የህብረቱ የንግድ ኃላፊ ማሮስ ሴፍኮቪች

ከ 4 ሰአት በፊት

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ 50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል የዛቱበት 27 አባላት ያሉት የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ጋር ያለው የንግድ ግንኙነት “በማስፈራራት ላይ የተመሰረተ” መሆን የለበትም አለ።

የኅብረቱ የንግድ ኃላፊ ማሮስ ሴፍኮቪች እንደሚሉት ከአሜሪካ ጋር ያለው የንግድ ስምምነት “በአክብሮት ” ላይ እንዲመሰረት ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከአውሮፓ ኅብረት ወደ አሜሪካ በሚገቡ ማናቸውም እቃዎች ላይ 50 በመቶ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸውን ተከትሎ ነው ይህ ምላሽ ከኅብረቱ የተሰማው።

“የአውሮፓ ኅብረት ለሁለቱም ወገኖች የሚሰራ ስምምነትን ለማረጋገጥ እየሰራ ነው፤ ቁርጠኛም ነው” ሲሉ የአውሮፓ ብረት የንግድ ኮሚሸነር ማሮስ ሴፍኮቪች ከአሜሪካው የንግድ ተወካይ ጃሚሶን ግሬር እና ከንግድ ጸሐፊ ሐዋርድ ሉትኒክ ጋር ከተወያዩ በኋላ ገልጸዋል።

“የአውሮፓ ኅብረት እና የአሜሪካ ንግድ ግንኙነት ወደር የለሽ ነው። ይህም በጋራ መከባበር መመራት እንጂ በማስፈራሪያ ላይ የተመሰረተ መሆን የለበትም። ጥቅማችንን ለማስጠበቅ ዝግጁ ነን” ሲሉ አክለዋል።

በአውሮፓ ኅብረት እና በአሜሪካ መካከል እየተካሄደ ያለው የንግድ ድርድር መዘግየት ትዕግስት አልባ እንዳደረጋቸው ቀደም ብለው የገለጹት ትራምፕ፤ በተያዘው ዕቅድ መሰረት ከሳምንት በኋላ ታሪፉን እንደሚጥሉ ተናግረዋል።

ትሩዝ በተሰኘ የማኅበራዊ ሚዲያቸው ላይ ትራምፕ “ከአውሮፓ ኅብረት ጋር የምናደርገው ውይይት የትም አይደርስም” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሆኖም ፕሬዚዳንት ትራምፕ በአሜሪካ ውስጥ ለተሰሩ ወይም ለተመረቱ የአውሮፓ ምርቶች ታሪፍ እንደማይጣል አክለዋል።

“ስምምነትን እየጠበቅን አይደለም። ስምምነቱን አዘጋጅተናል” ሲሉ ለጋዜጠኞች የተናገሩት ትራምፕ ይህንን ታሪፍ ሊያዘገየው የሚችለው የአውሮፓ ኩባንያ በአሜሪካ ውስጥ ትልቅ መዋዕለ ንዋይ ለማፍሰስ ከተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ትልቅ የንግድ አጋሮች አንዱ ነው። በአውሮፓውያኑ ባለፈው ዓመት ኅብረቱ 600 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጦችን ወጪ ንግድ ያደረገ ሲሆን 370 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ምርቶችን ደግሞ ከአሜሪካ መግዛቱን የአሜሪካ መንግሥት መረጃዎች ያሳያሉ።

ትራምፕ አገራቸው በአለም አቀፍ ንግድ ላይ ተጠቃሚ አይደለችም እንዲያውም እየተጎዳች ነው ብለው ያምናሉ።

በእርሳቸው አመለካከት ሌሎች አገራት የአሜሪካን ገበያ በርካሽ ዕቃዎች እያጥለቀለቁት ነው፤ ይህም የአገሪቱን ኩባንያዎች የሚጎዳ እንዲሁም ከስራ ውጭ እያደረጋቸው ነው።

ትራምፕ እንደሚሉት እነዚህ አገራት የአሜሪካ ምርቶች በገበያቸው ተወዳዳሪ እንዳይሆኑ የተለያዩ ክልከላዎችን እያስቀመጡ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ትራምፕ እነዚህ ታሪፎችን በመጠቀም የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ጉድለት በማስተካከል የአገሪቱን የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲያብብ እና ስራዎችን ለመፍጠር ተስፋ አድርገዋል።