ከታሰሩት የጤና ባለሙያዎች መካከል
የምስሉ መግለጫ,ከታሰሩት የጤና ባለሙያዎች መካከል

23 ግንቦት 2025

የኢትዮጵያ ባለስልጣናት የስራ ማቆም አድማ እያደረጉ ካሉ የጤና ባለሙያዎች ጋር ሊደራደሩ እንደሚገባ እና የታሰሩትንም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ የመብት ተቆርቋሪው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠየቀ።

በተጨማሪም በሰላማዊ መንገድ የስራ ማቆም አድማ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ወከባ እና ማስፈራራት ባለስልጣናቱ እንዲያቆሙ ተቋሙ አርብ፣ ግንቦት 15/ 2017 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አሳስቧል።

“ምንም አይነት የመፍትሄ አቅጣጫ ሳይያዝ የስራ ማቆም አድማው ሁለተኛ ሳምንቱ የያዘ ሲሆን ይህም በመላው አገሪቱ አስፈላጊ የሆነው የጤና ዘርፍ አገልግሎት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል አስከትሏል። መንግሥት፣ በመላው አገሪቱ ያሉ ታካሚዎችን የጤና አገልግሎት የማግኘት መብትን በእጅጉ የሚገድበው ቀውስን የበለጠ ማራዘም የለበትም። መንግሥት እና የጤና ባለሙያዎች በጋራ እና ገንቢ በሆነ መልኩ በድርድር ይህንን ችግር ሊፈቱት ይገባል” ሲሉ የአምነስቲ የምስራቅ እና የደቡብ አፍሪካ ቀጣና ዳይሬክተር ታይገሬ ቻጉታህ አሳስበዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም “የአሁኑ ወቅት በጭካኔ ለማፈን እና ይህንን ለማሳየት ጊዜው አይደለም። ባለስልጣቱ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት እና የጤና አገልግሎቶችን እንደገና ለማስጀመር ወደ ድርድር ጠረጴዛው ሊመጡ ይገባል” ብለዋል።

የስራ ማቆም አድማ ከተጀመረበት ዕለት ከግንቦት 5/ 2017 ዓ.ም ጀምሮ በመላ አገሪቱ የታሰሩ የ212 ጤና ባለሙያዎችን የስም ዝርዝር ሐሙስ፣ ግንቦት 14/ 2017 ዓ.ም ከጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ እንዳገኘ አምነስቲ ገልጿል።

ከሰሞኑ ‘የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ’ በሚል ስያሜ የደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄን ጨምሮ የጤና ሥርዓቱን ያስተካክላሉ ያሏቸው 12 ጥያቄዎች ይመለስ በሚል ካነሱት የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ በመላው አገሪቱ ከ80 በላይ የጤና ባለሙያዎች መታሰራቸውን የንቅናቄው አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በተለይም በትላልቅ ከተሞች በሚገኙ ሆስፒታሎች የሚያገለግሉ በርካታ የጤና ባለሙያዎችን እያሰሩ እና እያዋከቡ መሆኑን የንቅናቄው አስተባባሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ፌደራል ፖሊስ በበኩሉ፤ በጤና ባለሙያዎች እየተነሳ ያለውን “የመብት ጥያቄ ሽፋን በማድረግ”፤ በአገሪቱ ውስጥ “ትርምስ እንዲፈጠር ከሚሠሩ ኃይሎች ጋር ያበሩ” ያላቸውን 47 የጤና ባለሙያዎች በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል።

ፌደራል ፖሊስ፤ የጤና ባለሙያዎችን እስር ለመጀመሪያ ጊዜ ያረጋገጠው አርብ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ነው።

አምነስቲ፣ በአዲስ አበባ ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ውስጥ 20 ባለሙያዎች ታስረው እንደሚገኙ በገለልተኛ አካል ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።

ተቋሙ የህግ ባለሙያዎች፣ በእስር ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች ቤተሰቦችን እንዲሁም የፍርድ ቤቶችን ሰነዶችን መገምገሙን በዚሁ መግለጫ አስፍሯል።

ለእስር ከተዳረጉት መካከል የፓቶሎጂ ባለሙያ የሆነችው ዶክተር ማህሌት ጉኡሽ አንዷ ስትሆን ከመታሰሯ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ከቢቢሲ ፖድካስት ጋር ቆይታ አድርጋ ነበር።

“ቢያንስ 20 የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች ተመጣጣኝ ክፍያ እና ምቹ የስራ ቦታ በመጠየቃቸው በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤት መታሰራቸው አሳፋሪ እንዲሁም በእጅጉ አሳሳቢ ነው። ፖሊስ ዓመጽ ማነሳሳት በሚል ያቀረበው መሰረተ ቢስ ውንጀላ ተቃዋሚዎችን ዝም ለማሰኘት እና ለመብታቸው የሚነሱትን ለማስፈራራት የዘፈቀደ እስራትን መጠቀሚያ ያደረገ አሳፋሪ አምባገነናዊ አሰራርን የሚያሳይ ነው” ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በእስር ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ሶስት የቤተሰብ አባላት “የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጉብኝትን የሚፈቅደውን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተላልፎ” ዘመዶቻቸውን እንዳይጠይቁ በመከልከሉ ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳሳደረባቸው አምነስቲ ነግረውኛል ብሏል።

የሕክምና ባለሙያዎቹ ከተመጣጣኝ ደመወዝ፣ ጥቅማጥቅም፣ የሙያ ዕድገት ዕድሎች እንዲሁም ከምቹ የሥራ ቦታ እና የሥራ ቦታ ነጻነት ጋር የተያያዙ ባለ 12 ነጥብ ጥያቄዎችን ለጤና ሚኒስትር ሚያዝያ 3/ 2017 ዓ.ም ማቅረባቸው ይታወሳል። የጤና መድን ሽፋን አለመዘርጋት፣ ከስራ ጋር በተያያዙ አደጋዎች በቂ ካሳ አለማግኘት፣ የደመወዝ መዘግየት እና ሌሎች መሰረታዊ ጉዳዮች ሲንከባለሉ የቆዩ ጉዳዮች መሆናቸው ተጠቅሷል።

መንግሥት አነዚህን ጥያቄዎች በተሰጠው 30 ቀናት ምላሽ ባለመስጠቱ ከግንቦት 5 ጀምሮ የሥራ ማቆም አድማ ለማድረግ መገደዳቸውን ባለሙያዎቹ ገልጸዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ የህብረተሰቡን ጤናን በመጠበቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና ቢጫወቱም የጤና ባለሙያዎች በአማካይ የሚያገኙት በወር 80 ዶላር ሲሆን ነርሶች፣ የጤና መኮንኖች እና ሌሎች ባለሙያዎች ከዚህ ያነሰ እንደሚከፈላቸው አምነስቲ ጠቅሷል።

አምነስቲ በዚሁ መግለጫው ላይ የኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ለማጠናከር እና በሰላማዊ ተቃውሞ ላይ ያሉ የጤና ባለሙያዎችን መብት ለማስጠበቅ የልማት አጋሮች የሁለትዮሽ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርጓል።

“ባለስልጣናት ከአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ግዴታዎቻቸው ጎን ለጎን ከፍተኛውን ሃብት እንደ ጤና ላሉ ወሳኝ የህዝብ አገልግሎቶች መመደባቸውን ለማረጋገጥ አስቸኳይ እርምጃዎችን መውሰድ አላባቸው” ብለዋል።