May 26, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ

ከደቡብ ሱዳን የመጡ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች፤ በጋምቤላ ክልል፣ በአኙዋሃ ዞን፣ ዲማ ወረዳ በሚገኝ ቦታ ላይ በከፈቱት “የደፈጣ ተኩስ ጥቃት” ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የወረዳው የአስተዳደር እና የፖሊስ ኃላፊዎች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናገሩ። በትላንትናው ዕለት ጠዋት በተፈጸመው በዚህ ጥቃት፤ በዘጠኝ ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን መመልከታቸውን በአካባቢው የሚገኙ የህክምና ባለሙያ ገልጸዋል።

የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ጥቃቱን የሰነዘሩት፤ ከዲማ ወረዳ 39 ሰዎች አሳፍሮ ወደ ጎግ ወረዳ ሲጓዝ በነበረ የህዝብ ማመላለሻ አውቶብስ ላይ እንደሆነ የወረዳው ፖሊስ አዛዥ ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክ ሜዶ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል። የህዝብ ማመላለሻ አውቶብሱ የደፈጣ ጥቃት የተሰነዘረበት፤ ከዲማ ከተማ 45 ኪሎ ሜትር ርቀት ተጉዞ አቻኛ እና 45 በተባሉ ቀበሌዎች መካከል በደረሰበት ወቅት እንደሆነ የፖሊስ አዛዡ አስረድተዋል።

ታጣቂዎቹ በአውቶብሱ ላይ ተኩስ በከፈቱበት ወቅት “መሳሪያ የያዘ ተሳፋሪ” መልሶ በመተኮስ አጸፋውን መመለሱን ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክ አመልክተዋል። በተኩስ ልውውጡ አንድ ታጣቂ መገደሉንም የፖሊስ አዛዡ ጠቁመዋል። በታጣቂዎቹ የደፈጣ ጥቃት የአውቶብሱን ሹፌር ጨምሮ የስድስት ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በስድስት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱንም ጨምረው ገልጸዋል። 

ታጣቂዎች ጥቃቱን ከሰነዘሩ በኋላ በህዝብ ማመላለሻው አውቶብሱ ላይ የመገልበጥ አደጋ መድረሱንም ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክም አክለዋል። በጥቃቱ ቀላል ጉዳት የደረሰባቸው በዲማ ወረዳ ጤና ጣቢያ ህክምና እንዲያገኙ መደረጉን የገለጹት ረዳት ኢንስፔክተር ኡታክ፤ ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠማቸው ወደ ሚዛን ቴፒ ከተማ መላካቸውን አብራርተዋል። 

ከጥቃቱ በኋላ ዘጠኝ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ዲማ ጤና ጣቢያ መምጣታቸውን በህክምና ተቋሙ የሚሰሩ አንድ የጤና ባለሙያ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል ሶስቱ ለተሻለ ህክምና ወደ ሚዛን አማን ሆስፒታል መወሰዳቸውንም ተናግረዋል። 

የትላንቱን ጥቃት የፈጸሙት “ሲቪል የለበሱ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ናቸው” ሲሉ የዲማ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ ወንጅለዋል። ከደቡብ ሱዳን የሚነሱት እነዚሁ ታጣቂዎች ከዚህ ቀደምም ድንበር አቋርጠው ወደ አካባቢው በመግባት፤ በወረዳው ነዋሪዎች ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱ እና ከብቶቻቸው ሲዘረፉ መቆየታቸውንም አስረድተዋል። 

ፎቶ፦ የዲማ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

የዲማ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ኡጁሉ ኡጁሉም በወረዳው ስር በሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቃቶች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ከሁለት ወር በፊት በናምካዶ፣ ቻሞ እና ኡጁዋ ቀበሌዎች የተፈጸሙ ጥቃቶችን በማሳያነት የጠቀሱት የወረዳው አስተዳዳሪ፤ በዚህ ጊዜም የሰዎች ህይወት ማለፉን ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል።

የትላንቱን ጥቃት ተከትሎ የአካባቢው ሚሊሺያዎች ታጣቂዎቹን ተከታትለው ለመያዝ ያደረጉት ሙከራ አለመሳካቱንም አቶ ኡጁሉ አመልክተዋል። የዲማ ወረዳ ፖሊስ አዛዥ በበኩላቸው ጥቃቱ ወደ ደረሰበት ቦታ የፖሊስ ኃይል መሰማራቱን አስረድተዋል።  

የሙርሌ ታጣቂዎች በዲማ ወረዳ ላይ ጥቃቱን የሰነዘሩት፤ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ እና ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ወደ አካባቢው ካቀኑ ከአንድ ቀን በኋላ ነበር። ርዕሰ መስተዳድሯ ባለፈው ሳምንት አርብ እና ቅዳሜ ጠዋት በዲማ ወረዳ ካሳለፉ በኋላ በዚያኑ ዕለት ከሰዓት ወደ ሚዛን ከተማ አምርተዋል። 

ፎቶ፦ የዲማ ወረዳ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት

አለሚቱ ወደ ሚዛን ከተማ የተጓዙት በጋምቤላ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች “የሰላም እና የትብብር ፎረም” ላይ ለመገኘት ነበር። በትላንትናው ዕለት የተካሄደው ይህ ፎረም ሲጠናቀቅ፤ ወደ ዲማ ወረዳ መመለሳቸውን የአካባቢው ምንጮች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሯ እና ምክትላቸው ዶ/ር ጋትሉዋክ ሮን በዛሬው ዕለት ከዲማ ወረዳ ከፍተኛ አመራሮች ጋር “በተለያዩ ጉዳዮች ላይ” ውይይት ማድረጋቸውን የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ ከሰዓት ባወጣው መረጃ አስታውቋል። በዛሬው ውይይት ከተነሱ ጉዳዮች ውስጥ “የሙርሌ ጎሳ ድንበር ዘለል ጥቃት እንቅስቃሴ” አንዱ መሆኑን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል። 

በወረዳው የሙርሌ ጎሳ ጥቃት “ከሰሞኑ መከሰቱን” የጠቀሰው ጽህፈት ቤቱ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ “የተጠናከረ የጸጥታ አካላት ክትትል እንዲደረግ” በውይይት መድረኩ ላይ “አቅጣጫ ተቀምጧል” ብሏል። በዲማ ወረዳ ያለው የሙርሌ ታጣቂዎች እንቅስቃሴ “እንዲገታ”፤ መንግስት ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በዚሁ ውይይት ላይ መናገራቸውንም ጽህፈቱ ቤቱ አመልክቷል።

Post

Ethiopia Insider

@ethiopiainsider

የሙርሌ ታጣቂዎች በጋምቤላ ክልል የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች ተባብሰው ቀጥለዋል ተባለ። ታጣቂዎቹ

ትላንት በኑዌር እና አኙዋ ዞኖች በፈጸሙት ጥቃት 2 ሰዎች መግደላቸውን የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ

አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ተናግረዋል።

https://ethiopiainsider.com/2022/6240/

Image

1 2 2

የደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች ድንበር ተሻግረው በየጊዜው ለሚፈጽሟቸው ጥቃቶች፤ የፌደራል መንግስት በዘላቂነት መፍታት ያልቻለበት ምክንያት ከዓመታት በፊትም በፓርላማ ጭምር ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ነበር። በየካቲት 2014 በተካሄደ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ የሙርሌ ታጣቂዎች በሚሰነዝሩት ጥቃት አሁንም የሰው ህይወት እያለፈ ይገኛል፤ ህጻናትም እየተሰረቁ ነው” ሲሉ የማጃንግ ዞን የፓርላማ ተመራጭ አሳሳቢ ላሉት ችግር ትኩረት እንዲሰጥ አቤት ብለው ነበር። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)