
ከ 2 ሰአት በፊት
ሀን ቴሱን ልጇን ስታስታውስ የመጨረሻ ትውስታዋ ወደ አውሮፓውያኑ 1975 ይወስዳታል።
ልጇ ኩንግሀ ከገበያ እንድትገዛላት የምትፈልገው ነገር ካለ ጠየቀቻት። ልጇ ከጓደኞቿ ጋር መጫወት ስለፈለገች ገበያ አብራት አልሄደችም።
ከዚያ ቀን በኋላ እናትና ልጅ ለአራት አሥርታት አልተያዩም።
ኩንግሀ እናቷን ያገኘችው ትልቅ ሰው ከሆነች በኋላ ነው። ስሟ ሎሪ ቤንደር ተብሏል። በዜግነትም አሜሪካዊት ናት።
ኩንግሀ ከቤቷ ነበር ታፍና የተወሰደችው። ወደ ሕጻናት ማሳደጊያ ተወስዳ በሕገ ወጥ መንገድ አሜሪካ ተወስዳለች።
እናቷ ሀን የደቡብ ኮሪያን መንግሥት እየከሰሰች ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማጭበርበር፣ በሕገ ወጥ ማደጎ፣ በአፈና እና በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ምርመራ እንዲደረግ ጠይቀዋል። ከእነዚህ አንዷ ሀን ናት።
የደቡብ ኮሪያ አነጋጋሪ የማደጎ ሥርዓት ያላት አገር ናት።
በ1950ዎቹ የማደጎ አሠራር ከተዘረጋ ጀምሮ እንደ ደቡብ ኮሪያ ልጆችን ወደ ውጭ አገራት ለማደጎ የላከ አገር የለም።
ከ170,000 እስከ 200,000 ልጆች በአብዛኛው ወደ ምዕራባውያን አገራት በማደጎ ተልከዋል።
አሠራሩ ላይ ክትትል ባለማድረግና የግል ተቋማት በጅምላ ልጆችን ለማደጎ እንዲወስዱ በማድረግ የአገሪቱ ተከታታይ መንግሥታት ይተቻሉ።
ሀን በቀጣይ ወር ጉዳዩን ፍርድ ቤት ትወስዳለች። ለተጨማሪ ምርመራዎችና ክሶች በር ይከፍታል ተብሎም ይታሰባል።
በማደጎ ከተወሰዱ ልጆች መካከል አሜሪካ የተወሰደ ግለሰብ በ2019 ክስ በመመሥረት የመጀመሪያው የማደጎ ልጅ ሆኗል።
ሀን ደግሞ ክስ በመመሥረት የመጀመሪያዋ ወላጅ እናት ትሆናለች።
የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ቃል አቀባይ “በግለሰቦችና ወላጆች ላይ የደረሰው የስሜት ጠባሳ ያሳዝነናል። ለረዥም ጊዜ ሳይገናኙ መቅረታቸው ልብ ይሰብራል” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
የ71 ዓመቷ ሀን የምትከፍተውን ክስ ተከትሎ መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ ትፈልጋለች።
“44 ዓመት ልጄን ስፈልግ አእምሮዬም አካሌም ተጎድቷል። አንድም ሰው ይቅርታ አልጠየቀኝም” ትላለች።

ሀን እና ባለቤቷ ለዓመታት ልጃቸውን ሲፈልጉ ነበር። በየፖሊስ ጣቢያውና ሕጻናት ማሳደጊያው በመሄድ የልጃቸውን ፎቶ ለጥፈው ፈልገዋታል።
“አሥሩም የእግር ጥፍሮቼ እስከሚነቀሉ በየመንገዱ እፈልጋት ነበር” ስትል እናትየው ታስታውሳለች።
በ1990 በቴሌቭዥን ቀርባ ታሪኳን ካጋራች በኋላ ልጇ ልትሆን ትችላለች ከተባለች ወጣት ጋር ብትገናኝም ወጣቷ ልጇ እንዳልሆነች ነግራታለች።
ከደቡብ ኮሪያ በማደጎ የተወሰዱ ልጆች የዘረ መል ናሙና የሚሰጡበት ‘325 ካርማ’ የተባለ ገጽ ላይ ተመዘገበች።
በ2019 ፍለጋዋ ውጤት ማሳየት ጀመረ። ከሀን ዘረ መል ጋር ተመሳሳይ የሆነ ዘረ መል ያላት ሴት ካሊፎርንያ ተገኘች።
ሎሪ ነርስ ናት። ከእናቷ ጋር ተመሳሳይ ዘረ መል እንዳላቸው ከታወቀ በኋላ ወደ ሲዑል በረረች።
“ፀጉር አስተካካይ ሆኜ 30 ዓመት ሠርቻለሁ። ልጄ መሆኗን ፀጉሯን ዳብሼ አውቃለሁ” ትላለች ሀን።
መጀመሪያ ልጇን ስታገኛት ይቅርታ ነው የጠየቀቻት። ለዓመታት ወላጆቿ እየፈለጓት መሆኑን አለማወቋ እንዴት ልጇን ሊረብሻት እንደሚችል ትገምታለች።
ኩንግሀ ከእናቷ ጋር ስትገናኝ እምባዋን ማቆም አልቻለችም።
“ልቤ ለዓመታት ሽንቁር ነበረው። አሁን ገና ነው ልቤ ሙሉ የሆነው። ሙሉ ሰው ሆኛለሁ” ብላለች።
ኩንግሀ የተሰረቀች ቀን ምን እንደተፈጠረ እናትና ልጅ ከ44 ዓመታት በኋላ ማውራት ችለዋል።
ኩንግሀ ስትሰረቅ ገና 6 ዓመቷ ነበር።

እየተጫወተች ሳለ አንድ ሴት ተጠጋቻት። እናቷን እንደምታውቃት ነግራት ወደ ባቡር ጣቢያ ወሰደቻት።
ከዚያም ፖሊሶች አግኝተው የሕጻናት ማሳደጊያ አስገቡዋት። አሜሪካ፣ ቨርጂኒያ የሚኖሩ ጥንዶች በማደጎ ወሰዷት።
የሕጻናት ማሳደጊያ ተጥላ እንደተገኘች የሚገልጹ ሰነዶች ሐሰተኛ መሆናቸውን የደረሰችበት ከዓመታት በኋላ ነበር።
“ሐሰተኛ ሕይወት ነበር ስኖር የነበረው” ብላለች ልጅቷ።
እናትና ልጅ ከ44 ዓመታት በኋላ ቢገናኙም በርካታ ልጆች ከደቡብ ኮሪያ በማደጎ ተወስደው ከወላጆቻቸው ጋር ሳይገናኙ ይቀራሉ።
በአገሪቱ ማደጎ መጀመሪያ ላይ የተጀመረው ልጅ ማግኘት የሚፈልጉ ጥንዶች ለመርዳት ነበር። አሠራሩን የሚቆጣጠሩት የግል ተቋማት ቢሆኑም መንግሥት ቁጥጥር ያደርግም ነበር።
እአአ በ1985 ብቻ 8,800 ልጆች በማደጎ ተልከዋል።
በምዕራባውያን አገራት የወሊድ ምጣኔ ከመቀነሱ ጋር በተያያዘ በማደጎ ልጅ የማሳደግ ፍላጎት እየጨመረ ነው።
የእውነትና ዕርቅ ኮሚቴ በሚል የተመሠረተው ተቋም ከደቡብ ኮሪያ ይወሰዱ የነበሩ ሕጻናት “በካርጎ ተጭነው ይጓዙ ነበር” ይላል።
ሕጻናቱ በረዥም በረራ ወቅት እንክብካቤ አይሰጣቸውም ነበር።
ደቡብ ኮሪያ የምጣኔ ሀብት ዕድገት እያሳየች ከመሆኑ አንጻር በርካታ ሕጻናትን በማደጎ መላክ ተገቢ አይደለም የሚል ትችት ሲሰነዘር ቆይቷል።
የሕጻናት የማደጎ ጉዞ “ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል” በሚልም ሲገለጽ ቆይቷል።
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በማደጎ የሚወሰዱ ሕጻናት ቁጥር ይመድብ ስለነበር ሕጻናት እየተሰረቁ ለማደጎ ይወሰዱ ነበር።
በሺዎች የሚቆጠሩ የጎዳና ተዳዳሪ ሕጻናትም በሕጻናት ማሳደጊያዎች ገብተዋል።
አንዳንድ ወላጆች ልጆቻቸው ታመው መሞታቸው ቢነገራቸውም ልጆቻቸው ግን በማደጎ ይወሰዱ ነበር።
ያለ ወላጆች ፈቃድ ልጆች ለማደጎ ስለሚሰጡ ሐሰተኛ ሰነዶች ይዘጋጃሉ።
ልጆቹ ስለ ወላጆቻቸው ማንነት ከጠየቁ ወላጆቻቸው እንደሞቱ ወይም ለማደጎ ጥለዋቸው እንደሄዱ ይነገራቸዋል።
ለማደጎ ልጆች መብት የሚሠራ ተቋም የመሠረተው ሀን ቡንዩንግ “መንግሥት ጭካኔ ነው የፈጸመብን። ታግተን በሐሰተኛ ሰነድ ነው የተዘዋወርነው። የሰብአዊ መብት ጥሰት ነው። ጥፋተኞች ተቀጥተው ፍትሕ ያስፈልጋል” ይላል።
የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት የግል ተቋማት የማደጎ ሒደቱን እንደሚቆጣጠሩ ቢገለጽም መንግሥትም ከፍተኛ ድርሻ ወስዷል።
የዓለም አቀፍ ማደጎ አጥኚ ሺን ኦኢልሲክ “ካፕቴኑ መንግሥት ነበር። የግል ተቋማት እንደ ሹፌር አገልግለዋል” ይላሉ።
ሀን ልጇን ብታገኝም ፍትሕ እንዲሰፍን ትጠይቃለች።
“ልጄን ባገኛትም የእውነት እንዳገኘኋት አይሰማኝም። መላው ሕይወቴ ነው የተመሳቀለው። የትኛውም ያህል ገንዘብ ያጣሁትን አይመልስልኝም” ትላለች።