በአፍሪካ የሚገኙ ሁለት የወባ ትንኞች በእጅ ላይ አርፈው

ከ 5 ሰአት በፊት

የወባ ትንኞች በሽታውን እንዳያስፋፉ እንዲሁም ጥገኛ ተህዋስያኑን (ፓራሳይት) በውስጣቸው ለመግደል የወባ መድኃኒት ሊሰጣቸው እንደሚገባ የአሜሪካ ተመራማሪዎች ገለፁ።

ይህ ዘዴ በቤተ ሙከራ ውስጥ በተካሄደበት ፍተሻ ውጤታማ መሆኑ የተረጋገጠ ሲሆን፣ በቀጣይ ደግሞ በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ ሙከራ ለማድረግ ዕቅድ ተይዟል።

በየዓመቱ 600 ሺህ ያህል ሰዎችን የሚገድለው የወባ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው ፓራሳይት ተሸካሚ እና አስተላላፊ በሆነች ሴት አኖፌሌስ በተሰኘች ትንኝ ሲነከሱ ነው።

የአኖፌሌስ ትንኝ ብቻ ከ400 ዘር በላይ ያሉ ሲሆን፣ ከእነሱ መካከል 30ዎቹ ብቻ ናቸው ወባ የሚያስተላልፉት።

በአሁኑ ወቅት የወባ ትንኝን ከበሽታ አምጪው ፓራሳይቱ ከማዳን ይልቅ በፀረ ተባይ ለማጥፋት ጥረት ይደረጋል።

የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎች በወባ ትንኟ እግር ገብተው በሽታ አምጪውን ፓራሳይት የሚገድሉ ሁለት መድኃኒቶች አግኝተዋል።

ይህንንም ለማድረግ የወባ መከላከያ አጎበርን ለረዥም ጊዜ በመድኃኒቶቹ ለመንከር ዕቅድ ተይዟል።

የወባ ትንኝ የምትናደፈው በምሽት በመሆኑ መከላከል ውጤታማ ከሆኑት መንገዶች መካከል አንዱ አልጋን በአጎበር ሸፍኖ መተኛት ነው።

ለወባ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕጻናትን ለመከላከል ክትባት መስጠት ይመከራል።

አጎበር የወባ ትንኟ እንዳትናደፍ መከላከያ ብቻ ሳይሆን ፀረ ተባይ የተነከረ በመሆኑ ስታርፍበት ይገድላታል።

ይሁን አንጂ የወባ ትንኞች ፀረ ተባይን የመቋቋም ችሎታ በማዳበራቸው አጎበሩ የተነከረው መድኃኒት በሚፈለገው መጠን አይገድላቸውም።

ምርምሩን ካካሄዱት ሳይንቲስቶች መካከል የሆኑት ዶ/ር አሌክሳንድራ ፕሮብስት “ከዚህ በፊት ፓራሳይቱን የወባ ትንኟ ውስጥ እያለ ለመግደል ጥረት አላደረግንም። ምክንያቱም የወባ ትንኟን መግደል ላይ ነበር ያተኮርነው።”

ይሁን እንጂ ይህ መንገድ “የሚፈለገውን ያህል ውጤታማ እያደረገን አይደለም” ብለዋል።

ተመራማሪዎቹ የወባ ትንኟ የምትሸከመው ፓራሳይት ዘረ መልን በመመርመር ደካማ ቀዳዳ ለማግኘት የሚችሉበትን መንገድ ፈትሸዋል።

ከዚያ በኋላም ይከላከላሉ ተብሎ የታመነባቸውን በርካታ መድኃኒቶች በመውሰድ 22ቱን መምረጥ ችለዋል።

በመቀጠልም ሴቷ የወባ ትንኝ ፓራሳይት ያለበት ደም በምትመገብበት ወቅት መድኃኒቱ ተሰጥቷታል።

ተመራማሪዎቹ በኔቸር መጽሔት ላይ በታተመው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ እንዳስቀመጡት ሁለት መድኃኒቶች ፓራሳይቱን ሙሉ በሙሉ ገድለዋል።

እነዚህ መድኃኒቶች በአጎበር ላይም ፍተሻ ተደርጎባቸዋል።

“የወባ ትንኟ አጎበሩ ላይ በምታርፍበት ወቅት ባትሞት እንኳ ፓራሳይቱ በውስጧ ይሞታል፤ ስለዚህ ወባ ማስተላለፍ አትችልም ማለት ነው” ብለዋል ዶ/ር ፕሮብስት።

“ይህ በጣም አስደናቂ አቀራረብ ይመስለኛል፤ ምክንያቱም ይህ ራሳቸው የወባ ትንኞችን ዒላማ የምናደርግበት አዲስ መንገድ ነው።”

ተመራማሪዋ በእያንዳንዱ በወባ በተያዘ ሰው ውስጥ የወባ ፓራሳይቶች በቢሊዮኞች እንደሚገኙ ገልፀው፣ በእያንዳንዱ ወባ ትንኝ ውስጥ ግን ከአምስት በታች በመሆናቸው መድኃኒት የመቋቋም አቅማቸው በጣም ደካማ ነው ብለዋል።

መድኃኒቱ በአጎበር ላይ ዓመት ያህል የሚቆይ ሲሆን፣ ከዋጋ እንዲሁም ከፀረ ተባይ አንጻር ርካሽ እና ረዥም ጊዜ የሚቆይ አማራጭ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል።

ይህ መከላከያ መንገድ በላብራቶሪ ተፈትሾ ውጤታማ መሆኑ ተረጋግጧል።

ቀጣዩ ዕቅድ በሌላው ዓለም አጎበሩ እንደሚከላከል ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ፍተሻ ለማድረግ ነው።

ይህ አካሄድ ውጤታማ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ የሚደረጉ ጥናቶችን ለማጠናቀቅ ቢያንስ ስድስት ዓመታት ይወስዳል።

ነገር ግን ዕቅዱ አጎበሮች በሁለቱም ፀረ ወባ መድኃኒቶች እና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች እንዲታከሙ ነው።

ይህም አንዱ አቀራረብ ካልሠራ ሌላኛው እንዲሠራ ያስችለዋል።

ዓለም አቀፍ የጤና ድርጅት መድኃኒት በተረጩ አጎበሮች ሥር መተኛት ከቢምቢዎቹ ጋር ያለውን ግንኙነት ስለሚቀንስ በጣም ውጤማ መሆኑን ይናገራል።

ከአጎበሩ በተጨማሪ ደግሞ የመኖሪያ ስፍራዎችን መድኃኒት መርጨትም ጠቃሚ እና አንደኛው የመከላከያ መንገድ መሆኑን ይናገራል።

በተለያየ ጊዜ መድኃኒቱን ከመርጨት ባሻገር ለሚጓዙ ሰዎች የሚዋጡ መድኃኒቶችን መውሰዱም በጣም ጠቃሚ የሆነ የወባ መከላከያ መንገድ እንደሆነ ይገለፃል።