
ከ 9 ሰአት በፊት
የሰው ልጅ ምድር በምትባለው ፕላኔት ላይ መኖር ከመጀመሩ በፊት የሆነው ምንድን ነው? ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ከ30 አገራት ሳይንቲስቶች ተሰባስበዋል።
በአሜሪካ ደቡብ ዳኮታ በሚገኝ አንድ ቤተ ሙከራ ውስጥ የሳይንስ ሊቃውንት ለአንድ ትልቅ ሳይንሳዊ ጥያቄ መልስ እየፈለጉ ነው።
ጥያቄው አጽናፈ ዓለማት ወይንም ዩኒቨርስ ለምን ተፈጠሩ? የሚል ነው።
ከበርካታ ዓመታት ጀምሮ የጃፓን ሳይንቲስቶች ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሩጫ ላይ ሲሆኑ ከፍተኛ እመርታ አሳይተዋል።
አጽናፈ ዓለም እንዴት እንደተፈጠረ አሁን ያለው ንድፈ ሃሳብ በዙሪያችን የምናያቸው ፕላኔቶች፣ ከዋክብት እና ጋላክሲዎች መኖራቸውን ሊያስረዳ አይችልም።
የአሜሪካ እና የጃፓን ሳይንቲስቶች ቡድን መልስ ለማግኘት ተስፋ በማድረግ ኒውትሪኖ የሚባል ንዑስ የአቶሚክ ቅንጣትን የሚያጠኑ መመርመሪያዎችን በመገንባት ላይ ናቸው።
በአሜሪካ የሚመራው ዓለም አቀፍ ትብብር መልሱ ‘ዱን’ ሲል በሰየመው ከመሬት በታች ከሚገኝ ስፍራ እንደሚገኝ ተስፋ አድርጓል።
ሳይንቲስቶቹ ከመሬት በታች 1,500 ሜትር ወደ ሦስት ግዙፍ የመሬት ውስጥ ዋሻዎች ቆፍረዋል።
የግንባታ ሠራተኞች እና ቡልዶዘሮቻቸው በንፅፅር ትንሽ የፕላስቲክ መጫወቻዎች ነው የሚመስሉት።
የዚህ ተቋም የሳይንስ ዳይሬክተር ዶ/ር ጃሬት ሃይሴ ግዙፎቹን ዋሻዎች “የሳይንስ ካቴድራሎች” በማለት ይገልጿቸዋል።
ዶ/ር ሃይሴ እነዚህን ዋሻዎች በሳንፎርድ የመሬት ውስጥ ምርምር ተቋም በመገንባት ለአስር ዓመታት ያህል ሠርተዋል።
በምድር ላይ ከሚንከላወስ ፍጥረት ከሚሰማ ጫጫታ እና ጨረሮች ሙሉ በሙሉ ዘግተውታል።
አሁን ‘ዱን’ ለሚቀጥለው ደረጃ ዝግጁ ነው።
“ለምን በምድር ላይ ኖርን የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ፍላጎት ባላቸው ከ35 አገራት የተውጣጡ ከ1,400 በላይ የሳይንስ ሊቃውንት በሚሠሩ መሳሪያዎች ስለ ዩኒቨርስ ያለንን ግንዛቤ የሚቀይር መሳሪያ ለመሥራት ተዘጋጅተናል” ብሏል።

አጽናፈ ዓለም (ዩኒቨርስ) ሲፈጠር ሁለት ዓይነት ቅንጣቶች ተፈጠሩ።
የትኛው ከዋክብት፣ ፕላኔቶች እና በዙሪያችን ያሉ ሁሉም ነገሮች የተፈጠሩት ከዚህ ቁስ አካል (matter) ነው።
በዚያው ልክ ደግሞ ፍጹም ተቃራኒ የሆኑት ፀረ ቁስ አካላት አሉ።
በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ሁለቱ ከትልቅ የኃይል ፍንዳታ በስተቀር ምንም ነገር ሳይተዉ፣ አንዳቸው ሌላኛቸውን ማጥፋት ነበረባቸው።
እና እኛ በዚያ ምክንያት ተገኝተናል የሚል እሳቤ አለ።
የሳይንስ ሊቃውንት ቁስ አካል አሸንፎ ለምን እኛ መገኘት እንደቻልን መልሱ የሚገኘው ኒውትሪኖ የተባለውን ቅንጣት እና ፀረ-ኒውትሪኖን በማጥናት ላይ ነው ብለው ያምናሉ።
በኢሊኖይ ጥልቅ መሬት ውስጥ በሚገኘው ላብራቶሪ 800 ማይሎች ርቆ ሳውዝ ዳኮታ ወደሚገኘው መሳሪያ ሁለቱንም ቅንጣቶች የያዘ ጨረር ይተኩሳሉ።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ኒውትሪኖች እና ፀረ-ኒውትሪኖች በሚጓዙበት ጊዜ በትንሽ በትንሹ ይቀየራሉ።
የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህ ለውጦች በኒውትሪኖስ እና ለፀረ-ኒውትሪኖስ የተለያዩ መሆን አለመሆናቸውን ማወቅ ይፈልጋሉ።
ለዚህ ምላሽ የሚያገኙ ከሆነ ለምን ቁስ አካል እና ፀረ-ቁስ አካል እርስ በርሳቸው እንደማይጠፋፉ ምላሽ ሊሰጣቸው ይችላል።
ዱን ከሠላሳ አገሮች የተውጣጡ 1,400 ሳይንቲስቶችን ያሳተፈ ዓለም አቀፍ ትብብር ነው።
ከእነርሱ መካከል ከዩናይትድ ኪንግደም ሰሴክስ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ዶ/ር ኬት ሻው፣ በሂደት ላይ ያሉ ምርምሮች ስለ አጽናፈ ዓለም እና የሰው ልጅ ስለራሱ ያለውን አመለካከት ለመረዳት “መሠረታዊ ግኝቶች” እንደሚሆኑ ይናገራሉ።
“እነዚህን ትልልቅ ጥያቄዎች ለመመለስ በቴክኖሎጂው፣ በምህንድስና፣ በኮምፒዩተር ሶፍትዌር ክህሎት አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ መገኘታችን በጣም የሚያስደስት ነው” ብለዋል።

የጃፓን ሳይንቲስቶች በበኩላቸው ለተመሳሳይ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የሚያብረቀርቁ ወርቃማ ሉሎችን እየተጠቀሙ ነው።
በደቡብ ዳኮታ 9,650 ኪሜ ርቀት ላይ የሚገኘውን ካቴድራል ላይ በትይዩ የሚያንጸባርቀው ይህ ወርቃማ ሉል በድምቀቱ እና በአብረቅራቂነቱ ለሳይንስ እንደ ቤተ መቅደስ ነው።
ሳይንቲስቶች ኒውትሪኖን መለየት የሚያስችል አሁን ካለው ሃይፐር ኬ (Hyper-K) የገዘፈ እና የተሻለ ሱፐር ኬ (Super-K) የተሰኘ መሣሪያ እየገነቡ ነው።
በጃፓን የሚመራው የተመራማሪዎች ቡድን ከአሜሪካው ፕሮጀክት በበርካታ ዓመታት ቀደም ብሎ ከሦስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የኒውትሪኖ ጨረርን ለመሞከር ዝግጁ ነው።
ልክ እንደ ዱን ሁሉ ሃይፐር ኬም ዓለም አቀፍ ትብብር ነው።
ከለንደን ኢምፔሪያል ኮሌጅ የመጡት ዶ/ር ማርክ ስኮት ቡድናቸው ስለ አጽናፈ ዓለም አመጣጥ ለመረዳት ከመቼውም ጊዜ የላቀ ግኝቶች ላይ ለመድረስ መቃረቡን ያምናሉ።
ሁለቱንም ሙከራዎች አንድ ላይ ማስኬድ ማለት ሳይንቲስቶቹ እርስ በርስ የበለጠ ይማማራሉ ማለት ነው። ነገር ግን “መጀመሪያ እዚያ መድረስ እፈልጋለሁ!” ብለዋል ዶ/ር ስኮት።
ለዱን ፕሮጀክት የሚሠሩት የኩዊን ሜሪ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶ/ር ሊንዳ ክሪሞኔሲ፣ በጃፓን የሚመራው ቡድን መጀመሪያ ግኝቶቹ ላይ መድረስ ከቻለ ምን እየተከናወነ እንዳለ ሙሉ መረጃ ላይሰጥ ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
“የዘር ጉዳይ አለ፣ ኒውትሪኖ እና ፀረ-ኒውትሪኖች የተለየ ባህሪ ካላቸው ልንረዳቸው የሚገቡት ሁሉም ንጥረ ነገሮች ሃይፐር ኬ ገና የሉትም።”
የተመራማሪዎቹ ፉክክር ተጀምሮ ሊሆን ይችላል፤ ግን የመጀመሪያው ውጤት የሚጠበቀው ከጥቂት ዓመታት በኋላ ነው።
የሰው ልጅ ኅልው ከመሆኑ በፊት፣ መጀመሪያ ላይ የሆነው ነገር ምንድን ነው የሚለው አሁንም እንቆቅልሽ ሆኖ ይቆያል፤ ለጊዜው።