ኮሌራ መታከም የሚችል ቢሆንም በሱዳን ደካማ የጤና መሰረተ ልማት ምክንያት በበሽታው ሰዎች እየሞቱ ነው።
የምስሉ መግለጫ,ኮሌራ መታከም የሚችል ቢሆንም በሱዳን ደካማ የጤና መሰረተ ልማት ምክንያት በበሽታው ሰዎች እየሞቱ ነው።

ከ 9 ሰአት በፊት

ዓለም አቀፍ የነፍስ አድን ኮሚቴ (አይአርሲ) በጦርነት እየተናጠች ያለችው ሱዳን በኮሌራ እና ሌሎች በሽታዎች መቀስቀስ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ውስጥ ለመግባት ጫፍ ላይ ናት ብሏል።

በአንድ ሳምንት ብቻ 172 ሰዎች በኮሌራ በሽታ ሕይወታቸው ማለፉን የሱዳን ጤና ሚኒስቴር ያሳወቀ ሲሆን፤ አዳዲስ ኬዞች በካርቱም ግዛት መመዝገባቸውን ገልጿል።

የሱዳን ሐኪሞች የድሮን ጥቃቶች በውሃ ማጣሪያ ጣቢያዎች ኃይል እንዲቋረጥ ማድረጉን ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

ይህም ሰዎች ንፁህ ያልሆነ ውሃን እንዲጠቀሙ ምርጫ አሳጥቷል ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የነፍስ አድን ኮሚቴ የሱዳን ዳይሬክተር ኢቲዛዝ የሱፍ እንዳሉት ሦስት ዓመቱን የያዘው የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት “የኮሌራ በሽታ እንዲያገረሽ አድርጓል”።

ኮሚቴው በመግለጫው የኮሌራ ክትባት ተደራሽነት ዝቅተኛ መሆኑን ያሰመረ ሲሆን፤ አስፈላጊ ግብዓቶችም እየቀነሱ መሆኑን ጠቅሷል።

የሕክምና ረድኤት ድርጅት የሆነው ድንበር የለሽ የሐኪሞች ቡድን ካለፈው ወር አጋማሽ ጀምሮ በካርቱም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኮሌራ መያዛቸውን አስታውቋል።

በሱዳን የቡድኑ አስተባባሪ ስሌይመን አማር “ግጭቱ በግልፅ አስፈላጊ መሰረተ ልማቶችን ጎድቷል” ብለዋል።

በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚገኙ የጤና ተቋማት “አገልግሎት አይሰጡም አሊያም ለኪስ ተመጣጣኝ አይደሉም” ያሉ ሲሆን አብዛኞቹ የጤና ባለሙያዎች በግጭቱ ምክንያት ለቀው ለመውጣት ተገደዋል ሲሉ አክለዋል።

አገልግሎት የሚሰጡ ጥቂት የጤና ተቋማት ደግሞ ከአቅማቸው በላይ መጨናነቃቸውንም ተናግረዋል።

በካርቱም ባለፈው ሳምንት በአንድ ቀን ብቻ 500 የኮሌራ ኬዞች መመዝገባቸውን ኃላፊው አስታውቀዋል።

ከካርቱም ባሻገር በሰሜን እና ደቡብ ሱዳን ኮሌራ መቀስቀሱን አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘግቧል።

በአብዛኞቹ በኮሌራ የሚያዙ ሰዎች ቀላል ምልክቶች ወይም ምንም ምልክት ላያሳዩ ይችላሉ።

ነገር ግን በሽታው ከባድ ተቅማጥ የሚያስከትል ከሆነ ገዳይ ሲሆን በአንቲባዮቲክስ እና ግሉኮስ መታከም እንደሚችል የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ይገልፃል።

በአገሪቱ ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል በተጀመረው የስልጣን ሽኩቻ ምክንያት ከሁለት ዓመታት በፊት በተቀሰቀሰው የሱዳን ግጭት ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ተገድለዋል።

ሚሊዮኖች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ የተገደዱ ሲሆን፤ ጦርነቱ አገሪቱን የዓለማችን የከፋ የሰብዓዊ ቀውስ ውስጥ እንደከተታት የመንግሥታቱ ድርጅት ገልጿል።