ተቃውሞ እያደረጉ ያሉ ተማሪዎች

ከ 9 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር በውጭ አገሮች የሚገኙ ኤምባሲዎቹ የተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጡ አዘዘ።

የአመልካቾችን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች የማጣራት ሂደት ለማስፋት በዝግጅት ላይ እንዳለ ያስተዋወቀው አስተዳደሩ፤ ለተማሪዎች የቪዛ ቀጠሮ እንዳይሰጥ በጊዜያዊነት አግዷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማርኮ ሩቢዮ መልዕክት በሰፈረበት ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ በተላከ ማስታወሻ ላይ እገዳው “ተጨማሪ መመሪያ እስኪወጣ ድረስ” ይቆያል ተብሏል።

አስተዳደሩ የተማሪዎች አመልካቾች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾችን የማጣራት ስራ አጠናክሮ የሚሰራ ሲሆን ይህም በኤምባሲዎች እና በቆንስላ ጽ/ቤቶች ላይ ትልቅ አንድምታ እንደሚኖረው ተገልጿል።

ትራምፕ የግራውን ርዕዮተዓለም እየተከተሉ ናቸው ካሏቸው ታዋቂ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ የተወሰነ ውሳኔ ነው።

ዩኒቨርስቲዎች በግቢው ውስጥ ጸረ ሴማዊነቶች እንዲሰፍን አስችለዋል እንዲሁም የተማሪዎች የቅበላ ፖሊሲዎቻቸው አድሎአዊነት አለው ሲሉ ትራምፕ ተችተዋቸዋል።

የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ የተመለከተው የመንግሥት የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ማሰታወሻ ቀጠሮዎች ላልተሰጣቸው አመልካች ተማሪዎች አዲስ ቀጠሮ እንዳይያዝላቸው ነገር ግን ቀጠሮ የተሰጣቸው ተማሪዎች ግን በዚያው መሰረት እንዲስተናገዱ ይላል።

በተጨማሪም የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቶች ሁሉም የተማሪ ቪዛ አመልካቾች የማህበራዊ ሚዲያ ገጾቻቸው እንዲጣራ እና እንዲፈተሽ የሚያደርግ ዝግጅት እያደረገ እንደሆነም ይጠቅሳል።

ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ትምህርታቸውን ለመማር የሚፈልጉ የውጭ አገር ተማሪዎች ቪዛ ከመሰጠቱ በፊት በአገራቸው በሚገኝ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ቃለ መጠይቆችን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር።

የውጭ አገር ተማሪዎቹ ለትምህርት ከፍተኛውን ክፍያ ስለሚያደርጉ ተቋማቱ ከፍተኛውን ገቢያቸውን የሚያገኙት በዚህ መልክ ነበር።

“ወደ አገራችን የሚመጡ ተማሪዎች እነማን እንደሆኑ የማጣራት ሂደቱን በቁም ነገር የምንወስደው እና ያንን ማድረጋችንን እንቀጥላለን” ሲሉ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ታሚ ብሩስ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

የትራምፕ አስተደዳደር ለዩኒቨርስቲዎች የሚሰጠውን በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላሮችን በማገድ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ቪዛዎችን በመሰረዝ ተማሪዎችን ከአገር ለማስወጣት ተንቀሳቅሷል።

እነዚህ የአስተዳደሩ አብዛኛው እርምጃዎች በፍርድ ቤት ታግደዋል።

አንዳንዶቹ የአሜሪካ ዩኒቨርስቲዎች በግቢያቸው ውስጥ በሚደረገው የፍልስጤም ድጋፎች ለጸረ-ሴማዊነት በር ከፍተዋል ሲል ዋይት ሃውስ ከሷቸዋል።

ዩኒቨርስቲዎች በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር በነጻነት ሃሳብን የመግለጽ መብቶችን ለመጣስ እየሞከረ ነው ሲሉ ይወቅሳሉ።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ታዋቂው ዩኒቨርስቲ ሐርቫርድ የውጭ አገር ተማሪዎችን እንዲሁም ተመራማሪዎችን እንዳይቀበል በሚል ፈቃዱን ቢሰርዙም ይህ ፖሊሲያቸው በፌደራል ዳኛ ታግዷል።

ይህ በሐርቫርድ ላይ የጣሉት ውሳኔ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ሩብ የሚሆኑት ተማሪዎቹ ከውጭ አገር የሆኑት ተቋሙ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጎዳ ይችላል ተብሏል።