የሕክምና ባለሙያ [ከጀርባ የሩዋንዳ ባንዲራ]

29 ሚያዚያ 2024

ተሻሽሏል ከ 5 ሰአት በፊት

ሩዋንዳ በጤና መስክ እጅግ ስኬታማ ጉዞ እያደረጉ ያሉ አገራት ብሎ የዓለም ጤና ድርጅት ከመሰከረላቸው መካከል አንዷ ናት።

“የሺህ ተራራዎች ምድር” ተብላ የምትጠራው ትንሽዬዋ የምሥራቅ አፍሪካ አገር የሕዝብ ቁጥር ከ15 ሚሊዮን ባይልቅም በጤናው ዘርፍ ግንባር ቀደም ከሚባሉት ተርታ ተመድባለች።

የዓለም ኢኮኖሚክ ፎረም መረጃ እንደሚጠቁመው 90 በመቶ ሕዝቧ የጤና ኢንሹራንስ ሽፋን አለው። ኤችአይቪ በደማቸው ካለ ሰዎች 90 በመቶው የመድኃኒት አቅርቦት አላቸው። 93 በመቶ ሕፃናት ደግሞ ተላላፊ በሽታዎችን ለመግታት ክትባት ወስደዋል።

በአውሮፓውያኑ 2000 የሩዋንዳውያን አማካይ የዕድሜ ጣሪያዋ 48 ነበር፤ አሁን ግን ይህ ቁጥር ከ67 በላይ ሆኗል።

እርግጥ ነው ሩዋንዳ አሁንም በምጣኔ ሀብት የዳበረች የምትባል አይደለችም። ነገር ግን ከ2000 እስከ 2015 ባለው ጊዜ በድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎችን ቁጥር ከ40 በመቶ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ማድረግ ችላለች።

የሩዋንዳ መንግሥት በጤና ዘርፍ ማሳካት የሚፈልገው ትልቁ ግብ የጤና አገልግሎትን ለሁሉም ማዳረስ ነው። ለዚህ ግብ መሳካት ደግሞ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረጉ ይመስላል።

ለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ሩዋንዳን የሚመርጡት ለምንድን ነው? እንዴትስ ነው ወደ ሩዋንዳ የሚያቀኑት?

ሩዋንዳ ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሕክምና ባለሙያዎች በጥቂቱ

ጉምቱ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች በሩዋንዳ

ዶክተር የቆየሰው በለጠ ነዋሪነታቸውን በሩዋንዳ ሲሆን፣ በክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሺየቲቭ የሄልዝ ሲስተምስ ዳይሬክተር ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

“በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ቦትስዋና በሚፈልሱበት ወቅት እኔ ተማሪ ነበርኩ” የሚሉት የሕብረተሰብ ጤና (ፐብሊክ ሄልዝ) ባለሙያው አሁን ደግሞ ተራው የሩዋንዳ እንደሆነ ይናገራሉ።

እሳቸው እንደሚሉት መጀመሪያ አንድ ሰው ወደ አዲስ አገር በሕክምና ሙያ ካቀና በኋላ ዕድሉ እንዳለ ለሙያ አጋሮቹ ያሳውቃል፤ ይሄኔ ነው ሐኪሞች ወደ ውጭ መውጣት የሚጀምሩት።

የፐብሊክ ሄልዝ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር የቆየሰው፣ በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ከማገልገላቸውም በላይ ከሩዋንዳ በተጨማሪ ዛምቢያ ውስጥም ሠርተዋል።

የጤና ባለሙያው እንደሚሉት አብዛኞቹ ሩዋንዳ ያሉ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ‘ሰብ-ስፔሻሊስቶች’ ናቸው።

“ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ሐኪም በውስጥ ደዌ አሊያም በማህጸን ወይም በሕፃናት ሕክምና ስፔሻላይዝ ያደርጋል። ከዚያ በኋላ ለምሳሌ በውስጥ ደዌ ሕክምና የልብ ስፔሻሊስት ሊሆን ይችላል። እንግዲህ ምን ያክል ትልልቅ ባለሙያዎች እንደሆኑ ያሳየናል ማለት ነው።”

ዶክተር የቆየሰው እንደሚሉት ምንም እንኳ የሩዋንዳው ትልቁ ኪንግ ፋይሳል ሆስፒታል ዋነኛው የኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ቀጣሪ ቢሆንም፤ በሌሎች ሆስፒታሎች ውስጥም ኢትዮጵያውያን ሐኪሞች ይሠራሉ።

አክለው ኢትዮጵያውያን ሆስፒታሉን ከማስተዳደር ጀምሮ አንዳንዶቹ በስፔሻሊስት ሌሎቹ ደግሞ በሰብ-ስፔሻሊስት ደረጃ በማገልገል ላይ ይገኛሉ።https://flo.uri.sh/visualisation/23366223/embed?auto=1

ዶክተር ዘሪሁን አበበ የኪንግ ፋይሳል ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሲሆኑ፣ ዶክተር ሃና አበራ ደግሞ የጋስትሮኢንትሮሎጂ ክፍል ኃላፊ ናቸው።

ዶክተር የቆየለት እንደሚሉት ቢያንስ ከ20 አስከ 30 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ዶክተሮች ሩዋንዳ ውስጥ ያገለግላሉ።

የነርሶች እና የአንስቴዢያ ባለሙያዎች ቁጥር ግን እምብዛም አይደለም። ለሁለት እና ሦስት ወራት ወደ ሩዋንዳ መጥተው፤ በሙያቸው ሠርተው፤ ልምዳቸውን አካፍለው የሚሄዱ ባለሙያዎችም አሉ።

ፐብሊክ ሄልዝን ጨምሮ በሌሎች መስኮች በተለያዩ ትምህርት ቤቶች የሚያስተምሩ ከ10 እስከ 15 የሚሆኑ ስፔሻሊስቶችም እንዳሉ ዶክተሩ ይናገራሉ።

“ኢትዮጵያ በቁጥርም በዓይነትም በጣም ብዙ የሕክምና ባለሙያዎችን ስላሰጠነች እነዚህ ባለሙያዎች መጥተው እየሠሩም እያሠለጡንም ነው ያሉት። እኛ የፐብሊክ ሄልዝ ባሙያዎች ደግሞ ስትራቴጂ የማውጣት እና የማማከር ሥራ እንሠራለን።”

ምክንያቱ ምንድን ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት ቢያንስ አራት የሕክምና ባለሙያዎች ለአንድ ሺህ ሰው መድረስ አለበት የሚለውን ስትራቴጂ ካወጣ በኋላ የሩዋንዳ መንግሥት በአራት ዓመት ውስጥ ይህን ለማሳካት እየተጋ ይገኛል።

የሩዋንዳ የጤና ሚኒስትር እና ዴኤታቸው ይህን ዕቅዳ ለማሳካት እየሠሩ መሆናቸውን የሚናገሩት የፐብሊክ ሄልዝ ስፔሻሊስቱ፤ አገሪቱ እየሠሩ የሚያስተምሩ የሕክምና ባለሙያዎችን ትፈልጋለች ይላሉ።

“አንደኛው ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ወደ እዚህ እየመጡ ያሉበት ምክንያት ሩዋንዳ ያወጣችው ስትራቴጂ የሥራ ዕድል መፍጠሩ ነው። አገሪቱ ያወጣችውን መስፈርት የሚያሟሉ በርካታ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ።”

ነገር ግን ይላሉ ለበርካታ ዓመታት በፐበሊክ ሄልዝ ሙያ ያገለገሉት ዶክተር የቆየሰው፤ “ነገር ግን መሠረታዊው ምክንያት ግን ሌላ ነው” በማለት የክፍያ ጉዳይን ያነሳሉ።

“ኢትዮጵያ ለሕክምና ባለሙያዎች እጅግ ዝቅተኛ ገንዘብ ከሚከፍሉ የዓለማችን አገራት መካከል ናት። ያለው ሁኔታ ብዙዎች ከአገራቸው ወጥተው ያለውን ዕድል እንዲሞክሩ የሚያደርግ ነው።”

ዶክተር የቆየሰው ሌላኛው ምክንያት የሚሉት ደግሞ “ሙያን ለማሳደግ የሚደረግ እንቅስቃሴ” ነው። ይህን ለማስረዳት የራሳቸውን ልምድ በምሳሌ ያነሳሉ።

“እኔ ብጠየቅ የግሎባል ሄልዝ ስፔሻሊስት ነው መሆን የምፈልገው። ማንኛውም ባለሙያ ሙያውን ዓለም አቀፍ በሚባል ደረጃ ማሳደግ ይፈልጋል። ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ወደ አፍሪካ አገራት ሄደው ሠርተው ራሳቸውን ያሳድጋሉ፤ በግሎባል ሄልዝ ላይ አሻራቸውን ማሳረፍ ይፈልጋሉ። ፍልሰቱ ከችግር ብቻ ነው የሚመነጨው ብሎ ማሰብም ተገቢ አይደለም” ይላሉ።https://flo.uri.sh/visualisation/23366296/embed?auto=1

በአንድ ወቅት የጤና ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ውጭ ተጉዘው እንዳያገለግሉ ያወጣውን መመሪያ የሚያነሱት ዶክተር የቆየሰው “አስረን ልናስቀረው የሞከርንበት ጊዜም ነበር፤ ግን አይጠቅምም” በማለት ማንኛውም ባለሙያ ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብቱ ሊጠበቅለት ይገባል ባይ ናቸው።

የሩዋንዳ መንግሥት ጤናን ለሁሉም ለማዳረስ ያወጣውን ስትራቴጂ ለማሳካት ይረዳው ዘንድ ከዓለም አቀፍ ተቋማት እና የተራድዖ ድርጅቶች ጋር እየሠራ ይገኛል።

የዓለም የጤና ድርጅት፣ ዩኤስኤአይዲ እና ክሊንተን ሄልዝ አክሰስ ኢኒሺዬትቭን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ከሩዋንዳ መንግሥት ጋር ይሠራሉ።

ከኢትዮጵያ እና ከሌሎች አገራት የሚመጡ የሕክምና ባለሙያዎች በእነዚህ ድርጅቶች አማካይነት ይመጣሉ የሚሉት ዶክተር የቆየሰው “ጥሩ ጥቅማጥቅም፣ ጥሩ ደመወዝ እና መልካም የሥራ ሁኔታ አመቻችተው ነው ወደዚህ አገር የሚያስመጡት” ሲሉም ያስረዳሉ።

“እኛ [ኢትዮጵያ] በስትራቴጂ ብዙ ባንታማም ስትራቴጂዎችን ለማሳካት የሚሆን የተመቻቸ የሥራ ሁኔታ በመፍጠር ላይ ግን ብዙ ይቀረናል። የጤና ባለሙያው በትክክል ሥራውን እንዲሠራ የማያስችሉ ብዙ ተግዳሮቶች አሉ።”

እሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ወደ ውጭ አገራት ተጉዘው ልምድ መቅሰማቸው የሚጠቅም እንጂ የሚጎዳ አይደለም።

“የጤና ባለሙያዎች አምርተናል፤ ሐኪሞቹ አገር ውስጥ አገልግለዋል፤ ሌሎችን ዕድሎችንም እንዲያዩ ማድረግ ለአገሪቱ ጠቃሚ ነው ብዬ አስባለሁ። አንድ ወቅት ላይ ሁሉም ሰው ወደ አገሩ ይመለሳል። ወደ አገራቸው የተመለሱ የጤና ባለሙያዎች እየሠሩ ያሉትን ነገር ስንመለከት በጣም የሚያኮራ ነው።”

ዶክተር የቆየሰው እና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን
የምስሉ መግለጫ,ዶክተር የቆየሰው እና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ቢል ክሊንተን

ከሩዋንዳ ምን እንማር?

ከ30 ዓመታት በፊት አስከፊ በሚባል የእርስ በርስ ጦርነት እና ድህነት ስትታመስ የነበረችው ሩዋንዳ አሁን በጤና እና በቱሪዝም እንዲሁም በሌሎች መስኮች በአፍሪካ ምሳሌ ተብላ የምትጠቀስ ሆናለች።

የዓለም ጤና ድርጅት በአውሮፓውያኑ 2018 ባወጣው ሪፖርት ከ1994 የሩዋንዳ ዘር ጭፍጨፋ (ጄኖሳይድ) በኋላ ባሉት 20 ዓመታት የዜጎቿ አማካይ ዕድሜ በእጥፍ አድጓል።

ሪፖርቱ አክሎም በሩዋንዳ የጤና አገልግሎት ከመሻሻሉም በላይ የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ከፍ ብሏል፤ የእናቶች እና የሕፃናት ሞት ቁጥር ደግሞ አሽቆልቁሏል ይላል።

ዶክተር የቆየሰው እንደሚሉት ሩዋንዳ በጤናው ዘርፍ ተጠቃሽ አገር ለመሆን የቻለችው “ግልፅ ስትራቴጂ እና ተጠያቂነት” ስላለ ነው።

“አንድ አገር፤ አንድ የጤና ፖሊሲ፤ አንድ ስትራቴጂ አላቸው። እሱን ተከትለው ነው የሚሠሩት” ይላሉ።

“አንድ ሰው በጤና ሚኒስቴር በኩል ወደ ሥልጣን ሲመጣ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ለመወጣት ነው። ኃላፊነቱን ካልተወጣ አይቆይም። ይህ እጅግ በጣም ከሚያስቀኑኝ ነገሮች አንዱ ነው።”

በኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር ዳይሬክተር ጄነራል ሆነው ያገለገሉት ዶክተር የቆየሰው፤ በኢትዮጵያ ምንም እንኳ “ስትራቴጂው ቢኖረንም” ተግባራዊ ማድረጉ ላይ ደካማ ነው ይላሉ።

እሳቸው በጤና ሚኒስቴር እየሠሩ ሳለ የሆነውን አውስተው ችግሩ ያለው ከፖሊስ ሳይሆን ከትግበራ መሆኑን ያስረዳሉ።

“በአንድ ወቅት ብዙ ሐኪሞች በዓለም ጤና ድርጅት መስፈርት እናሠልጥን ተባለ፤ ሠለጠኑ። ግን ሥራ አልነበራቸውም። በወቅቱ በርካታ የጤና ባለሙያዎች ለተቃውሞ ወጥተው ነበር። ክልሎች ናቸው ሐኪም መቅጠር የሚችሉት። ፌዴራል መንግሥቱ መቅጠር የሚችለው ለሆስፒታሎች እና ለፌዴራል ተቋማት ብቻ ነው። ነገር ግን የጤና ሚኒስቴር ያወጣው ስትራቴጂ ጥሩ ሆኖ ቀጣሪው ግን የፈለገውን የማድረግ መብት አለው።”

ዶክተሩ ሌላኛው በሩዋንዳ ቆይታቸው ያስቀናቸው ጉዳይ ያለው ሰላም እና ደኅንነት መሆኑን ይናገራሉ። በተለይ የጤና ባለሙያዎች ሰላማዊ የሥራም ሆነ የመኖሪያ ሥፍራ ያስፈልጋቸዋል የሚል እምነት አላቸው።

አክለውም ሩዋንዳውያን ለንጽህና ያላቸው አመለካከት ሌላኛው “ነቅለው ወደ ኢትዮጵያ ቢወስዱት” የሚመኙት ነገር ነው። ምክንያቱም ንጽህና ለጤናውም መስክ አስተዋፅዖ አለውና ይላሉ።

ኪጋሊ በየወሩ በሦስተኛው ቅዳሜ “ኡሙጋንዳ”ን ታከብራለች። ይህ ቀን ሁሉም ሰው ወጥቶ አካባቢውን የሚያጸዳበት ቀን ነው። በየወሩ በአራተኛው እሑድ ደግሞ “ካር ፍሪ ደይ” ነው። እስከ ጥዋቱ 5፡00 ድረስ መኪኖች መንገድ ላይ አይታዩም።

“እርግጥ እኛ አገር በተለያዩ ጊዜያት ብልጭ ብሎ አይተነዋል። እዚህ ግን ቀልድ የለም፤ ሁሉም ያከብረዋል” ይላሉ።

“ሩዋንዳ ችግር የሌለባት፤ ሁሉ ነገር የተስተካከለባት አገር ነች” እያሉ እንዳልሆነ የሚናገሩት ዶክተር የቆየሰው፤ ነገር ግን ችግሮቻቸውን ለይተው እየሠሩበት ነው። ለዚህም ኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች የውጭ አገር ባለሙያዎች መጥተው እየሠሩ ነው።

እሳቸው እንደሚሉት ሩዋንዳውያን ለኢትዮጵያውያን የሕክምና ባለሙያዎች የሚሰጡት ቦታ ደግሞ ከፍ ያለ ነው።

“ታድያ ጉምቱ የሕክምና ባለሙያ ሆነህ የምትናገረውን የሚያደምጥ፤ የምትጽፈውን የሚያነብ ከሌለ፤ እንዲህ ዓይነት ለሥራ ምቹ የሆነ አገር እንዴት አትመጣ?

“እኛ አገር ያለው ‘ሲስተም’ ሥነ ልቦናዊ ተፅዕኖ ያሳድራል፤ ደኅንነት አይሰማም፤ ሙስናው እና የአሠራር ብልሹነት እንዲሁም ቢሮክራሲው፤ የሚባክነው ጊዜ፣ ጉልበት፣ ገንዘብ ጨለምተኛ እንደትሆን ያደርጋል።”

———-

ማስታወሻ፡ ይህ ዘገባ በድጋሚ የቀረበ ነው።