
ከ 5 ሰአት በፊት
ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ ‘ገበያ መር’ የውጭ ምንዛሬ ማሻሻያ ከተደረገ በኋላ የዶላር ምንዛሬ128 በመቶ ገደማ ጭማሪ ሲያሳይ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በአሜሪካ የዶላር ምንዛሬ ላይ በአንድ ሳምንት የሰባት ብር ጭማሪ አድርጎ 131 ብር ደረሰ።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም. አዲስ የውጭ ምንዛሬ አስተዳደር ስርዓት ያስተዋወቀ ሲሆን፤ ያ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ሐምሌ 19/ 2016 አንድ የአሜሪካን ዶላር የመግዣ ዋጋ 57.48 ብር ነበር።
ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) እና ከዓለም ባንክ 10.7 ቢሊዮን ዶላር ብድር ለማግኘት በተደረገው ስምምነት መሰረት በገበያ ላይ የተመሠረተ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ በማድረግ ብሯን ማዳከሟ ይታወሳል።
ለአስርት ዓመታት መንግሥት በሚወስነው የውጭ ምንዛሪ የግብይት ሥርዓትን (ፊክስድ ፎሬይን ኤክስቸንጅ ማርኬት) ይመራ የነበረውን አሠራር በመቀየር በገበያ ፍላጎት የሚመራ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።
ተግባራዊ በተደረገም በአንድ ሳምት ብቻ የብር የመግዛት አቅም በ57 በመቶ መዳከሙ ይታወሳል።
ጭማሪውን ተከትሎ በወቅቱ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እና ቸርቻሪዎች የሸቀጦች እና የግብዓቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ መታየቱን ገልጸዋል።
አዲሱ ማሻሻያ ገቢራዊ ከመሆኑ በፊት አንድ የአሜሪካን ዶላር ግብይት 57.48 ብር የነበረ ሲሆን፤ ረቡዕ ግንቦት 20/2016 ዓ.ም. አንድ የአሜሪካን ዶላር 131 ብር የመግዣ ተመን ወጥቶለታል።
ቢቢሲ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ዳሸን ባንክ ዕለታዊ ምንዛሬዎችን የተመለከተ ሲሆን ሁለቱም ባንኮች የሳንቲም ልዩነት ብቻ አድርገው አንድ ዶላር 131 ብር ገደማ ለመግዛት ተመን አውጥተዋል።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለበርካታ ወራት አንድን የአሜሪካ ዶር 124 ብር ሲገዛ እና ሁለት ብር ጨምሮ ደግሞ ሲሸጥ የከረመ ቢሆንም፤ ካለፈው ሳምንት አጋማሽ በኋላ አራት ብር ጨምሮ 128 ብር ሲገዛ ቆይቷል።
ባንኩ በአንድ ሳምንት የሰባት ብር ጭማሪ በማድረግ አንድን የአሜሪካን ዶላር 131 ብር ገዝቶ 133 ብር እንደሚሸጥ አስታውቋል።
ዳሽን ባንክ በበኩሉ ግንቦት 20/2017 ዓ.ም. በድረ ገጹ ባወጣው ተመን አንድ የአሜሪካ ዶላር 131 ብር ከ80 ሳንቲም በመግዛት 134 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሚሸጥ ገልጿል።
ብሔራዊ ባንክ ለባንኮች የውጭ ምንሬ በጨረታ የሚሸጥ ሲሆን፤ ባለፈው ሳምንት በስድስተኛው ዙር ያቀረበውን 50 ሚሊዮን ዶላር 14 ባንኮች በአማካኝ 133 ብር ከ17 ሳንቲም መውሰዳቸውን አስታውቋል።
በአምስተኛው ዙር ጨረታ ደግሞ 60 ሚሊዮን ዶላር ለጨረታ ቀርቦ 132 ብር ከ90 ሳንቲም አማካኝ ዋጋ ተሽጧል።
መንግሥት ብሩን በማዳከም ከትይዩው ገበያ ጋር ለማመጣጠን እየሰራ እንዳለ ቢናገርም ልዩነቱ እየጨመረ መጥቷል። ባለፉት ሳምንታት በመደበኛ ገበያው የአንድ ዶላር ዋጋ 124 በነበረበት ወቅት በትይዩ ገበያው ደግሞ 154 ሲመነዘር ነበር።
ብሔራዊ ባንክ ለአስርት ዓመታት በመንግሥት ቁጥጥር ስለነበረውን ማሻሻያ ሲያብራራ ከዚህ ቀደም የነበረው አሠራር “ጠንካራ መሠረት የሌለው” ትይዩ ገበያን የፈጠረ በመሆኑ፤ ዶላር ከይፋዊ የግብይት ተመን እጥፍ በሆነ ዋጋ ለግብይት እንዲቀርብ መንገድ የከፈተ መሆኑን ገልጿል።
በዚህ ምክንያት አገሪቱ በውጭ ምንዛሪ እጥረት ስትፈተን ነበር ያለው ባንኩ፤ ይህም በዋነኛነት መሰናክል የሆነው ለግል ዘርፉ እንደሆነ ጠቅሶ “ጥቂት ሕገ ወጥ አካሎች እና ደላሎች የማይገባቸውን ጥቅም ሲያጋብሱ ነበር” ብሏል።
የውጭ ምንዛሪ ተመንን በገበያ ላይ እንዲመሠረት ክፍት ማድረግ የአገራቱን የመገበያያ ገንዘብ በማዳከም ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን የበለጠ ውድ ያደርጋቸዋል።
በዚህም የተነሳ እንደ ምግብ፣ ነዳጅ እና መድኃኒቶች ዋጋን በማናር በነዋሪዎች አብዛኛውን መሠረታዊ የሚባሉ ሸቀጦች በአመብዛኛው ከውጭ ለሚያስገቡ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ነዋሪዎች ዋጋን እንደሚንር እና በንግድ ተቋማት ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር ይታመናል።
የማሻሻያውን ጫና ለመቋቋም ዝቅተኛ ደመወዝ ላላቸው ሠራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እንደሚደረግ መንግሥት አስታውቆ ነበር።
የብሔራዊ ባንክ የገንዘብ ፖሊሲ ኮሚቴ ባለፈው ታኅሳስ ዓመታዊ የዋጋ ግሽበት እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሷል።