ለመተግበር ተስማምቷል።