
ከ 4 ሰአት በፊት
ዴንማርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ2040 ጀምሮ ጡረታ የመውጫ ዕድሜን ወደ 70 ከፍ አደረገች።
ይህ በአውሮፓ ትልቁ ነው የተባለው ጡረታ የመውጫ ዕድሜ በትናንትናው ዕለት በአገሪቱ ፓርላማ ጸድቋል።
ዴንማርክ ከ2006 ጀምሮ ይፋዊ ጡረታ የመውጫ ዕድሜን ከዕድሜ ጣርያ (life expectancy) ጋር አቻ ያደረገች ሲሆን፣ በየአምስት ዓመቱ ስትከልስ ቆይታለች።
በአሁኑ ጊዜ ጡረታ የመውጫ ዕድሜ 67 ሲሆን፣ በ2030 ወደ 68 እና በ2035 ወደ 69 ከፍ ይላል።
ሐሙስ ዕለት ምክር ቤቱ ያጸደቀው አዲሱ ሕግ 81 አባላቱ ሲደግፉት 21 ደግሞ ድምጻቸውን ነፍገውታል።
ይኹን እንጂ ባለፈው ዓመት የሶሻል ዲሞክራቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን ይህ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ድርድር ሊደረግበት እንደሚችል ተናግረዋል።
“ወድያውኑ የጡረታ መውጫ ዕድሜ መጨመር አለበት ብለን አናምንም” ያለችው ጠቅላይ ሚኒስትሯ በፓርቲዋ ዕይታ መሰረት “ሰዎች ዕድሜያቸው በጨመረ ቁጥር መስራት አለባቸው ብለን አንናገርም።” ብላለች።
የ47 ዓመቱ ቶማስ ጄንሰን ለዳኒሽ ሚዲያ በሰጠው ቃለ ምልልስ የተደረገውን ለውጥ “ምክንያት የለሽ” ሲል ጠርቶታል።
“እየሰራን ነው፤ እናም መስራት፣ መስራት፣ መስራት ብቻ ይሆናል። በዚህ መልኩ ልንቀጥል አንችልም” ብሏል።
በቢሮ ተቀምጠው ለሚሰሩ ሁኔታው የተለየ ሊሆን ይችላል ያለው ጄንሰን፣ ነገር ግን አካላዊ ጉልበት በሚጠይቅ ስራ ላይ ለተሰማሩ ለውጡ ፈታኝ ይሆናል ብሏል።
ጄንሰን አክሎም “የሚጠበቅብኝን ግብር በሕይወት ዘመኔ ሁሉ ስከፍል ቆይቻለሁ። ከልጆቼ እና ከልጅ ልጆቼ ጋር የማሳልፍበት ጊዜ ሊኖረኝ ይገባል” ሲል ተናግሯል።
ባለፈው ሳምንታት የጡረታ ዕድሜ መጨመሩን በመቃወም በንግድ ማኅበራት የተደገፉ ሠልፎች በኮፐንሀገን ተካሂደዋል።
ሐሙስ ዕለት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕጉ ከመጽደቁ በፊት የዳኒሽ ንግድ ሕብረት ኮንፌዴሬሽን ሊቀ መንበር ጄስፐር ኢትሩፕ ራስሙሰን፣ የጡረታ ዕድሜን ለመጨመር የቀረበው ምክረ ሃሳብ “ፍፁም ኢፍትሀዊ ነው” ብለው ነበር።
“ዴንማርክ ጤናማ ኢኮኖሚ ነው ያላት፤ በተቃራኒው ግን ከአውሮፓ አገራት ሁሉ ከፍተኛው የጡረታ መውጫ ዕድሜም የሚገኘው እዚሁ ነው” ብለዋል።
“ከፍተኛ የጡረታ መውጫ ዕድሜ ማለት ሰዎች ለተከበረ የእርጅና ጊዜ የሚኖራቸውን መብት ያሳጣል።”
በአውሮፓ ጡረታ የመውጫ ዕድሜ የተለያየ ነው።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መንግሥታት ረዥም ከዕድሜ ጣርያ ከግምት በማስገባት ያለባቸውን የበጀት ጉድለት ለመከላከል ሲሉ የጡረታ መውጫ ዕድሜን አስተካክለዋል።
በስውዲን ሰዎች ጡረታቸውን ማግኘት የሚችሉበት ትንሹ ዕድሜ 63 ነው።
ልክ እንደ ዴንማርክ ሁሉ በጣሊያንም የጡረታ መውጫ ዕድሜ 67 ሲሆን፣ ይህም በሕይወት የመኖር ዕድሜን ከግምት ገብቶ ሲሆን በ2026 ሊጨምር ይችላል ተብሏል።
በዩናይትድ ኪንግደም ከጥቅምት 6 /1954 እና በሚያዝያ 5/1960 መካከል የተወለዱ ጡረታቸውን መቀበል የሚችሉት በ66 ዓመታቸው ነው።
ነገር ግን ከዚህ በኋላ የተወለዱ ሰዎች የጡረታ ዕድሜ ቀስ በቀስ እየጨመረ ሊሄድ ይችላል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2023 ፈረንሳይ ባጸደቀችው እና ከፍተኛ ተቃውሞ በቀሰቀሰው ሕግ መሰረት የጡረታ መውጫ ዕድሜ ከ62 ወደ 64 ከፍ ብሏል።