
ከ 3 ሰአት በፊት
በሱዳን በቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት ባለፈው ዓመት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) ላይ የኬሚካል ጦር መሳሪያ ተጠቅማለች በማለት አዲስ ማዕቀብ እንደምትጥል የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አስታወቀ።
ከሰኔ 6 ጀምሮ አሜሪካ ወደ አገሪቱ የምትልካቸው ምርቶች እንደሚገደቡ እና የፋይናንስ ብድር ገደቦች ተግባራዊ ይሆናሉ ሲሉ ቃል አቀባዩ ታሚ ብሩስ ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም የሱዳን ጦር እና የፈጥኖ ደራሽ አማፂያኑ በግጭቱ ወቅት የጦር ወንጀሎችን ፈጽመዋል በሚል ተከሰው ነበር።
አሜሪካ ለወሰደችው እርምጃ ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ የሱዳንን ባለስልጣናት ቢጠይቅም እስካሁን መግለጫ አለማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከሁለት ዓመት በፊት የሱዳን ጦር እና አርኤስኤፍ መካከል በተፈጠር የስልጣን ሽኩቻ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ባለፉት ወራት የሱዳን ጦር ዋና ከተማዋ ካርቱምን ቢቆጣጠርም ውጊያው አሁንም እንደቀጠለ ነው።
አሜሪካ የትኛውን የኬሚካል ጦር መሳሪያ አገኘሁ እንዳለች የተገለጸ ነገር የለም።
ሱዳን ብዙ ጉዳት፣ ስቃይ እና አለፍ ሲልም ሊገድል የሚችለውን ክሎሪን ጋዝ ለሁለት ጊዜያት ተጠቅማለች ሲል ኒውዮርክ ታይምስ በጥር ወር ዘግቧል።
“የሱዳን መንግሥት ሁሉንም የኬሚካል ጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም እንዲያቆም እና የዓለም አቀፍ መርህ ስር ያሉትን ግዴታዎች እንዲወጣ ዩናይትድ ስቴትስ ትጠይቃለች” ብሏል በመግለጫው።
በዓለም አቀፉ የኬሚካል ጦር ስምምነት መሠረት ፈራሚ አገራት የያዙትን የጦር መሳሪያ ክምችት ለማስወገድ ቃል ገብተዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ መቀመጫውን እንዳደረገው አርምስ ኮንትሮል አሶሴሽን ከሆነ ስምምነቱን ከግብጽ፣ ከሰሜን ኮሪያ እና ከደቡብ ሱዳን በስተቀር ሱዳንን ጨምሮ ሁሉም አገራት ፈርመዋል።
እስራኤል ስምምነቱን ብትፈርምም ግን ፊርማዋን አላጸደቀችውም። ይህም ማለት በስምምነቱ ውስጥ መግባቷን በሕጋዊ መንገድ አላረጋገጠችም ሲል ተቋሙ ገልጿል።
ብሩስ አክለውም “ዩናይትድ ስቴትስ ለኬሚካል ጦር መሳሪያ መስፋፋት አስተዋፅኦ የሚያደርጉትን ተጠያቂ ለማድረግ ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ነች።”
አሜሪካ በሱዳን ላይ ማዕቀብ ስትጥል ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። በጥር ወር በግጭቱ ውስጥ በተሳተፉት የሁለቱም ወገን መሪዎች ላይ ማዕቀብ ጥላለች።
የሱዳኑ ወታደራዊ መሪ አብዱልፈታህ አል ቡርሃን “ሱዳንን በማተራመስ እና የዲሞክራሲ ሽግግር ግብን ማፍረስ” የሚል ክስ የቀርበባቸው ቢሆንም የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር “እንግዳ እና አሳሳቢ” ሲል አውግዞታል።
የአርኤስኤፍ መሪው መሃመድ ሃምዳን ዳግሎ (ሄሜቲ) በአገሪቱ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንዲፈጸም ቆርጠዋል ሲሉ በቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተከሰዋል።
ሁለቱም ወገኖች ላለፉት ሁለት ዓመታት ስልጣን ለመቆጣጠር ሲፋለሙ ቆይተዋል።
በዚህም የተነሳ ወደ 12 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ሲፈናቀሉ እና 25 ሚሊዮን ሕዝብ ደግሞ የምግብ እርዳታ ጠባቂ ሆኗል።
በቀደምት እርምጃዎች ምክንያት አዳዲስ ማዕቀቦች በአገሪቱ ላይ ብዙም ተጽዕኖ አይኖራቸውም ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።
የአሁኑ የአሜሪካ እርምጃ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች በግጭቱ ውስጥ በመሳተፏ ዙሪያ ውጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እና ሱዳን እስከዚህ ወር መጀመሪያ ድረስ ዲፕሎማሲያው ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም የሱዳን መንግሥት የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ለአርኤፍኤፍ የጦር መሳሪያ ሰጥታለች በማለት ከሷል።
የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ውንጀላ አልተቀበችውም።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ባለፈው ሳምንት በባህረ ሰላጤዋ አገር ያደረጉትን ደማቅ ጉብኝትን ተከትሎ በኮንግረስ የሚገኙ ዲሞክራቶች፤ አሜሪካ ለተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለመሸጥ ያቀደችውን የጦር መሳሪያ በከፊል ለማገድ ሞክረዋል።
ምክንያት ያሉት ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት በግጭቱ ውስጥ እጇ አለበት በሚል ነው።
የሱዳን የዲፕሎማቲክ ምንጭ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ከሆነ አሜሪካ አዲሱን ማዕቀብ የጣለችው “በቅርቡ በኮንግረስ ውስጥ በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ የተካሄደውን ዘመቻ አቅጣጫ ለማስቀየር” ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሱዳን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ላይ ያቀረበችውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ክስ ውድቅ አድርጎታል።