
ከ 4 ሰአት በፊት
በደቡብ እና በመካከለኛው ሶማሊያ ዳግም የተቀሰቀሰው የአልሸባብ መልሶ ማጥቃት የመንግሥት ሠራዊት ላለፉት 3 ዓመታት በከባድ መስዋዕትነት በቁጥጥሩ ስር ያዋላቸውን ግዛቶች እንዲለቅ በማድረግ በዋና ከተማይቱ ሞቃዲሾ ላይ ከባድ ጥቃት ሊደርስ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱ የደረሰው በፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ መሐሙድ እና በፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸው መካከል የተፈጠረው አለመግባባትን ተከትሎ ለሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ ዓለም አቀፍ ድጋፍ እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንዲሁም በብሔራዊ ጦር ሠራዊት ውስጥ ያለው ደካማ አደረጃጀት በመኖሩ ነው ይላሉ።
የአልሸባብ ጥቃት በየካቲት ወር በከፍተኛ ደረጃ ተጠናክሮ የነበረ ሲሆን፣ ትኩረቱን የዋና ከተማዋ ሞቃዲሾ አጎራባች በሆኑት እና በመካከለኛው ሂራን ክልል አካባቢዎች በሚገኙት የታችኛው እና መካከለኛው ሸበሌ ላይ አድርጎ ነበር።
አልሸባብ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2022 ጀምሮ በመንግሥት ጦር ኃይል ተወስደውበት የነበሩትን በሦስት ክልሎች የሚገኙ በርካታ መንደሮችን እና ከተሞችን በቁጥጥሩ ሥር አውሏል።
እነዚህ በታጣቂዎቹ ቁጥጥር ስር ዳግም የወደቁ ስፍራዎች በሞቃዲሾ እና በሸበሌ ክልል እንዲሁም በተቀረው የአገሪቱ አካባቢዎች ወታደሮችን እና አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ ወሳኝ ናቸው።
የሶማሊያን ጦር የሚደግፉት የአሜሪካ፣ የቱርክ እና የኢትዮጵያ አየር ኃይሎች ተደጋጋሚ የአየር ድብደባዎች ቢያደርጉም አልሸባብ ግን ማንሰራራቱ አልቀረም።
ታጣቂዎቹ ከተሞችን የሚያገናኙ መንገዶችን የቆረጡ ሲሆን፣ የጦር መሳሪያ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ወደ ሞቃዲሾ ለማስገባት የሚያስችሉ ድልድዮችንም በቁጥጥራቸው ሥር አውለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ፕሬዝዳንቱን ያጀቡ መኪኖች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል፤ እንዲሁም በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያሉ ቁልፍ ቦታዎች ላይ ጫና ፈጥረዋል።
ሁኔታውን የበለጠ የሚያወሳስበው ደግሞ መንግሥት ከምንጊዜውም በላይ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑ ነው።
አልሸባብን ለመዋጋት ይረዳል የተባለው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ በገንዘብ እጥረት እና ወሳኝ በሆነ የሽግግር ወቅት ፖለቲካ አለመግባባት ቅርቃር ውስጥ ገብቷል።
ፕሬዝዳንት መሐሙድ ከአምስት አስርት ዓመታት በኋላ በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀጥተኛ ምርጫ እንዲካሄድ መወሰናችውን ተከትሎ ከተቀናቃኞቻቸው ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
ፕሬዝዳንት መሐሙድ በአውሮፓውያኑ መጋቢት 18/2025 ሞቃዲሾ ውስጥ ከአልሸባብ ጋር ውጊያ ወደ ሚካሄድበት አካባቢ ሲጓዙ የአጃቢዎቹ መኪና ላይ የቦምብ ጥቃት ተርፈዋል።
በሚቀጥለው ዓመት ለቀጥታ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደ ሙከራ ሆኖ ያገለግላል ተብሎ የሚጠበቀው የአካባቢ ምክር ቤት ምርጫ በሰኔ መጨረሻ ለማካሄድ ቀጠሮ ተይዟል።
የፕሬዚደንቱ ተቀናቃኞች የዚህ ዕቅድ አዋጭነት ላይ ጥያቄ እያነሱ ባሉበት ወቅት፣ መንግሥት ተጨማሪ ቦታዎችን በአልሸባብ መነጠቅ የሚችልበት ሁኔታ የበለጠ ገዝፎ መታየት ጀምሯል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በፌዴራል መንግሥት እና በክልሎች መካከል ያለው ሥር የሰደደ የሥልጣን ሽኩቻ የሰላም እና የአገር ግንባታ ሂደቱን ማደናቀፍ ቀጥሏል።
መካከለኛው ሸበሌ እና ሂራን
በአልሸባብ ከባድ ጥቃት ከደረሰባቸው አካባቢዎች አንዱ መካከለኛው ሸበሌ ሲሆን፣ እስከ ሚያዝያ 16 ድረስ ለሠራዊቱ ዋና የሎጂስቲክስ ማዕከል ሆና ያገለገለችውን አዳን ያባልን ጨምሮ በርካታ መንደሮችን እንዲሁም ከተሞችን በቁጥጥሩ ስር ማድረግ ችሏል።
የአዳን ያባል በታጣቂዎቹ እጅ መውደቅ ለሠራዊቱ እና ለመንግሥት ቁልፍ ቦታን ከማጣት ባሻገር ተምሳሌታዊ ውድቀት ነበር።
አልሸባብ የመንግሥት ኃይሎች ላይ የውጊያ የበላይነት ባሳየበት ወቅት የአገሪቱ ጦር አዛዥ ጄነራል ኦዶዋ ዩሱፍ ራጌህ እና የወታደራዊ ፍርድ ቤት ኃላፊ ሐሰን አሊ ኑር በከተማዋ ውስጥ ነበሩ ተብሏል።
ከተማዋ በአልሸባብ ቁጥጥር ሥር ከመውደቋ አንድ ወር በፊት ፕሬዝዳንት መሐሙድ በስፍራው የሚገኙ ወታደሮችን አግኝተው ንግግር አድርገው ነበር።
አልሸባብ የጦር አዛዡ ተቀምጠውባት የነበረችን ከተማ በቀላሉ በእጁ ማስገባት መቻሉ ለፕሮፓጋንዳነት ተጠቅሞበታል።
አልሸባብም መካከለኛው ሸበሌን ከሞቃዲሾ እና ከመካከለኛው ሶማሌ ክልሎች ጋር የሚያገናኙትን በርካታ መንገዶችን ቆርጧል። ከእነዚህም መካከል የክልሉን ዋና ከተማ ጁሃር እና የባላድ ከተማን የሚያገናኘውን ዋና መንገድ ይገኙበታል።
ይህ መንገድ ሞቃዲሾን ከመካከለኛው ሸበሌ፣ ሂራን እና ጋልጉዱድ ከሚገኙ በርካታ ከተሞች ጋር ያገናኛል።
አሁን በመንግሥት ቁጥጥር ስር የሚገኙት እንደ ጁሃር እና ማሃዳይ ያሉ ዋና ዋና ከተሞች መንገዶቻቸው በታጣቂ ቡድኑ ቁጥጥር ሥር ወድቆ ስጋት ውስጥ ገብተዋል።
ታጣቂዎቹም ከአደን ያባል በኋላ በክልሉ ውስጥ ለሠራዊቱ በጣም አስፈላጊ የሆነውን ዋርጋዲ መያዙን እየገለፁ ነው።
መንግሥት እና አንዳንድ የግል መገናኛ ብዙኃን የአገሪቱ ጦር አካባቢውን እና ቁልፍ የአየር ማረፊያ ቦታን መልሰው በቁጥጥራቸው ሥር ማዋል ችለዋል ሲሉ ያስተባብላሉ።
በሂራን አልሸባብ ብዙ ቦታዎችን ዳግም በቁጥጥሩ ስር ማዋል ችሏል።
አብዛኞቹ በመጀመሪያ በመንግሥት እና በተባባሪ የጎሳ ታጣቂዎች በ2022 እና 2023 ከእጁ የወጡ ነበሩ።
ክልሉ ከ2022 ጀምሮ በአልሸባብ ላይ የማያቋርጥ ጥቃት የሚሰነዝረው እና የመንግሥት ደጋፊ የሆነው የማአዊስሌ ተዋጊ ቡድን መነሻ ነው።
ታጣቂዎች በአሁኑ ጊዜ ሞቆኮሪን እየከበቡ ሲሆን፣ ግንቦት 18 ከከተማዋ ውጪ ከባድ ጦርነት መካሄዱ ተዘግቧል።
በታጣቂዎች እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ውጊያ እየተካሄደ ባለበት ወቅት መንግሥት ወታደሮቹን ከሞቆኮሪ፣ ኤል ድር እና ማሳጋዋን ጨምሮ ከታላላቅ የጦር ሰፈሮች ለማስወጣት እና እንደገና የማጥቃት ስልት ለመቀየስ እያሰበ መሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እየወጡ ነው።

ታችኛው ሸበሌ እና ሞቃዲሾ
አልሸባብ የጭነት መኪናዎች የሸበሌ ወንዝን አቋርጠው ወደ ሞቃዲሾ ለመግባት እና ለመውጣት የሚጠቀሙባቸውን በታችኛው ሸበሌ አውድግሌ፣ ባሪሬ፣ ሳቢድ እና አኖሌ የሚገኙ ቁልፍ ድልድዮች ተቆጣጥሯል።
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሞቃዲሾ የሚደርሰው ከባድ የአልሸባብ የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት ከቀነሰባቸው ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱ የመንግሥት ኃይሎች ታጣቂዎቹን ከእነዚህ አካባቢዎች በማስወጣታቸው ነበር።
አሁን ግን ቡድኑ መልሶ በቁጥጥር ስር ስላዋላቸው ከተማዋ እንደገና ለጥቃቶች የተጋለጠች ሲሆን፣ ውጤቱም ቀድሞውኑ ሊገመት የሚችል ሆኗል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ግንቦት 18 በሞቃዲሾ፣አልሸባብ በወታደራዊ ካምፕ በሥልጠና ላይ የሚገኙ ወታደሮች ላይ ባነጣጠረው የአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 30 ሠልጣኝ ወታደሮችን መግደሉን እና ሌሎች 50 ማቁሰሉን ተናግሯል።
የግል መገናኛ ብዙኃን 20 ሰዎች መሞታቸውን እና 15 መቁሰላቸውን ዘግበዋል።
ከመጋቢት 15 እስከ ግንቦት 19 ባለው ጊዜ ውስጥ፣ አልሸባብ በሶማሊያ ውስጥ በጣም አስተማማኝ ከሆኑት ስፍራዎች አንዱ እና የውጭ አገር ዲፕሎማቶች፣ የተባበሩት መንግሥታት ቢሮዎች እና የአፍሪካ ኅብረት ወታደራዊ ተልዕኮ መቀመጫ የሆነው የሃላኔን ሕንጻ ቢያንስ አምስት ጊዜ ደብድቧል።
ብዙ የሞርታር ጥቃት የደረሰበት ሃላኔ ከአደን አዴ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አጠገብ ይገኛል።
የሚያዝያ 6ቱ ድብደባን ተከትሎ አንዳንድ በረራዎች ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲመለሱ የተገደዱ ሲሆን፣ በአካባቢው ባሉ ሌሎች ስፍራዎች ላይም ጥቃት በመድረሱ በአየር ማረፊያው የአደጋ ጊዜ ደወል ተሰምቶ ነበር።
በተጨማሪም አልሸባብ በሚያዝያ 28 በሃላኔ ላይ በፈጸመው ጥቃት “ሦስት አሜሪካውያንን” መግደሉን እና ስድስት ጣሊያናውያንን ማቁሰሉን ተናግሯል።
ባለሥልጣናት መገናኛ ብዙኃን ጥቃቱን እንዳይዘግቡት ከልክለዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ፕሬዝዳንቱ መጋቢት 18 በሂራን እና በመካከለኛው ሸበሌ የሚገኙትን ወታደሮች ለመጎብኘት ከሞቃዲሾ ሲወጡ አጃቢዎቻቸው ላይ የቦምብ ጥቃት መፈጸም ችሎ ነበር።
ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ ጉዳት ባይደርስባቸውም ጥቃቱ ቢያንስ ስምንት ሰዎችን ሲገድል የከተማዋን ደኅንነት የስጋት ጥላ እንዲያንዣብብበት አድርጓል።
በተጨማሪም አልሸባብ ከሞቃዲሾ ወጣ ብለው ከአፍጎዬ ከተማ ጋር በሚያገናኘው መንገድ ላይ የሚገኙትን ላፎሌ፣ ሃዋ አብዲ እና ኤላሻ ቢያ አካባቢዎችን ለአጭር ጊዜም ቢሆን በቁጥጥር ስር አውሏል።

እየተንገታገተ የሚገኘው የአፍሪካ ኅብረት ተልዕኮ
በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ሥልጣን ባለፈው ታኅሣሥ በይፋ አብቅቷል።
ዕቅዱ የሶማሊያ ጦር የአገሪቱን ፀጥታ ሙሉ በሙሉ እንዲቆጣጠሩ የነበረ ቢሆንም መንግሥት በሽግግሩ ወቅት ኃይሉን ለማጠናከር አዲስ ተልዕኮ እንዲሰማራ ጠይቋል።
እንደ አውሮፓውያኑ በታኅሣሥ 27/2024 የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት አዲሱን የአፍሪካ ኅብረት ድጋፍ እና ማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ከታኅሣሥ 2025 ጀምሮ ለ12 ወራት እንዲቀጥል አጽድቋል።
ሆኖም ጥቂት ወታደሮች (ወደ 11,000 አካባቢ) ያሉት እና ከአቲሚስ የበለጠ ጠባብ ሥልጣን ያለው ኤዩሶም፣ አሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ እንደማትሰጥ ካሳወቀች በኋላ የማያላውስ የገንዘብ ተግዳሮት አጋጥሞታል።
የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ውሳኔውን በሶማሊያ መንግሥት ውስጥ ካለው ደካማ ቁጥጥር እና ሙስና ጋር አያይዘውታል።
አሁን ቢያንስ ለሰባት ወራት ደሞዝ ሳያገኙ የቆዩት የኤዩሶም ወታደሮች በአካባቢው ሕዝብ ላይ ብስጭታቸውን መወጣት ሊጀምሩ እንደሚችሉ የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉ።
ባለፈው ሚያዝያ አጋማሽ የሶማሊያ መንግሥት በታችኛው ሸበሌ የኡጋንዳ ጦር እርሻን በቁጥጥር ስር አውሎ ወደ አየር ማረፊያነት ከመቀየሩ በፊት ሰብሎችን መውሰዱን ገልጿል።
የኡጋንዳ መከላከያ ሚኒስትር ጃኮብ ማርክሰንስ ኦቦዝ በሚያዝያ 25 በካምፓላ የኤዩሶም ጦር አባል አገራት ሚኒስትሮች ባደረጉት ስብሰባ የአልሸባብ ዳግም ማንሰራራት በአፍሪካ ቀንድ ላይ ከባድ ስጋት መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እንዳለው ኤዩሶም አልሸባብን ለመቋቋም 8,000 ተጨማሪ ጦር ያስፈልገዋል።
በአውሮፓውያኑ 2012 አንስቶ፣ ኢትዮጵያ በሶማሊያ የአፍሪካ ኅብረት የሽግግር ተልእኮ (አትሚስ) አካል ኾና ቆይታለች።
የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መንግሥታት፣ በአዲሱ የአፍሪካ ኅብረት የድጋፍ እና የማረጋጋት ተልዕኮ (ኤዩሶም) ውስጥ፣ የኢትዮጵያን ጦር ተሳትፎ የሚያረጋግጥ ስምምነት መፈራረማቸው የታወሳል።

ሞቃዲሾ በአልሸባብ እጅ ልትወድቅ ትችላለች?
በአውሮፓውያኑ ሚያዝያ 18 አንድ አጥፍቶ ጠፊ በሞቃዲሾ በሚገኘው በዳማኒዮ ካምፕ ውስጥ የጦር ሠራዊት አባላትን ዒላማ አድርጎ ነበር።
ጠንካራ የአፍሪካ ኅብረት የፀጥታ ድጋፍ ከሌለ አልሸባብ ሞቃዲሾ ላይ ጥቃት ሊሰነዝር እና ደካማ የሆነውን የአገሪቱ ጦር ሊያፈራርሰው ይችላል የሚል ስጋት አይሏል።
የካቲት መጨረሻ ላይ ታጣቂዎቹ ለአጭር ጊዜም ቢሆን ከሞቃዲሾ 30 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኘዋን ባላድን በቁጥጥር ስር ሲያውሉ፤ የአሜሪካ ኤምባሲ በዋና ከተማዋ ከሳምንት በኋለ ጥቃት ይኖራል ሲል ያስጠነቀቀ ሲሆን ከተማዋ በታጣቂዎቹ እጅ ትወድቃለች የሚል ስጋት አስከትሏል።
አልሸባብ በሞቃዲሾ ደጃፍ ላይ እንደሚገኝ ሲነገር በዓለም ዙሪያ ያሉ ታጣቂዎችም ተደስተው ነበር።
እንደ እውነቱ ከሆነ አልሸባብ ሞቃዲሾን ለመያዝ አስፈላጊውን የሰው ኃይል ያዘጋጀ፣ በቁሳቁስም ቢሆን የደረጀ አይመስልም።
ይህ ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ባይሆንም በአጠቃላይ ግን ከብሔራዊ ጦር የበለጠ ቁርጠኛ እና የተቀናጀ ኃይል አለው።
በመስከረም 2022፣መንግሥት ቡድኑ ከ15,000 እስከ 18,000 የሚደርሱ ተዋጊዎች እንዳሉት ገምቶ ነበር። ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች የታጣቂዎቹ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል።
መንግሥት ሁለት እጥፍ ወታደሮች እና የደኅንነት አባላት አሉት።
አንድ የተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ አባል በመጋቢት ወር እንደገለፁት መንግሥት እስከ 70,000 የሚደርሱ የሠራዊት አባላት (የፖሊስ መኮንኖች እና የስለላ መኮንኖችን ጨምሮ) እንዳሉት ተናግረዋል።
ነገር ግን የመንግሥት ኃይሎች በጎሳ ክፍፍል፣ በሥነ ምግባር፣ በሥርዓት ጉድለት እና በተበታተነ የሥልጠና እና የዕዝ መዋቅር ደካማ ናቸው።
ሶማሊያ የኃያላን አገራት ድጋፍ አላት።
እንደ ሱማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ ከሆነ ቱርክ በቅርቡ በሞቃዲሾ የሚደርስ ጥቃትን ለመከላከል በሚል 500 ወታደሮችን ወደ አገሪቱ የላከች ሲሆን 2,000 ተጨማሪ እንደሚመጡ ገልጻለች።
ቱርክ በሶማሊያ ሰፊ መዋዕለ ንዋይ የምታፈስ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን በማሠልጠን የጦር አውሮፕላኖችን ጨምሮ የላቀ የጦር መሳሪያዎችን ትደግፋለች።
በተጨማሪም በሞቃዲሾ ከሚገኙት ትልቁ የባሕር ማዶ አገራት ወታደራዊ ካምፖች መካከል አንዱ የቱርክ ነው።
ምንም ይሁን ምን የአልሸባብ ጥቃት ስኬት በሶማሊያ ውስጥ ዘላቂ መረጋጋትን ወደ ነበረበት ለመመለስ ለዓመታት የተደረገው ጥረት ላይ ከባድ ጉዳት ያደረሰ ነው።