
ከ 8 ሰአት በፊት
የወር አበባ መቅረት (amenorrhea) በብዛት ከእርግዝና ጋር ይተሳሰራል። ሆኖም ግን እርግዝና ሳይፈጠርም የወር አበባ የሚቀርባቸው ምክንያቶች አሉ።
የወር አበባ በአማካይ በ28 ቀናት ይመጣል። ከ24 እስከ 35 ባሉት ቀናት የወር አበባ ዑደት ያላቸው ሴቶችም አሉ።
የወር አበባ አልፎ አልፎ ቢቀር እንደ ችግር ባይወሰድም በተደጋጋሚ ከተከሰተ መነሻ ምክንያቱ መታወቅ አለበት።
የማሕጸን ሐኪም ዶ/ር አሚራ አልኮርዲን ማርቲኔዝ እንደሚሉት፣ ሰውነት በምን መንገድ ይሠራል የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል።
“ትክክል ያልሆነ ነገር ሲከሰት ማወቅ ያስፈልጋል። እያንዳንዷ ሴት ሰውነቷ በተለያየ መንገድ ይሠራል። አንድ ዓይነት ሊሆን አይችልም” ይላሉ።
እርግዝና ሳይከሰት ለሦስት ተከታታይ ወራት የወር አበባ ከቀረ ሐኪምን ማማከር ያስፈልጋል።
የወር አበባ ከ45 ዓመት በፊት ከቆመም የባለሙያ ምክር መጠየቅ ያሻል።
15 ዓመት ሞልቷቸው የወር አበባ ማየት ያልጀመሩ ሴቶች ወደ ሕክምና መሄድ እንዳለባቸው ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ከእርግዝና ውጭ ሴቶች የወር አበባቸው እንዲቀር የሚያደርጉ 8 ምክንያቶች ቀጣዮቹ ናቸው።
1. ጭንቀት
ዶ/ር አሚራ እንደሚሉት ጭንቀት “የዘመኑ ወረርሽኝ” ሆኗል። የወር አበባ እንዲዘገይም ያደርጋል።
ጭንቀት አድሬናሊን ሆርሞን እንዲፈጠር ያደርጋል። ይህም ሰውነት አደጋ ሊመጣ ይችላል በሚል በተጠንቀቅ እንዲቆም የሚያደርግ ሆርሞን ነው።
አድሬናሊን መጠኑን ሲይልፍ የወር አበባ ያዛባል። የወር አበባ እንዲያጥር ወይም እንዲረዝም ሊያደርግም ይችላል። የወር አበባ ሕመም እንዲበረታ ምክንያትም ነው።
በአራት ሳምንታት ዑደት ውስጥ ሁለት ጊዜ የወር አበባ እንዲመጣም ያደርጋል።
የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ እና በመተንፈስ ሆርሞኑን ለመቆጣጠር መሞከር እንደሚቻል ይመከራል።
እነዚህ ውጤታማ ካልሆኑ ደግሞ የአእምሮ ሕመም እና የስሜት መዛባትን ለመቆጣጠር የሚውለው የሥነ ልቦና ሕክምና (cognitive-behavioural therapy) እንደ አማራጭ ይወሰዳል።
2. ከመጠን ያለፈ መክሳት
ድንገተኛ እና ከፍተኛ የሆነ የሰውነት መጠን መቀነስ ከማሕጸን እንቁላል የሚለቀቅበት ሒደት (ovulation) እንዲዛባ ያደርጋል።
ሰውነት ከሚፈለገው በታች ወይም ጤናማ ባልሆነ መንገድ ሲቀንስ፣ ማስተካከል የሚቻልበትን መንገድ የሚያማክሩ የሥነ ምግብ ባለሙያዎች አሉ።
አመጋገብ ተዛብቶ የሰውነት መጠን ሲቀንስ ወይም የተዛባ አመጋገብ ሕመም (anorexi) ሲከሰት የሥነ ልቦና ባለሙያ ማማከር ያሻል።

3. ከመጠን ያለፈ ውፍረት
ከመጠን ያለፈ ውፍረት ሰውነት ከልክ በላይ ኤስትሮጅን እንዲያመርት ያደርጋል።
ይህ የሴቶችን ሥነ ተዋልዶ ከሚቆጣጠሩ ሆርሞኖች አንዱ ነው። መጠኑ ሲጨምር ደግሞ የወር አበባ የሚታይበትን ፍጥነት ይጨምራል። አንዳንዴም የወር አበባ እንዲቀር ያደርጋል።
የሰውነት ክብደት እና ቁመት ምጣኔያቸው ከ30 በላይ የሆነ ሴቶች ከሥነ ምግብ ባለሙያዎች ምክር መጠየቅ አለባቸው።
4. ከልክ ያለፈ ስፖርት
ከመጠን በላይ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የወር አበባን የሚቆጣጠረውን የሰውነት ሆርሞን ያዛባል።
ከልክ በላይ የሰውነትን ስብ ማጣትም ከማሕጸን እንቁላል የሚለቀቅበትን ሒደት ያዛባል።
ፕሮፌሽናል ስፖርተኞች ሰውነታቸውን መቆጣጠር እና መከታተል የሚችሉበት መንገድ ተቀምጦላቸዋል።
5. ፖሊሲስቲክ ኦቫሪ ሲንድረም
እንቁላል የሚያድግበት የማሕጸን ክፍል ላይ የሚፈጠር የሆርሞን መዛባት (Polycystic Ovary Syndrome ወይም PCOS) መቀነስ ከማሕጸን እንቁላል የሚለቀቅበትን ሒደት ያውካል።
የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የጤና ተቋም እንደሚለው ከአሥር ሴቶች አንዷ ይህ እክል ይገጥማታል። ይህም 33 በመቶ የወር አበባ እንዲቀር ምክንያት ይሆናል።

6. ማረጥ ወይም ያለ ጊዜው ማረጥ
ከእርግዝና እና ጡት ማጥባት ውጭ ተፈጥሯዊ የሆነ የወር አበባ መቅረት ምክንያት ማረጥ ነው።
ወደ ማረጥ እየተቃረቡ ያሉ ሴቶች የኤስትሮጅን ሆርሞን መጠናቸው ይቀንሳል። ከማሕጸን እንቁላል የሚለቀቅበትንን መጠን እንዲቀንስም ያደርጋል።
ማረጥ የሚከሰተው ከ45 እስከ 55 ባለው ዕድሜ ቢሆንም፣ ከ40 ዓመት በፊት ቅድመ ማረጥ ሊከሰትም ይችላል።
7. የእርግዝና መከላከያ
አንዳንድ የእርግዝና መከላከያ እንክብሎች ወይም መርፌ የወር አበባ እንዲቀር ምክንያት ይሆናሉ።
የወሊድ መከላከያ መውሰድ ካቆሙ በኋላም ሰውነት ወደ መደበኛው የወር አበባ ዑደት ለመመለስ ጊዜ ይወስድበታል።

8. የተለያዩ ሕመሞች
ዘለግ ላለ ጊዜ የቆዩ ሕመሞች የወር አበባ እንዲቀር ያደርጋሉ። የስኳር ሕመም እና የሆርሞን መዛባት (hyperthyroidism) እንደ ምሳሌ ይጠቀሳሉ።
ለአእምሮ ሕመም የሚሰጡ መድኃኒቶች (antipsychotics)፣ የካንሰር ሕክምና (chemotherapy)፣ የድባቴ መድኃኒቶች (antidepressant) እንዲሁም የደም ግፊት እና አልርጂን ለማከም የሚወሰዱ መድኃኒቶች የወር አበባ መቅረትን ከሚያስከትሉ መካከል ይገኙበታል።