May 26, 2025

የቀድሞው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በነበሩት አቶ ጌታቸው ረዳ እና የእርሳቸውን ጎራ በተቀላቀሉ የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የተመሰረተ አዲስ ክልላዊ ፓርቲ፤ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ “ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃድ” አገኘ። “ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ” (ስምረት) የሚል ስያሜ ያለው አዲሱ ፓርቲ ያዘጋጃቸው ሰነዶች፤ “በህወሓት ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ይቀርቡ የነበሩ ናቸው” ተብሏል።

የአዲሱ ፓርቲ የሚዲያ እና የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ ረዳኢ ሓለፎም ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” እንደተናገሩት፤ “ስምረት”ን ለማስመዘገብ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የቀረበው ከሁለት ሳምንት በፊት ነው። “ስምረት” በክልላዊ ፓርቲነት ለመመዘገብ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ፤ አስተባባሪዎቹ በዛሬው ዕለት ጊዜያዊ የምዝገባ ፍቃድ ሰርተፊኬት ከምርጫ ቦርድ መቀበላቸውን አቶ ረዳኢ ገልጸዋል። 

ለሶስት ወራት የሚያገለግለው የጊዜያዊ ምዘገባ ፈቃድ ለአዲሱ ፓርቲ ዛሬ ሰኞ ግንቦት 18፤ 2017 መሰጠቱን የምርጫ ቦርድ የኮሚዩኒኬሽን ክፍል ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጧል። የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነምግባር አዋጅ፤ የፖለቲካ ፓርቲ ለማስመዘገብ ጥያቄ ያቀረቡ አመልካቾች “በቂ ምክንያት ያቀረቡ ከሆነ” የተሰጣቸው ጊዜያዊ የምዘገባ ፈቃድ ለተጨማሪ ሶስት ወራት ሊራዘም እንደሚችል ይደነግጋል። 

ይኸው አዋጅ፤ የጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃዱ የሚያገለግለው “የፖለቲካ ፓርቲውን ለማስመዘገብ የሚያስፈልጉ ተግባራትን ለማከናወን ብቻ ይሆናል” የሚል ድንጋጌም ይዟል። ምርጫ ቦርድ ለአዲሱ ፓርቲ በሰጠው ጊዜያዊ የምዝገባ ፈቃዱ ሰርተፊኬት መጨረሻ ላይም ይህንኑ ድንጋጌ “በማሳሰቢያነት” አስፍሯል።

ጊዜያዊ ፈቃድ ያገኘ የፖለቲካ ፓርቲ፤ በምርጫ ቦርድ በቋሚነት ለመመዘገብ ማሟላት ከሚገባቸው ሰነዶች መካከል፤ የፖለቲካ ፓርቲው መመስረቻ ጽሁፍ፤ ፕሮግራም እና መተዳደሪያ ደንብ ይገኙበታል። አቶ ረዳኢ “የአዲሱ ፓርቲ ሰነዶች፣ በህወሓት ለውጥ ለማምጣት ይቅርቡ የነበሩ ሰነዶች ናቸው። ለውጥ ከሚፈልጉ የትግራይ ተወላጆች በጋራ በመሆን፣ በውይይት በማዳበር እና ጉባኤ በማካሄድ ቋሚ የፓርቲ ምዝገባ ይካሄዳል” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አስረድተዋል።

አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በክልል የፖለቲካ ፓርቲነት የሚመሰረተው አራት ሺህ መስራች አባላት ሲኖሩት እንደሆነ በ2012 ዓ.ም የወጣው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ያስቀምጣል። ከእነዚህ መስራች አባላት ውስጥ ከስልሳ በመቶ በላይ የሆኑት የክልሉ መደበኛ ነዋሪዎች መሆን እንዳለባቸው በዚሁ አዋጅ ግዴታ ተጥሏል።

“ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ”ን ለመመስረት ከተሰባሰቡት ግለሰቦች ውስጥ፤ ባለፈው ነሐሴ ወር ከተካሄደውን የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ድርጅታዊ ጉባኤ የተቃወሙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ይገኙበታል። በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ጎራ ያካሄደውን ይህን ጉባኤ በወቅቱ የተቃወሙ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ብዛት 14 ነበር። 

አቶ ረዳኢ አዲሱ ፓርቲ “የህወሓት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የነበሩ” እና “ሌሎች ለውጥ ፈላጊ ኃይሎች የተሳተፉበት ነው” ሲሉ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ቢናገሩም፤ በቁጥር ምን ያህል እንደሆኑ ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል። “አዲስ ፓርቲ ወደ መመስረት የገባነው፤ ህወሓትን ለማዳን እና ለዘመኑ የሚመጥን ፓርቲ ለማድረግ የተደረገ ጥረት ባለመሳካቱ ነው” ሲሉም ሂደቱን አስረድተዋል። 

የአዲሱ ፓርቲ የሚዲያ እና የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ ለዚህ በማስረጃነት የጠቀሱት፤ ባለፈው ሚያዝያ ወር “በጋራ ጉባኤ ለማካሄድ” አድርግነዋል ያሉትን ጥሪ ነው። ይህ ጥሪ “ተቀባይነት ባለማግኘቱ አዲስ ፓርቲ ወደ መመስረት ገብተናል” ሲሉም አብራርተዋል። አዲስ ፓርቲ ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ ያሉ የቀድሞው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ያሉበትን ምክንያት ሲያስረዱ ደግሞ “ለህይወታችን አስጊ ሁኔታ በመኖሩ እና ደም መፋሰስ ለማስቀረት ነው” ብለዋል።

“አዲስ ፓርቲ ወደ መመስረት የገባነው፤ ህወሓትን ለማዳን እና ለዘመኑ የሚመጥን ፓርቲ ለማድረግ የተደረገ ጥረት ባለመሳካቱ ነው”አቶ ረዳኢ ሓለፎም፤ የዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ የሚዲያ እና የኮሚዩኒኬሽን ዘርፍ አስተባባሪ



ከፓርቲው መስራቾች መካከል አቶ ጌታቸው ረዳ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የአፍሪካ ቀንድ አማካሪ ሚኒስትር፣ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረህይወት ደግሞ የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ሆነው ተሹመው በአዲስ አበባ እየሰሩ ይገኛሉ። የትግራይ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ረዳኢ ሓለፎምም በአሁኑ ወቅት ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ከተማ እንዳደረጉ ለማረጋገጥ ተችሏል። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)