
ከ 4 ሰአት በፊት
የጃፓን እርሻ ሚኒስትር ሩዝ ገዝቼ አላውቅም፤ ምክንያቱም ደጋፊዎቼ “ብዙ” ስጦታ ይሰጡኛል ብለው ሲያሳውቁ ፈገግታ አጭራለሁ ብለው ጠብቀው ነበር።
ይልቁንም ታኩ ኢቶ ቁጣ ተከተላቸው። ይህም ሥራቸውን በፈቃዳቸው እንዲለቁ በቂ ምክንያት ሆኗል።
ጃፓን በአስርት ዓመታት ውስጥ የመጀመሪያው የኑሮ ውድነት ቀውስ ገጥሟታል። ይህም በተወዳጁ እና ዋነኛው ምግብ ሩዝ ላይ ጫናው አሳርፏል።
ሩዝ በአንድ ዓመት ውስጥ ከእጥፍ በላይ ዋጋው ጨምሯል።
ሚኒስትሩ በአንድ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ላይ ላሰሙት ንግግር ይቅርታ ጠይቀዋል። ነገር ግን የተቃዋሚ ፓርቲዎች የመተማመኛ ድምፅ እንዲያጡ እናደርጋለን በሚል በመዛታቸው ሥራቸውን ለቀዋል።
የካቢኔ አባሉ ከሥልጣን መገፋት ሕዝባዊ ድጋፉ እያሽቆለቆለ ለመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ሼጌሩ ኢሽባ አናሳ መንግሥት ኪሳራ ነው።
ሩዝ በጃፓን ኃይል ያለው መሳሪያ ነው። ከዚህ ቀደም በአገሪቱ የተከሰተ የሩዝ እጥረት የፖለቲካ አለመረጋጋትን ፈጥሯል። በአውሮፓውያኑ 1918 የሩዝ ዋጋ መወደድ መንግሥትን ገልብጧል።
ስለዚህ የሩዝ ዋጋ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኢሽባ መንግሥት ላሽቆለቆለው ሕዝባዊ የድጋፍ ደረጃ ሚና እንዳለው ማወቅ አያስደንቅም።
“ፖለቲከኞች ወደ ገበያዎች በመሄድ አስቤዛቸውን ስለማይገዙ አይረዱትም” ስትል የ31 ዓመቷ ሚሞሪ ሂጉቺ ለቢቢሲ ተናግራለች።
የሰባት ወር ጨቅላ ልጅ ያላት ሂጉቺ ለአራስ ጥሩ ምግብ ወሳኝ እንደሆነ በማንሳት፤ ምግብ በቅርቡ ለምትጀምረው ልጇ ከወዲሁ ስጋት አድሮባታል።
“ጥሩ ምግብ እንድትመገብ እፈልጋለሁ። ስለዚህ የምግብ ዋጋ እየጨመረ ከሄደ እኔ እና ባለቤቴ የምንበላውን የሩዝ መጠን መቀነስ አለብን” ትላለች።
የኢባራኪ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ኩኒዮ ኒሺካዋ ዋጋ ያስከፈለው ስህተት የአቅርቦት እና የፍላጎት ያለመጣጣም ጉዳይ ነው ይላሉ።

ባለሙያው የመንግሥት የተሳሳተ ስሌት የተፈጠረ ቀውስ ነው ብለው ያምናሉ።
በአውሮፓውያኑ እስከ 1995 ድረስ መንግሥት ከግብርና ኅብረት ሥራ ማኅበራት ጋር ተቀራርቦ በመሥራት በአርሶ አደሮች የሚመረተውን የሩዝ መጠን ይቆጣጠር ነበር።
ሕጉ በዚሁ ዓመት ቢሰረዝም አርሶ አደሮች ከፍላጎት በላይ ሩዝ እንዳያመርቱ በሚል የግብርና ሚኒስቴር የፍላጎት ግምቶችን ይፋ ማድረጉን ቀጥሏል።
ነገር ግን ፕሮፌሰር ኒሺካዋ እንደሚሉት በ2023 እና 2024 በፍላጎት ትንበያው ስህተት ተፈጥሯል። ፍላጎቱ 6.8 ሚሊዮን ቶን እንደሆነ ገምተው የነበረ ቢሆንም፤ ትክክለኛው ፍላጎት ግን 7.05 ሚሊዮን ቶን ነበር ብለዋል።
ጃፓንን ለመጎብኘት በሚመጡ ቱሪስቶች እና ከኮቪድ ወረርሽኝ በኋላ ከቤት ውጪ ምግብ የሚመገቡ ሰዎች በመበራከታቸው የሩዝ ፍላጎት ጨምሯል።
አርሶ አደሮችም ሩዝ ማምረት ትርፋማ መሆኑ አብቅቷል እያሉ ነው።
መንግሥት ከሩዝ ውጪ ሌሎች ሰብሎችን ለሚያመርቱ አርሶ አደሮች ይሰጠው የነበረውን የማበረታቻ ገንዘብ ካቆመ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ከዓለም አቀፍ የሩዝ ምርት 30 በመቶውን በሚሸፍነው ደቡብ ምሥራቅ እስያም የሩዝ ዋጋ እያሻቀበ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ እና የአየር ንብረት ጫናዎች የሩዝ እጥረት አስከትለዋል።
በጃፓን ጉዳዩ በጣም አሳሳቢ ከመሆኑ የተነሳ አገሪቱ ከሩብ ክፍለ ዘመን በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከደቡብ ኮሪያ ሩዝ ማስገባት ተገዳለች። ምንም እንኳን ተጠቃሚዎች የአገር ውስጥ ሩዝን ቢመርጡም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሺባ ከዋሽንግተን ጋር የንግድ ስምምነት በቀጠለበት ወቅት መንግሥታቸው ከአሜሪካ የሩዝ ምርት እንደሚያስገባ ፍንጭ ሰጥተዋል።
ነገር ግን እንደ ሂጉቺ ያሉ ሸማቾች አገር በቀል ያልሆነን ሩዝ የመግዛት ፍላጎታቸው እምብዛም ነው።
በአገሪቱ በተከሰተው የሩዝ ምርት እጥረት ምክንያት እጥረቱ እንዳይባባስ በርካታ መደብሮች ደንበኞቻቸው በግለሰብ ወይም በቤተሰብ አንድ እሽግ ሩዝ ብቻ እንዲገዙ ይጠይቃሉ።