የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ እና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

ከ 2 ሰአት በፊት

ዶናልድ ትራምፕ ረቡዕ ዕለት በዋይት ሐውስ ከፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ ጋር ተፋጥጠው ነበር።

በደቡብ አፍሪካ በነጭ ገበሬዎች ላይ ግድያ ተፈጽሟል የሚል ያልተረጋገጠ ጉዳይ በትራምፕ በኩል ቀርቧል።

ውይይቱ ሲጀምር ሞቅ ያለ እና ቀለል ያለ ነበር።

ትራምፕ ሠራተኞቻቸው አንድ ቪዲዮ እንዲያጫወቱ ሲጠይቁ ሁሉም ነገር በፍጥነት ተቀየረ።

በቪዲዮው ላይ የደቡብ አፍሪካው ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ጁሊየስ ማሌማ በነጭ አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ሲዘምሩ ይታያል።

በቪዲዮው በርካታ መስቀሎችም የሚታዩበት ስፍራ አለ።

ትራምፕ ስፍራው የተገደሉ ነጭ ገበሬዎች የቀብር ቦታ ነው ከማለት ባለፈ በደቡብ አፍሪካ አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮች ላይ የሚደርሰውን መጠነ ሰፊ ጭካኔ መዝግበው የያዙ ጽሑፎችንም ለራማፎሳ አቅርበዋል።

የትራምፕ አስተዳደር ደጋፊዎች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ነጮች ላይ ጥቃት ተፈጽሟል የሚለውን ሃሳብ ለረዥም ጊዜ ሲያቀነቅኑ ቆይተዋል።

በተለይም ኤለን መስክ እና የቀድሞ የፎክስ ኒውስ አዘጋጅ ተከር ካርልሰን በፕሬዝዳንቱ የመጀመሪያ የስልጣን ዘመን እስከዘር ማጥፋት መፈጸሙን ጠቅሰዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ሐሰተኛ ናቸው።

የተደረደሩት መስቀሎች የነጭ ገበሬዎች መቃብሮች ናቸው?

ኦቫል ኦፊስ ውስጥ በትራምፕ እንዲታይ በተደረገው ቪዲዮ ላይ በአንድ የገጠር መንገድ ረዥም ርቀት የተዘረጋ የነጭ መስቀሎች ረድፍ ይታያል።

ትራምፕ “እነዚህ የመቃብር ስፍራዎች ናቸው። የመቃብር ቦታዎች ናቸው። ከሺህ በላይ ነጭ ገበሬዎች ናቸው” በማለት ተናግረዋል።

ይኹን እንጂ መስቀሎች መቃብሮችን አያሳዩም። ቪዲዮው እአአ በ2020 በግቢያቸው ውስጥ በጥይት የተገደሉትን አርሶ አደሮቹን ነጭ ጥንዶች፣ ግሌን እና ቪዳ ራፈርቲን ግድያ በመቃወም የተቀረጸ ነው።

ቪዲዮው በዩቲዩብ ላይ በተቃውሞው ማግስት መስከረም 6 ተሰራጭቷል።

ከዝግጅቱ አስተባባሪዎች አንዱ የሆነው ሮብ ሆትሰን “የቀብር ቦታ አይደለም ነገር ግን መታሰቢያ ነበር” ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

መስቀሎቹ የተተከሉት ለጥንዶች “ጊዜያዊ መታሰቢያነት” በሚል ነው ብሏል።

ትራምፕ መስቀሎች በመደዳ ስለተከሉበት ስለዚህ አከካባቢ ተናግረዋል

ሆትሰን አክለውም መስቀሎቹ በኋላ ላይ ተነስተዋል ብለዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ይህ የተፈጸመው በክዋዙሉ-ናታል ግዛት የሚገኘው ኒውካስል አካባቢ መሆኑን አረጋግጧል።

በግንቦት 2023 የተቀረጸው የጎግል ስትሪት ቪው ምስል እንደሚያሳየው ቀረጻው በበይነ መረብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከተለቀቀ ከሦስት ዓመት በኋላ ገደማ መስቀሎቹ በስፍራው እንዳልነበሩ ያሳያል።

በነጭ ገበሬዎች ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል?

በውይይቱ ወቅት ትራምፕ “ብዙ ሰዎች ደቡብ አፍሪካን በተመለከተ ከፍተኛ ስጋት አላቸው… ብዙ ሰዎች ጥቃት ይደርስብናል ብለው ስለሚሰጉ ወደ አሜሪካ እየመጡ ነው። ስለዚህ ጥቃት ወይም የዘር ማጥፋት እየተካሄደ እንዳለ ከተሰማን ከብዙ ቦታዎች እንወስዳለን” ብለዋል።

ከዚህ ቀደም “ነጮች ላይ ስላተኮረ የዘር ማጥፋት ወንጀል” ለበርካታ ጊዜያት በመናገራቸው የአሁኑ ሃሳባቸው ያንን የሚያመለክት ይመስላል።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በደቡብ አፍሪካ የነጭ ገበሬዎችን ግድያ በመጥቀስ “እየተካሄደ ያለው የዘር ማጥፋት ነው” ብለዋል።

ደቡብ አፍሪካ በዓለም ላይ ከፍተኛ ግድያ ከሚፈጸምባቸው መካከል አንዷ ነች።

ባለፈው ዓመት 26 ሺህ 232 ግድያዎች መፈጸማቸውን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ አገልግሎት (ሳፕስ) መረጃ ያሳያል።

44ቱ በአርሶ አደሩ ማኅበረሰብ ውስጥ የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ስምንቱ በገበሬዎች የተገደሉ ናቸው።

እነዚህ አሃዞች ዘርን መሰረት በማድረግ የተከፋፈሉ አይደሉም። በትራምፕ በተደጋጋሚ ለሚሰነዘሩት “ነጮች ላይ ያተኮረ የዘር ማጥፋት” ግልጽ ማስረጃዎች አይሆኑም።

በየካቲት ወር አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ዳኛ የዘር ማጥፋትን ሃሳብ “በግልጽ የታሰበ” እና “እውነተኛ ያልሆነ” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ገበሬዎችን የሚወክለው የትራንስቫል የግብርና ዩኒየን (ቲኤዩ) ስለ ተጎጂዎች የዘር ማንነት ግንዛቤ የሚሰጡ አሃዞችን ያጠናቅራል።

የቲኤዩ አሃዞች በመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ መረጃዎች እና በአባሎቻቸው ሪፖርቶች ላይ የተመሰረተ ነው።

ባለፈው ዓመት ባወጡት መረጃ መሠረት በእርሻ ስፍራ ጥቃት 23 ነጮች እና ዘጠኝ ጥቁሮች ተገድለዋል።

ባለፉት አምስት ወራት ደግሞ በደቡብ አፍሪካ እርሻዎች ሦስት ነጮች እና አራት ጥቁሮች መገደላቸውን ቲኤዩ መዝግቧል።

የደቡብ አፍሪካ ባለስልጣናት በነጭ ገበሬዎች ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ጥሪ አቅርበዋል?

ትራምፕ ውጥረት በበዛበት ስብሰባ ላይ “Kill the Boer (ቦወሮቹን ግደሉ)” ብለውየሚዘምሩበትን የፖለቲካ ሰልፎች ቪዲዮ አጫውተዋል።

ይህ አወዛጋቢ የጸረ-አፓርታይድ ዘፈን ሲሆን ተሳታፊዎች በነጭ ገበሬዎች ላይ ጥቃት እንዲፈጽሙ የሚጠይቅ ነው በሚል ትችት ይቀርብበታል።

የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤቶች ዘፈኑን የጥላቻ ንግግር ብለው ፈርጀውት ነበር።

በቅርቡ ደግሞ ይህ ዘፈን ፖለቲካዊ ዓላማ ያለው እንጂ በቀጥታ ግጭት የሚጋብዝ አይደለም በሚል በሕጋዊ መንገድ በስብሰባዎች ላይ መዝፈን ይቻላል የሚል ውሳኔ አስተላልፈዋል።

ትራምፕ ዘፈኑን የሚመሩት “ባለስልጣናት” እና “በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ናቸው” ብለዋል።

ሰልፉን ሲመሩ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ጁሊየስ ማሌማ ሲሆን ቀደም ሲል የገዢውን ኤኤንሲ ፓርቲ የወጣቶች ክንፍ መሪ ነበር።

እአአ በ 2012 ፓርቲውን ለቅቆ ከወጣ በኋላ አንድም ጊዜ የመንግሥት ሥልጣን ይዞ አያውቅም።

አሁን ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ (ኢኤፍኤፍ) የተሰኘውን ፓርቲ የሚመራ ሲሆን ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ 9.5 በመቶ ድምጽ በማሸነፍ የገዢው የመድበለ ፓርቲ ጥምረት ተቃዋሚ ሆኗል።

ጁሊየስ ማሌማ የገዢውን ኤኤንሲ ፓርቲ ለቅቆ ከወጣ በኋላ ኢኤፍኤፍ የተሰኘውን ፓርቲ አቋቁሟል

ራማፎሳ ለትራምፕ ውንጀላ ምላሽ ሲሰጡ ኢኤፍኤፍ “ትንሽ ፓርቲ” መሆኑን አፅንኦት ሰጥተው “የእኛ የመንግሥት ፖሊሲ እሱ ከሚናገረው ጋር ሙሉ በሙሉ ይቃረናል” ብለዋል።

በቪዲዮው ላይ የሚታዩት እና “ቦየር ላይ ተኩስበት” የሚለውን ግጥም ሲዘፍኑ የሚሰሙት እአአ በ2018 ሥልጣናቸውን የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጃኮብ ዙማ ናቸው።

ቪዲዮው ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት በ2012 የተቀረጸ ነው።

ኤኤንሲ ከዚያ በኋላ ዘፈኑን እንደማይጠቀም ቃል ገብቷል።

ዙማ ከኤኤንሲ ወጥተው ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ ከ14 በመቶ በላይ ያሸነፈውን ኡምኮንቶ ዌሲዝዌ ፓርቲን በመምራት ላይ ይገኛሉ።

የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎሳ እና የአሜሪካው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ

ትራምፕ ምን ዓይነት ሰነዶችን እንደ ማስረጃ አቀረቡ?

በስብሰባው ወቅት በደቡብ አፍሪካ የነጭ ገበሬዎች መገደላቸውን ያረጋግጡልኛል ያሏቸውን ጽሑፎችን ትራምፕ አቅርበዋል።

ትራምፕ ሲናገሩ በግልጽ የሚታይ ምስል ይዘው “ተመልከቱ በሁሉም ቦታ የመቃብር ቦታዎች አሉ። እነዚህ ሁሉ የነጭ ገበሬዎች መቃብሮች ናቸው።”

ምስሉ ግን ከደቡብ አፍሪካ አይደለም። በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ስለተገደሉ ሴቶች ከቀረበ ዘገባ የተወሰደ ነው።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ደግሞ በየካቲት ወር በዲሞክራቲክ ኮንጎ በምተገኘው የጎማ ከተማ ከተቀረጸው የሮይተርስ የዜና ወኪል ቪዲዮ ላይ የተገኘ መሆኑን አረጋግጧል።