የሞቱ ሰዎች አስክሬን

ከ 2 ሰአት በፊት

የደቡብ አፍሪካ የወንጀል አኃዝ ‘በነጮች ላይ የዘር ፍጅት’ እየተፈጸመ ነው የሚለውን ውንጀላ መሰረተ ቢስ መሆኑን እንደሚያሳይ የአገሪቱ የፖሊስ ሚኒስትር አስታወቁ።

በጥር እና መጋቢት መካከል በእርሻ ቦታዎች ከተገደሉት ስድስት ሰዎች መካከል አምስቱ ጥቁሮች መሆናቸውን የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ ሚኒስትር ሴንዞ ማኩኑ ገልጸዋል።

በደቡብ አፍሪካ አብዛኛውን የአገሪቱን የእርሻ መሬቶች የሚቆጣጠሩት አናሳ ነጮች ‘የዘር ፍጅት’ ስጋት አለባቸው የሚለው ጉዳይ መሰረተ ቢስ እንደሆነ በብዙዎች ዘንድ ቢታመንም ትራምፕ ከሰሞኑ ጉዳዩን አስተጋብተውታል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ አገራቸው ከአሜሪካ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማሻሻል ዋይት ሃውስ ባቀኑበት በዚህ ሳምንት ፕሬዚዳንት ትራምፕ “በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ ነጭ አርሶ አደሮች እየተገደሉ እንዲሁም እየተሳደዱ ነው” የሚል ክስ አቅርበዋል።

የፖሊስ ሚኒስትሩ የአገሪቱን የወንጀል አኃዝ በማጣቀስ እየተገደሉ ያሉት በእርሻ ስራ ላይ የተሰማሩ ጥቁሮች መሆናቸውን አሳይተዋል።

ሚኒስትሩ በአውሮፓውያኑ ጥቅምት እስከ ታህሳስ ያለውን የወንጀል አኃዝ ዋቢ በማድረግ 12 ያህል ግድያዎች መፈጸማቸውን ጠቅሰው ከእነዚህ ውስጥ 11ዱ ጥቁሮች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አንደኛው ብቻ ነጭ መሆኑንም ተናግረዋል።

የደቡብ አፍሪካ የወንጀል አኃዝ በዘር ሲከፋፈል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሆን ሚኒስትሩ ይህንን ያደረጉት በቅርቡ የሚነሱ የዘር ማጥፋት ውንጀላዎችን ተከትሎ ነው።

“በአገሪቱ በእርሻ ላይ የተፈጸሙ ግድያዎች ታሪክ ሁልጊዜም የተዛባ እና ሚዛናዊ ባልሆነ መንገድ ሪፖርት የሚደረግ ነው ነው” ብለዋል።

በየካቲት ወር አንድ ደቡብ አፍሪካዊ ዳኛ “በነጮች ላይ ዘር ፍጅት ስጋት” አለ የሚለውን ክስ “በምናብ ላይ ያለ”፣ “እውነተኛ ያልሆነ” ሲሉ በአንድ የውርስ የፍርድ ሂደት ላይ ውድቅ አድርገውታል።

ራማፎሳ ወደ ዋይት ሃውስ ያቀኑት ዶናልድ ትራምፕ 60 ለሚሆኑ አፍካነርስ ለተሰኙ ነጮች “ፍትሃዊ ያልሆነ የዘር መድልዎ ሰለባዎች ናቸው” በሚል ጥገኝነት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።

እነዚህ ነጮች በ17ኛው ክፍለ ዘመን ከደች የመጡ ሰፋሪዎች ናቸው።

በቀጥታ በተላለፈው የሁለቱ መሪዎች ውይይት ትራምፕ በነጮች ላይ የዘር ፍጅት እየተፈጸመ ነው የሚለውን ክሳቸውን ለማጠናከር ቪዲዮዎች እና ፎቶዎች አሳይተዋል።

ቢቢሲ ትራምፕ ማስረጃ ብለው ያቀረቡት አብዛኛው ሃሰተኛ መሆኑን ማረጋገጥ ችሏል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ቢሮ ቃል አቀባይ የትራምፕን አስተያየት አውግዘዋል።

“እነዚህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ናቸው። የዘር ማጥፋት ምን እንደሆነ ጥልቅ እውቀት የሌለው ሰው ይህንን ቃል ዝም ብሎ በአጋጣሚ መወርወር የለበትም። በተለይም የደቡብ አፍሪካን ታሪክ ለሚረዳ ይህ በጣም ተገቢ ያልሆነ ነው” ሲሉ ራቪና ሻማዳሲኒ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ደቡብ አፍሪካ ከጨቋኙ አናሳ ነጮች የአፓርታድ ስርዓት ከ30 ዓመታት በፊት ብትላቀቅም አሁንም አብዛኛው የአገሪቱ የእርሻ መሬቶች አነስተኛ በሆኑት ነጮች እንደተያዘ ነው።

በደቡብ አፍሪካ የነጮች ቁጥር 7 በመቶ ብቻ ቢሆንም 72 በመቶ የሚሆነውን የአገሪቱን የእርሻ መሬት ይቆጣጠራሉ።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የመሬት ባለቤትነት በአገሪቱ አከራካሪ እና አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኖ የቆየ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የጸደቀው የመሬት ፖሊሲ ይህንን ኢፍትሃዊነት ለማስተካከል ያለመ ነው ተብሏል።

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በአንዳንድ ሁኔታዎች ከነጭ የመሬት ባለቤቶች ያለ ካሳ መሬት መውረስ የሚያስችል ረቂቅ ሕግ እንዲሆን ፈርመዋል።

ምንም እንኳን ራማፎሳ በአዲሱ ህግ ምንም አይነት መሬት አልተወረሰም ቢሉም፤ ህጉ ከጸደቀ ከቀናት በኋላ ትራምፕ ለአገሪቱ የሚደረገውን በመቶ ሚሊዮኖች ዶላር እርዳታ እንዲቋረጥ አዘዋል።

በተጨማሪም አሜሪካ የደቡብ አፍሪካን አምባሳደር በማባረር የነበረው ውጥረት ወደ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫ እንዲያድግ አድርጎታል።

ደቡብ አፍሪካ እስራኤልን በፍልስጤማውያን ላይ የዘር ጭፍጨፋ እየፈጸመች ነው በሚል በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት የከሰሰቻት ሲሆን ይህም ጉዳይ በጦር መሳሪያ ጭምር እየደገፈቻት ያለችውን አሜሪካን አስቀይሟል።