
ከ 59 ደቂቃዎች በፊት
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ የፌደራል መንግሥት “በራሱ ሕዝብ ላይ” የሚፈጽማቸውን የድሮን ጥቃቶች “በአፋጣኝ እንዲያቆም” ጥሪ አቀረቡ።
አምባሳደሩ፤ የፋኖ ኃይሎች “ተጨባጭ እና ሰላማዊ ዓላማዎችን” እንዲይዙ፤ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ደግሞ “ድርድሮችን እንዲቀጥል” ጠይቀዋል።
ማክሰኞ ዕለት ወደ ትግራይ ክልል ተጉዘው በሽረ ከተማ ከክልሉ አመራሮች ጋር የተወያዩት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህንን ጥሪ ያቀረቡት ዛሬ አርብ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. በኤምባሲው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በወጣ መልዕክታቸው ነው።
በሀገሪቱ ያሉ ግጭቶችን ማቆምን የተመለከተው የአምባሳደሩ መልዕክት፤ ኢትዮጵያ “በቀጠሉ ግጭቶች ውስጥ ወደ ሌላ ዓመት” እየተሻገረች መሆኑን ይገልጻል።
እነዚህ ግጭቶች “በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖ መለስ ብሎ ማሰብ አስፈላጊ” እንደሆነ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
“ሕዝቡን ለማስቀደም ጊዜው አሁን ነው” ያሉት አምባሳደር ማሲንጋ፤ ይህንን ለማድረግም “ለኢትዮጵያ ውስጣዊ ግጭቶች ዘላቂ መፍትሄ መተግበር” እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
“የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቤታቸውን እንዲመለሱ ማድረግ” እንዲሁም “ሕጻናት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ” ማድረግም አስፈላጊ እርምጃዎች እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
አምባሳደሩ “የትጥቅ ትግል አካል እንደሆነ በማስመሰል [የተንሰራፋውን] ሕገ የለሽነት እንዲያበቃ ማድረግም” አምባሳደሩ “ሕዝብን ለማስቀደም” መተግበር አለባቸው ካሏቸው እርምጃዎች መካከል ነው።
አምባሳደር ማሲንጋ በዛሬው መልዕክታቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች በትጥቅ ትግል ላይ ላሉት የፋኖ ኃይሎች እና የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥሪ አቅርበዋል።
ለፋኖ ኃይሎች ባሰፈሩት መልዕክት፤ “ዩናይትድ ስቴትስ ፋኖ ከተጨባጭ እና ሰላማዊ ዓላማዎች ጋር ወደፊት እንዲመጣ ጥሪ ታቀርባለች” ብለዋል።
ቀጥለውም፤ “በኦሮሚያ የሚካሄደውን ግጭትን ለማቆም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ድርድሮችን እንዲቀጥል ጥሪ እናቀርባለን” ሲሉ ለሌላኛው ታጣቂ ቡድን መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ ያቀረቡት ሌላኛው ጥሪ የፌደራል መንግስትን የሚመለከት ነው። ለመንግሥት ባለስተላለፉት መልዕክት የሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀዋል።
አምባሳደሩ፤ “የፌደራል መንግሥት በአፋጣኝ በራሱ ሕዝብ ላይ ድሮን መጠቀም እንዲያቆም እና ስምምነትን እንዲያመቻች እንጠይቃለን” ብለዋል። “ሰላም እና መረጋጋትን ለመምረጥ ጊዜው [አሁን] ነው” በማለትም መልዕክታቸው ቋጭተዋል።
ይዘቱን X ይፈቅዳሉ?
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።Accept and continue
ማሳሰቢያ: በሌሎች ገጾች ላይ ላሉ ይዘቶች ቢቢሲ ኃላፊነት አይወስድም።
የ X ይዘት መጨረሻ
በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማሲንጋ ጥቃቶች እንዲያቆሙ ጥሪ ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም። ባለፈው ዓመት በዚሁ ግንቦት ወር የቀድሞው አሜሪካ ቆንስላ ግቢ (አሜሪካ ግቢ) ውስጥ ባደረጉት ጠንከር ያለ ንግግር፤ መሠረተ ልማቶችን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶች እንዲቆሙ ጠይቀው ነበር።
ማሲንጋ፤ “ሽፍቶች፣ ታጣቂ ቡድኖች እና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በሕይወት የመኖር እና የመከባበር መብቶች ላይ ጥሰት መፈፀማቸው የሕግ ሂደትን እና የሕግ የበላይነት አለማክበርን የሚያሳይ ነው” ሲሉም በመንግሥት እና ታጣቂዎች ላይ ጠንካራ ትችት አቅርበዋል።
ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲኖር እና ለዚህም መነሻ የሚሆን ጊዜያዊ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም አንዲደረግም በዚህ ንግግራቸው ጠይቀው ነበር። አምባሳደሩ በተመሳሳይ ለፋኖ ኃይሎች እና ለኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ምክር አዘል ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
አምባሳደር ማሲንጋ በወቅቱ ያቀረቡት ወቀሳ ግን ከመንግሥት በኩል ጠንካራ ምላሽን አስከትሎ ነበር። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአምባሳደሩን ንግግር ተከትሎ ባወጣው መግለጫ፤ ማሲንጋ “ያልተጠየቁትን ምክር” ሰጥተዋል በማለት ወቅሶ ነበር።
የአምባሳደሩን ንግግርም “በደንብ ያልተጤነ” እና “ብልሃት የሚጎድለው” ሲል ተችቷል። አምባሳደር ማሲንጋ “ሳይጠየቁ” ለኢትዮጵያ መንግሥት ምክር ለመለገስ ሞክረዋል ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ “ያልተገባ ክስ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቀርቧል” ሲልም የአምባሳደሩን ወቀሳ አጣጥሏል።
የመንግሥት ኃይሎች በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ቡድኖች ጋር በሚያደርጉት ግጭት በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት እየደረሰ ከመሆኑ በተጨማሪ የሕዝብ መደበኛ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጓጎለ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ከእነዚሁ ግጭቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጸሙ የድሮን ጥቃቶች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን መንግሥታዊው የሰብአዊ መብት ኮሚሽንን ጨምሮ ሌሎች ሪፖርቶች ማመልከታቸው ይታወሳል።