
ከ 4 ሰአት በፊት
ዶናልድ ትራምፕ “ጎልደን ዶም” የተሰኘው የሚሳዔል መከላከያ ሥርዓታቸው የፕሬዝዳንታዊ ዘመናቸው ከማብቃቱ በፊት “ሙሉ በሙሉ” ተግባራዊ” እንደሚሆን አሳውቀዋል።
በቅድሚያ 25 ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ ለማድረግ ቃል የገቡት ፕሬዝዳንቱ አጠቃላይ ወጪው ወደ 175 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚሆን ገምተዋል። ነገርግን አንዳንድ ባለሥልጣናት አጠቃላይ ወጪው ቢያንስ ሦስት እጥፍ ያህል ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
ዕቅዶቹ በመሬት፣ በባሕር እና በሕዋ ላይ ያሉ የ”ቀጣዩ ትውልድ” የቴክኖሎጂ መረብን፣ እንዲሁም አጥቂ ሚሳዔሎችን ለመከላከል ያለመ ሕዋ ላይ የተመሠረቱ አክሻፊ እና ጠቋሚዎች (ሴንሰር) ያካትታሉ።
“ጎልደን ዶም” እንደ ሩሲያ እና ቻይና ካሉ ሀገራት እየጨመረ ከሚመጣ የአየር ላይ አደጋዎች አሜሪካንን ለመከላከል በነባር ሥርዓቶች ላይ ይገነባል።
ጎልደን ዶም እንዴት ይሠራል?
የትራምፕ ዕቅድ በከፊል የመነጨው የአጭር ርቀት የሚሳዔል ስጋትን ለመጥለፍ የራዳር መከላከያ ዘዴዎችን በሚጠቀመው እና ከአውሮፓውያኑ 2011 ጀምሮ ጥቅም ላይ የዋለው የእስራኤል ‘አይረ ዶም’ ነው።
“ጎልደን ዶም” ግን ብዙ እጥፍ ይበልጣል እና ሰፋ ያለ ስጋትን ለመዋጋት የተነደፈ ይሆናል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶች ሊኖሩ የሚችሉ አውታረ መረቦችን ይጠቀማል፤ ይህ ቀደም ሲል ኪስ ሊያራቁት ይችል የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ዛሬ የበለጠ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል።
“ሮናልድ ሬጋን ከብዙ ዓመታት በፊት ፈልገው ነበር፤ ነገር ግን ቴክኖሎጂው አልነበራቸውም” ሲሉ ትራምፕ በሕዋ ላይ የተመሠረተውን ሚሳዔል መከላከያ ዘዴን በመጥቀስ ታዋቂው “ስታር ዋርስ” ተብሎ የሚጠራውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት በ1980ዎቹ ያቀረቡትን ሀሳብ ተናግረዋል።
ጎልደን ዶም “ከሌላኛው የዓለም ክፍል የተወነጨፉትን ወይም ከጠፈር የሚተኮሱ ሚሳዔሎችን እንኳን የመጥለፍ አቅም አለው” ሲሉ ትራምፕ አክለዋል።
የሚገነባው ከክሩዝ እና ባሊስቲክ ሚሳኤሎች (ሃይፐርሶኒክ የጦር መሳሪያዎች – ከድምጽ ፍጥነት በላይ የሚንቀሳቀሱትን ጨምሮ) እና ክፍልፋይ የምሕዋር የቦምብ ጥቃት ሥርዓቶች መከላከል እንዲችል ተደርጎ ነው።
ጡረተኛው የአሜሪካ የሳይበር እና ቴክኖሎጂ ፈጠራ ማዕከል ከፍተኛ ዳይሬክተር ሪር አድሚራል ማርክ ሞንትጎመሪ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ጎልደን ዶም “በሦስት ወይም በአራት የቡድን ሳተላይቶች ስብስብ እስከ መቶዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶች” እንደሚተማመን ተናግረዋል ።
ለኒውስዴይ ፕሮግራም እንደተናገሩት “ሚሳዔሎችን የሚለዩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሳተላይቶች አሉ። ከዚያም በርካታ የሚከታተሉ እና የእሳቱን የሚቆጣጠሩም አሉ። ከዚያም ኬኔቲክ መሳሪያዎችን የሚይዙ ወይም የሚተኮሰውን ማንኛውንም ነገር [የጠላት ሚሳዔሎችን] ለመጣል የሚውሉ ሳተላይቶች አሉ።”
“ጎልደን ዶም” በሦስት ዓመታት ውስጥ ሊገነባ ይችላል?

የ’ዘ ኢኮኖሚስት’ የመከላከያ አርታኢ ሻሻንክ ጆሺ የአሜሪካን ሠራዊት ዕቅዱን በቁም ነገር እንደሚከታተሉት፤ ነገር ግን በትራምፕ የሥልጣን ዘመን ይጠናቀቃል ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ መሆኑን እና ይህ ትልቅ ወጪ ከአሜሪካን የመከላከያ በጀት ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስድ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የቀድሞው አድሚራል ሞንትጎመሪም በዚህ ይስማማሉ።
“ይህን ተልዕኮ በቅጡ ለማጠናቀቅ ከአምስት እስከ ሰባት ምናልባትም 10 ዓመት የሚፈጅ ሊሆን ይችላል። በሦስት ዓመታት ውስጥ የበለጠ አስተማማኝ እንድንሆን የሚያደርጉን ነገሮች ይኖሩ ይሆን?” ብለዋል።
ነገር ግን “100 በመቶ ደኅንነቱ የተጠበቀ ሥርዓት” አሁን ባለው የፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ ሊተገበር አይችልም።
ለኮንግሬስ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ትንተና የመስጠት ኃላፊነት የተሰጠው የአሜሪካ መንግሥት ኮንግረስ የበጀት ጽህፈት ቤት፤ ወጭው በ20 ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሕዋ ላይ በተመሠረቱ የሥርዓቱ ክፍሎች ላይ ወደ 542 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ጠቁሟል።
“ጎልደን ዶም”ን ማን ይገነባዋል?
በብዙ ቢሊዮን ዶላር የ”ጎልደን ዶም”ን ፕሮጀክት ለመምራት የታጨው ሰው የዩናይትድ ስቴትስ የጠፈር ኃይል ጄነራል ማይክል ጉትሊን ነው።
ከታኅሣሥ 2023 ጀምሮ “የሚሳዔል ማስጠንቀቂያ፣ የጠፈር አካባቢ ግንዛቤ፣ አቀማመጥ፣ አሰሳ እና ጊዜ አቆጣጠር፣ የመገናኛ እና የጠፈር ኤሌክትሮኒክስ ጦርነት” በሚሰጠው የአሜሪካ ጦር ቅርንጫፍ የጠፈር ኃይል ውስጥ የሕዋ ኦፕሬሽን ምክትል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።
በፕሬዝዳንት ትራምፕ “በጣም ጎበዝ ሰው” በማለት የተገለፁት ባለ አራት ኮከብ ጄነራሉ ጉትሊን ቀደም ሲል የጠፈር ሥርዓት ኮማንድ መሪ እና የርቀት ዳሳሽ ሥርዓቶች ዳይሬክተር በመሆን ከፍተኛ የጠፈር እና የሚሳዔል ልምድ አላቸ።
በዩናይትድ ስቴትስ ኦክላሆማ ግዛት ተወልደው ያደጉት ጉትሊን በ1991 ከኦክላሆማ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው የዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይልን ተቀላቅለዋል።
ሩሲያ እና ቻይና ስለ “ጎልደን ዶም” ምን ያስባሉ?
“ጎልደን ዶም” በዋነኝነት የታሰበው በሩሲያ እና በቻይና የሚወነጨፉ ሚሳዔሎች ለመከላከል ነው።
በመከላከያ የደኅንነት ኤጀንሲ በቅርቡ ይፋ የተደረገው ሰነድ፣ የሚሳኤል ስጋት “በመጠን እና በተራቀቀ መልኩ እንደሚሰፋ” ገልጿል፤ ሁለቱም ሀገራት በአሜሪካ መከላከያ ውስጥ ያለውን “ክፍተቶች ለመጠቀም” በንቃት እየነደፉ ነው ተብሏል።
ቻይና እና ሩሲያ ሁለቱም ጽንሰ-ሐሳቡን “ጥልቅ አለመረጋጋት የሚፈጥር” ሲሉ ተችተውታል።
አዲሱ የመከላከያ ሥርዓት “በሕዋ ላይ የውጊያዎችን ለማካሄድ ጦሩን ጉልህ በሆነ መልኩ ማጠናከርን በግልፅ ያቀርባል” ይላል በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሩሲያ እና በቻይና መካከል ከተደረገው ንግግር በኋላ የወጣው የክሬምሊን መግለጫ።
ይሁን እንጂ የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በቅርቡ ዕቅዱን ለአሜሪካ “የሉዓላዊነት ጉዳይ” ሲሉ ገልፀው፤ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ድርድር እንደገና እንደሚጀመር ጠቁመዋል።
ቻይና በበኩሏ ዕቅዱ የውጪውን የሕዋ ክፍል ወታደራዊ ኃይል በማጎልበት እና የጦር መሳሪያ እሽቅድምድም አደጋ ላይ በመጣል የዓለም አቀፍ ደኅንነትን አደጋ ላይ ይጥላል ስትል ተናግራለች።
ጎልደን ዶም “በውጫዊው የሕዋ ክፍል ላይ ከፍተኛ የሆነ የጦርነት አቅም እንዲጨምር በግልፅ ሃሳብ ያቀርባል…እና በውጭ ሕዋ ስምምነት ከተደነገገው ሰላማዊ አጠቃቀም በተቃራኒ በተፈጥሮ ውስጥ በጣም አስቀያሚ የሆኑ ገጽታዎች አሉት” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ረቡዕ ዕለት ተናግረው አሜሪካ ዕቅዱን እንድትተው አሳስበዋል።
ካናዳ “ጎልደን ዶም” ሥርዓትን ትቀላቀላለች?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕቅዳቸውን በጽህፈት ቤታቸው ሲያስታውቁ ካናዳ የሥርዓቱ አካል ለመሆን ጠይቃለች ብለዋል።
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ እርሳቸው እና ሚኒስትሮቹ ከአሜሪካ አቻዎቻቸው ጋር ስለ አዲስ የፀጥታ እና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት እየተወያዩ መሆናቸውን ገልጿል።
“እነዚህ ውይይቶች በተፈጥሯቸው የሰሜን አሜሪካ የአየር እና ሕዋ መከላከያ ዕዝ እንዲሁም እንደ “ጎልደን ዶም” የመሳሰሉ ተያያዥ ውጥኖችን ማጠናከር ያካትታሉ” ሲል አክሏል።
በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ዋሽንግተንን በጎበኙበት ወቅት የካናዳው የመከላከያ ሚኒስትር ቢል ብሌየር አገራቸው በዶም ፕሮጀክት ላይ የመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት በመግለጽ “ትርጉም ያለው” እና የሀገሪቱ “ብሔራዊ ጥቅም” ነው ሲሉ ተናግረዋል።