በሺህዎች የሚቆጠሩ ጋዛዊያን እርዳታ ማሰራጫ ጣቢያው ሲገቡ
የምስሉ መግለጫ,በሺህዎች የሚቆጠሩ ጋዛዊያን እርዳታ ማሰራጫ ጣቢያው ሲገቡ

ከ 6 ሰአት በፊት

በጋዛ በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማዊያን በአሜሪካ እና አስራኤል በሚደገፍ የረድኤት ድርጅት እርዳታ ማከፋፈያ ሥራ በጀመረ በሁለተኛ ቀኑ አጨናንቀውታል።

ተንቀሳቃሽ ምስሎች በደቡባዊ ራፋ የተሰበሰበ ሕዝብ ‘የጋዛ ሂማኒቴሪያን ፋውንዴሽን’ ቅጥር ግቢን ጥሰው በወደቀ አጥር ሲርመሰመሱ አሳይተዋል።

ረድኤት ድርጅቱ እንዳለው እርዳታ ለማግኘት የመጡ ሰዎች ብዛት ያላቸው በመሆናቸው የቡድኑ አባላት ለቅፅበት ወደ ኃላ አፈግፍገው ነበር።

የእስራኤል ጦር በአቅራቢያ የነበሩ ወታደሮች የማስጠንቀቂያ ጥይት መተኮሳቸውን ተናግሯል።

በታጠቁ የአሜሪካ የደኅንነት ቅጥረኞች የሚታጀበው ድርጅቱ የመንግሥታቱ ድርጅትን በማለፍ በጋዛ ዋናነት የእርዳታ አቅራቢ ለመሆን አልሟል።

በጋዛ ረሃብ እያንዣበበ ሲሆን እስራኤል ለ11 ሳምንታት ጥላው የነበረውን እገዳ በቅረቡ አለዝባለች።

የመንግሥታቱ ድርጅት በራፋ የታየውን እርዳታ ፈላጊ ሕዝብ ትዕይንት “ልብ ሰባሪ” ያለው ሲሆን፤ አፋጣኝ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው 2.1 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ ለማድረስ ዝርዝር እቅድ መንደፉን ተናግሯል።

የመንግሥታቱ ድርጅት እና በርካታ የረድኤት ድርጅቶች ከፋውንዴሽኑ ጋር ለመተባበር ፈቃደኛ አይደሉም። ለዚህም ምክንያት ሲያቀርቡ ድርጅቱ የሰብዓዊነት መርሆችን የሚቃረን እና እርዳታን እንደ መሳሪያ እንደሚጠቀምበት ያሳያል ብለዋል።

ድርጅቱ መንቀሳቀስ የማይችሉትን ከእርዳታው ያገለለ ነውም ሲሉ ያስጠነቀቁ ሲሆን፤ ይህም ለተጨማሪ መፈናቀል ምክንያት ይሆናል ተብሏል።

ድርጅቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ለጉዳት ይዳርጋል፣ እርዳታን ለፖለቲካ እና ወታደራዊ ዓላማ ያውላል እንዲሆም በመላው ዓለም ታይቶ የማይታወቅ የእርዳታ አቅርቦት ስርዓት አለው በሚል አስጠንቅቀዋል።

ሀማስ የእርዳታ አቅርቦትን እየዘረፈ ነው የምትለው እስራኤል አሁን ካለው የአቅርቦት ስርዓት ሌላ አማራጭ አስፈላጊ ነው ብላለች። ምንም እንኳ ሐማስ ዝርፊያውን ቢያስተባብልም።

‘ጋዛ ሂማኒቴሪያን ፋውንዴሽን’ ሰኞ ዕለት በጋዛ ሥራ መጀመሩን ያሳወቀ ሲሆን፤ በማሰራጫ ጣቢያው ለፍልስጤማዊያን እርዳታ እያደረስኩ ነው ብሏል።

ማክሰኞ ዕለት የእስራኤል እና ፍልስጤም መገናኛ ብዙኃን በታል አል ሱልጣን ጣቢያ ሰዎች እርዳታ ለማግኘት ተሰልፈው የሚያሳዩ ተመሳሳይ ምስሎችን አጋርተዋል።

ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ደግሞ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህፃናትን ጨምሮ የጣቢያውን ቅጥር ግቢ ጥሰው ሲገቡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል ይፋ ሆኗል። በምስሉ ከተኩስ ራሳቸውን ለመከላከል አንዳንድ ሰዎች ሲሮጡ እና ሲያጎነብሱ ይታያሉ።

የዓይን እማኞች ሰዎች የምግብ እሽጎችን እና ሌሎች እርዳታዎችን መውሰዳቸው ገልፀዋል። በአካባቢው የተመደቡ የእስራኤል ወታደሮች ደግሞ ተኩስ መክፈታቸውንም አክለው ተናግረዋል።

“ሁኔታው በጣም ከባድ ነበር። አንድ ጊዜ 50 ሰዎች ብቻ እንዲገቡ ነበር የፈቀዱት” ያሉ አንድ የዓይን እማኝ፤ “በመጨረሻም ትርምስ ተፈጠረ። ሰዎች የግቢውን በር ዘለው ገቡ፤ ሰዎችን አጠቁ፤ እናም ሁሉንም [እርዳታ] ወሰዱት” ብለዋል።

“በጣም የሚያሳፍር ነው” ሲሉ ያካሉት እማኙ፤ “በረሃብ በጣም እየተሰቃየን ነው። ሻይ ለማፍላት ትንሽ ስኳር እና የምንበላው ሽራፊ ዳቦ ነው የፈለግነው” ብለዋል።

አንድ ሴት በበኩሏ ረሃብ እና ድህነት “ሁሉንም ሰው ከአቅሙ በላይ” አድርጎት ነበር ብለዋል።

‘ጋዛ ሂማኒቴሪያን ፋውንዴሽን’ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ብዙዎች እንደሆኑ በመጥቀስ 462 ሺህ ምግብ የሚሆን ስምንት ሺህ የምግብ ሳጥኖችን ማከፋፈሉን ገልጿል።