
ከ 4 ሰአት በፊት
ሀርቫርድ ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን እንዳይቀበል ዶናልድ ትራምፕ ውሳኔ ቢያሳልፉም ውሳኔው ለጊዜው በፍርድ ቤት ታግዷል።
የትራምፕን ውሳኔ ተከትሎ ሀርቫርድ ክስ ከመሠረተ በኋላ ነው ፍርድ ቤት ክልከላውን ያገደው።
ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ሀርቫርድ እንዳይገቡ ማገድ ሕግና የንግግር ነጻነትን የሚጻረር እንደሆነ ሀርቫርድ ገልጿል።
ሀርቫርድ ፀረ ሴማዊነትን ለማስቆም አልሞከረም በሚል ነው ትራምፕ በዩኒቨርስቲው ላይ ክልከላ የጣሉት።
ዩኒቨርስቲው ይህንን ክስ አጣጥሏል።
ዳኛ አሊሰን ቡሮህስ የትራምፕ ውሳኔ ለጊዜውም ቢሆን እንዲታገድ አድርገዋል።
የአገር ውስጥ ደኅንነት ቢሮ የሀርቫርድን የዓለም አቀፍ ተማሪዎች የመቀበል መብት እንዲነጥቅ ተወስኗል።
ሀርቫርድ ለፍርድ ቤት ባቀረበው ክስ “መንግሥት በአንድ ትእዛዝ ግማሽ ሀርቫርድን ሊያጠፋ ነው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለዩኒቨርስቲው ተልዕኮ ከፍተኛ ሚና አላቸው” ሲል ክልከላውን አጥብቆ ተቃውሟል።
የሀርቫርድ ፕሬዝዳንት አለን ጋርበር “ይሄንን ሕገ ወጥ ድርጊት እንቃወማለን” ብለዋል።
“የማስተማር ነጻነታችንን ለመጋፋት መንግሥት ያደረገውን ሙከራ ባለማስተናገዳችን ነው ይሄ እርምጃ የተወሰደብን። የፌደራል መንግሥት የትምህርት አሰጣጡን፣ ተማሪዎቻችንን እና የትምህርት ክፍሎችን እንዲቆጣጠር አንፈቅድም” ሲሉም አክለዋል።
የዋይት ሀውስ ምክትል ፕሬስ ሴክራተሪ አቢጌል ጃክሰን “ሀርቫርድ ፀረ አሜሪካና ፀረ ሴማዊነት ንቅናቄን ለማቆምና ሽብርን ላለመደገፍ ቁርጠኛ መሆን ቢሆን ኖሮ ይሄ ሁሉ አይፈጠርም ነበር” ብላለች።
“ያልተመረጡት ዳኛ የትራምፕ ውሳኔ ማገድ አይችሉም” በማለትም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጣጥላለች።
በሀርቫርድ የትምህርት ዕድል ያገኙ ተማሪዎች ዕጣ ፈንታቸው ምን እንደሆነ ባለማወቅ ጭንቀት ውስጥ ገብተዋል። ወደ አገራቸው ሊመለሱ እንደሚችሉ በማሰብም ፈርተዋል።
የመንግሥት አስተዳደር ምሩቅ ኮርማክ ሳቬግ ከአየርላንድ ነው ሀርቫርድ የገባው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ለቀጣይ 90 ቀናት አሜሪካ ከቆዩ ወደ አሜሪካ ተመልሰው ዲግሪያቸውን መጨረስ እንደሚችሉ ይናገራል።
ከዩናይትድ ኪንግደም ሀርቫርድን የተቀላቀለው ሮሀን ባቱላ “ተመልሼ ትምህርቴን መጨረስ አልችል ይሆናል ብዬ ፈርቻለሁ” ብሏል።
ተማሪዎቹ ፍርድ ቤት በትራምፕ ውሳኔ ላይ በሰጠው ጊዜያዊ ዕግድ ደስተኛ ቢሆኑም በቀጣይ ምን ይፈጠራል ብለው መስጋታቸው አልቀረም።
በሀርቫርድ 6,800 ዓለም አቀፍ ተማሪዎች ያሉ ሲሆን፣ ከአጠቃላይ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች 27% ናቸው።
አንድ አምስተኛው ከቻይና ሲሆኑ፣ ከካናዳ፣ ከሕንድ፣ ከደቡብ ኮሪያ እና ዩናይትድ ኪንግደምም ተማሪዎች በብዛት ይገኛሉ።
ነሐሴ ላይ ትምህርት ለመጀመር እየተዘጋጀ ያለው ሊዮ አክማን ሀርቫርድ መግባት “ሕልሜ ነበር” ይላል።
“በጣም ጓጉቼ ነበር። ይሄንን ዕድል ከመነጠቅ በላይ የሚያሳዝን ነገር የለም” ብሏል።
ዓለም አቀፍ ተማሪዎችን ሀርቫርድ እንዳይቀበል ማድረግ ከዩኒቨርስቲው በጀት ላይ ከፍተኛውን ድርሻ የሚያስቀር ነው። ዓለም አቀፍ ተማሪዎች የራሳቸውን የትምህርት ወጭ እንዲሸፍኑም የሚያስገድድ ሊሆን ይችላል።
በቀጣይ የትምህርት ዘመን የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርት ብቻ በዓመት 59,320 ዶላር ያስከፍላል። ያለ መንግሥት ድጋፍ የዓመት ጠቅላላ ወጭ (ቤት፣ ክፍያ፣ መጻሕፍት፣ ምግብና የጤና መድኅንን ጨምሮ) 100,000 ዶላር ይደርሳል።
ከሴራ ሊዮን ሀርቫርድ የገባው አይዛክ ባንጉራ ከባለቤቱና ሁለት ልጆቹ ጋር ይኖራል።
“ልጆቼ ወደ አገራችን በግድ ልንመለስ ነው? ብለው እየጠየቁኝ ነው። አሜሪካውያን ችግር ሲገጥማቸው መፍትሔ አያጡም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብሏል።
የአሜሪካ ዕውቅ ዩኒቨርስቲዎችን በተለይም ለፍልስጤም ከተደረጉ የድጋፍ ሰልፎ ጋር በተያያዘ ከትራምፕ አስተዳደር ጋር ውዝግብ ውስጥ ከገቡ ቆይተዋል።
ትራምፕ ዩኒቨርስቲዎቹ እንዲያደርጉ በሚፈልጉት ለውጥ ላይ ተቃውሞ ሲገጥማቸው በጀት እስከመቁረጥ ድረስ በመሄድ ዩኒቨርስቲዎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋል።
ከወራት በፊት የሀርቫርድ 2.2 ቢሊዮን በጀት ላይ ዕግድ መጣላቸው ይታወሳል። ዩኒቨርስቲው ግብር እንዳይከፍል የተሰጠውን መብት እንደሚነጥቁም ዝተዋል።