May 27, 2025

በቤርሳቤህ ገብረ
በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞች ውስጥ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት “በጣም ትልቅ ችግር ያለበት” የሻሸመኔ ከተማ መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተናገሩ። በሀገሪቱ ያለውን የውሃ ሽፋን በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት መቶ በመቶ ለማድረስ ይቻል ዘንድ፤ ክልሎች እና ከተሞች “የኮብል ስቶን” መንገዶችን ለመስራት “ቅድሚያ እንደሚሰጡት” ሁሉ ለውሃ አቅርቦትም ተመሳሳዩን እንዲያደርጉ ሚኒስትሩ ጠይቀዋል።
ዶ/ር ሀብታሙ ይህን ያሉት ዛሬ ማክሰኞ ግንቦት 19፣ 2017 በተካሄደው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ከፓርላማ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ነው። በዛሬው ስብሰባ ለሚኒስትሩ ጥያቄ ካቀረቡ ሰባት የፓርላማ አባላት መካከል አምስቱ በተመረጡባቸው አካባቢዎች ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር አንስተዋል።
ይህ ችግር የመረጣቸው ህዝብን በሚያነጋግሩበት ጊዜ በተደጋጋሚ የሚነሳ እና እነርሱም በአካል የተመለከቷቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በገዢው እና በተቃዋሚ ፓርቲ የፓርላማ ተመራጮች በተመሳሳይ መልኩ የተነሳው ይህ ጉዳይ፤ ይበልጡኑ ተደጋግሞ የቀረበው በአማራ ክልል ተወካዮች ነው።

በክልሉ ከሚገኘው ሰሜን ወሎ ዞን፣ ቡግና ወረዳ የተመረጡት የብልጽግና ፓርቲዋ ቅድስት አርአያ፤ አካባቢያቸው “ከፍተኛ የሆነ የውሃ ችግር” ያለበት መሆኑን ተናግረዋል። እርሳቸው በመጡበት ወረዳ የሚገኘው አይና ከተማ፤ “ህጻናት ሴቶች እና ወጣቶች ውሃ ፍለጋ ረጅም ሰዓት የሚንከራተቱበት፣ የትምህርት ሰዓታቸውን የሚያጠፉበት፣ ለከፍተኛ እንግልት እየተዳረጉበት” ያለ መሆኑን አስረድተዋል።
አይና ከተማ ላይ “ከውሃ ዘይት ይረክሳል” የሚል አባባል በህብረተሰቡ ዘንድ እንደሚነገርም ቅድስት በማሳያነት ጠቅሰዋል። ከዚህ ከተማ በአቅራቢያው ለሚገኘው የላሊበላ ከተማ የውሃ ፕሮጀክት ማስፋፊያ ጥያቄ መቅረቡንም በማከል፤ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በአካባቢው ያለውን ችግር ለመፍታት እያከናወነ ያለው ምን እንደሆነ ጠይቀዋል።
ከጎንደር ዙሪያ እንፍራንዝ ምርጫ ክልል ገዢው ፓርቲን ወክለው ፓርላማውን የተቀላቀሉት ተስፋነሽ ተፈራም እንደዚሁ በአካባቢያቸው ያለውን የመጠጥ ውሃ ችግር አንስተዋል። ጎንደር ከተማ “ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር ያለበት” መሆኑን የጠቆሙት የፓርላማ አባሏ፤ “ህዝቦቿ ውሃ እየተጠሙ ነው” ሲሉ የችግሩ አሳሳቢነት በአሃዝ በተደገፈ ንጽጽር አቅርበዋል።

በሀገር ደረጃ በከተማ እና ገጠር ያለው አጠቃላይ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ድምር ሽፋን “ከ64 በመቶ በላይ” መሆኑን የጠቀሱት ተስፋነሽ፤ በጎንደር ከተማ ያለው 21 በመቶ ሽፋን “እጅግ ዝቅተኛ” መሆኑን ተናግረዋል። በዚህም ማጣቀሻነት፤ የሀገር አቀፍ ሽፋን በሚል የሚጠቀሰው አሃዝ “መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው ወይ?” ሲሉ ጠይቀዋል።
በገጠር ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን “በጣም አነስተኛ” ሲሉ የገለጹት ተስፋነሽ፤ “የተወከልኩበት የማክሰኚት እንፍራንዝ [ህዝቦች]፤ ጣናዳር ተቀምጠው ውሃ እየተጠሙ ነው” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል። “እንደሀገር መቶ በመቶ ህዝባችን ንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆን ምን እየተሰራ ነው? መቼስ ነው የሚደርሰው?” ሲሉ የፓርላማ አባሏ ተጨማሪ ጥያቄ ሰንዝረዋል።
የኦሮሚያ ክልል የሻሸመኔ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ዎጌ ቁፋ በበኩላቸው፤ የመረጣቸው ህዝብ ከውሃ ተደራሽነት አኳያ “በቂ እና ዘላቂ” ድጋፍ ባለመገኘቱ ለችግር መጋለጡን እንደሚገልጽ አስረድተዋል። የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር “በሪጅን ደረጃ” የተደራጀ መሆኑን የገለጹት የፓርላማ አባሉ፤ ብዛት ያላቸው የገጠር ቀበሌዎች ወደ ሪጅኖች በመቀላቀላቸው እና ከተማው በፍጥነት እያደገ በመሆኑ ችግሩን እንዳባባሰው አስረድተዋል።

“በከተማው ከ48 አመት በፊት የተገነባው የውሃ ጉድጓድ እና መስመር ለ80 ሺህ ሰው ታስቦ ሲሆን በአሁኑ ጊዜ የህዝቡ ብዛት 371,168 በመድረሱ እና የተጠቃሚው ቁጥር ከመጠን በላይ በመጨመሩ፤ ለከፍተኛ የውሃ እጥረት በመጋለጣችን መፍትሄ እንሻለን ይላሉ” ሲሉ አቶ ዎጌ የአካባቢያቸው ህብረተሰብ የውሃ አቅርቦት ጥያቄ አስተጋብተዋል።
ለፓርላማ አባላቱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ፤ በሻሸመኔ ከተማ ከፍተኛ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዳለ አምነዋል። ሻሸመኔን “ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከተሞቻችን በጣም ትልቅ ችግር ያለበት” ሲሉ የጠሩት ሚኒስትሩ፤ ችግሩን ለመፍታት “ብድር መጠየቅ” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።
“ብድሩን ለመጠየቅ መስፈርቶች አሉ” ያሉት ዶ/ር ሀብታሙ፤ “የመጀመሪያው መስፈርት ቢዝነስ ፕላን ማዘጋጀት፣ እንዴት አድርጎ እንዴት ይገነባል? እንዴት ይመለሳል? ታሪፍ ስንት ነው? በስንት አመት ይመልሱታል?” የሚል እንደሆነ አብራርተዋል። ይህን “ማዘጋጀት ከቻሉ በእኛ በኩል ወረፋ ተይዞላቸው፣ እናስኬዳለን። ያንን እንደየቤት ስራ እንወስደዋለን። በብድር ደረጃ ቢዘጋጁ በጣም ጥሩ ይሆናል ማለት ነው” ሲሉ ከከተማዋ አስተዳደር የሚጠበቀውን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

የሻሸመኔ ከተማ በአሁኑ ወቅት በውሃ ምንጭነት የሚጠቀመው፤ ከወንዶ ወንዝ የሚመጣውን በማጣራት እና በአቅራቢያ ያሉ የውሃ ጉድጓዶችን እንደሆነ ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል። “ሻሸመኔ በጣም እያደገች ያለች ከተማ ነች። ስለዚህ ትልቁ መፍትሔ በዙሪያው ያሉ ከተሞችን ውሃ ማቅረብ ነው” ሲሉ ሚኒስትሩ አክለዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የላሊበላ ከተማን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል። በከተማው ያለውን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እርሳቸውም ጭምር በአካል ሄደው እንደተመለከቱት የጠቀሱት ዶ/ር ሀብታሙ፤ መስሪያ ቤታቸው “ትልቅ ትኩረት” ከሰጣቸው አካባቢዎች አንዱ ላሊበላ መሆኑን አመልክተዋል።
ለከተማው የውሃ ፕሮጀክት የሚሆን ዲዛይን ከተሰራ በኋላ በጀት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ “መፍትሔዎቹ የሚመጡት ከዚያ በኋላ ነው” ሲሉ መልሰዋል። ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገውን በጀት በተመለከተ ግን “ቃል ለመግባት ያስቸግራል” ብለዋል።

በተቃዋሚው የጌዲኦ ህዝቦች ዲሞክራቲክ ፓርቲ የፓርላማ ተወካይ አቶ ብርሃኑ ጎበና የተነሳው የጌዲኦ ዞን የውሃ ፕሮጀክት ጉዳይም በሚኒስትሩ ምላሽ ተሰጥቶበታል። በጌዲኦ ዞን ያለው የውሃ ፕሮጀክት እያለቀ መሆኑን እና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ትኩረት ያደረገበት ፕሮጀክት መሆኑን ዶ/ር ሀብታሙ ተናግረዋል።
“በዚሁ ዞን ላይ የተቆፈሩ ጉድጓዶች አሉ። ተቆፍረው ሳይጠቅሙ የቀሩ፣ ችግር ያለባቸው [አሉ]። ይሄንን ከዩኒሴፍ ጋር አያይዘነዋል። ዩኒሴፍ በሚያገኘው ገንዘብ፣ በሚያገኘው በጀት፣ ቅድሚያ እንዲሰጠን እየተነጋገርን እንገኛለን” ሲሉ አስረድተዋል። በሌሎች የፓርላማ አባላት በጥያቄነት የተነሱ የውሃ ፕሮጀክቶችም፤ በተመሳሳይ መልኩ ከአለም ባንክ፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ከአፍሪካ ወተር ፋሲሊቲ ጋር ለማያያዝ መታሰቡን ሚኒስትሩ አክለዋል።
የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ በማጠቃለያቸው የመለሱት፤ ሀገር አቀፍ የመጠጥ ውሃ ሽፋንን መቶ በመቶ ማድረስን በተመለከተ የቀረበላቸውን ጥያቄ ነው። ይህን ማሳካት “እንቆቅልሽ” እና “ረጅም ጊዜ የሚወስድ ነው” ሲሉ የተደመጡት ዶ/ር ሀብታሙ፤ ሆኖም በእነርሱ በኩል የተያዘው እቅድ ከፈረንጆቹ 2030 በኋላ መቶ በመቶ ሽፋን ላይ መድረስ እንደሆነ አመልክተዋል።
“በእኛ ሀሳብ በፈረንጆቹ 2030 ከአምስት አመት በኋላ አሁን ባለን ፍጥነት፣ አሁን ባለን አቅም አና የማስፈጸም አቅም [መቶ በመቶ ሽፋን] እናደርሳለን”– ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፤ የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር
“አሁን ባለን ፍጥነት፣ አሁን ባለን አቅም አና የማስፈጸም አቅም፤ ከአምስት አመት በኋላ እናደርሳለን” ሲሉ ሚኒስትሩ ለፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል። ይህን ለማሳካት ግን “ድጋፍ” እና “ሀብት” ያስፈልጋል ባይ ናቸው ዶ/ር ሀብታሙ። “ከውጭ የሚመጣው በጀት ብቻ በቂ አይደለም” ያሉት ሚኒስትሩ፤ “የክልል መንግስታት ከተሞቻችን በእያንዳንዱ ከተማ ውስጥ ለኮብል ስቶን ቅድሚያ እንደሚሰጡ፣ ለሼድ ቅድሚያ እንደሚሰጡ፣ ለውሃም ሊሰጡ ይገባል” ሲሉ አሳስበዋል።
የፌደራል መንግስት ለ2017 በጀት ዓመት ካጸደቀው 971.2 ቢሊዮን ብር ውስጥ ለውሃ እና ኢነርጂ የተመደበው 25.26 ቢሊዮን ብር ነው። ከአጠቃላይ በጀቱ ውስጥ ያለው 3.4 በመቶ ድርሻ ያለው የውሃ እና ኢነርጂ ዘርፍ፤ ከመደበኛ እና ካፒታል ወጪዎች ዝርዝር አንጻር በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠ ነው። (ኢትዮጵያ ኢንሳይደር)