የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

ከ 4 ሰአት በፊት

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ በአነጋጋሪ ሁኔታ ለኢትዮጵያውን “የ34ተኛ ዓመት የነጻነት በዓል” የመልካም ምኞች መግለጫ አስተላለፉ።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋዊ ድረ ገጽ ላይ የወጣው የማርኮ ሩቢዮ መግለጫ የተላለፈው ትናንት ማክሰኞ በግንቦት 20 ዋዜማ ነው።

ቢቢሲ በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ ከሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ምላሽ ባያገኝም፤ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ በይፋዊ ገጹ ላይ የወጣው ጽሁፍ መነሳቱን ቢቢሲ ተመልክቷል።

በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ውስጥ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ሩቢዮ ማክሰኞ ግንቦት 19/2017 ዓ.ም. ያወጡት መግለጫ፤ “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን” የሚል ስያሜን የያዘ ነው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው “በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ስም ለ34ተኛው የነጻነት ክብረ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ [መልካም ምኞቴን] አቀርባለሁ” ብለዋል።

አሜሪካ እና ኢትዮጵያ ክፍለ ዘመን የተሻገረ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እንዳላቸው ያስታወሰው መግለጫው፤ ዋሽንግተን እና አዲስ አበባ ባሏቸው “የጋራ ፍላጎቶች” ዙሪያ ለመሥራት ሀገራቸው ዝግጁ መሆኗንም ይገልጻል።

“ለኢኮኖሚ ዕድገት፤ ንግድ እና ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ” እንዲሁም “በንግግር ሰላምን ማሳደግ” የሁለቱ ሀገራት የጋራ ጉዳዮች ተብለው የተጠቀሱ አጀንዳዎች ናቸው።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ መልዕክት፤ “ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቡ መልካም ብሔራዊ በዓል ትመኛለች” ሲል መልካም ምኞትን በድጋሚ በመግለጽ ያበቃል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ያወጡት የመልካም ምኞት መግለጫ
የምስሉ መግለጫ,የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ያወጡት የመልካም ምኞት መግለጫ

ይህ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ ግንቦት 20ን “የነጻነት በዓል” ብሎ መጥቀሱ ያልተለመደ ነው።

በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አንቶኒ ብሊንከን ባለፈው ዓመት ለግንቦት 20 ባስተላለፉት መልዕክት ዕለቱን ለማመልከት የተጠቀሙት “የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቀን” እና “በዓል” የሚሉትን አገላለጾች ተጠቅመው ነበር።

የአሁኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሩቢዮ፤ ኤርትራ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. የነጻነት በዓሏን ባከበረችበት ዕለትም በተመሳሳይ የመልካም ምኞች መግለጫ አውጥተው ነበር።

በዚህ መልዕክታቸው፤ “በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ስም በዓለም ዙሪያ የምትገኙ ኤርትራውያንን እንኳን ለ34ተኛው የኤርትራ ነጻነት ክብረ በዓል እንኳን አደረሳችሁ እላለሁ” የሚል የመልካም ምኞች አስተላልፈዋል።

በኢህአዴግ ዘመነ መንግሥት በድምቀት ይከበር የነበረው ግንቦት 20፤ ይጠቀስ የነበረው የደርግ መንግሥት የተገረሰሰበት የድል በዓል ቀን በሚል ነው። በመንግሥት ደረጃ የሚከበረው ይህ ቀን ሲታሰብ ሥራ እና ትምህርት ጭምር ዝግ ይደረግ ነበር።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት በዓሉ መከበር ቢቀጥልም አከባበሩ መቀዛቀዝ ታይቶበታል።

በዘንድሮው ዓመት ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተለየ ሥራ እና ትምህርት ዝግ አልተደረገም። እንደ አዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ያሉ ተቋማት በዛሬው ዕለት ሥራ ዝግ እንዳልሆነ ለሠራተኞቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

በዘንድሮ በዕለቱ ዝግ ያልተደረገው የሕዝብ በዓላትን እና የእረፍት ቀንን ለመወሰን የተዘጋጀ አዲስ አዋጅ ሰኔ 2016 ዓ.ም. መጽደቁን ተከትሎ ነበር። ግንቦት 20 እስካለፈው ዓመት ድረስ ሲከበር የነበረው ምንም ዓይነት ሕጋዊ እውቅና ሳይሰጠው ነው።

እስካለፈው ዓመት ድረስ የሀገሪቱን ብሔራዊ በዓላት በተመለከተ ጥቅም ላይ ሲውል የነበረው ሕግ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተደደር ደርግ በ1967 ዓ.ም. ያወጣው አዋጅ ነው።

ኢህአዴግ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ በ1988 ዓ.ም. በዚህ አዋጅ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አድርጓል።

ኢህአዴግ በማሻሻያው የድል (የአርበኞች) ቀንን በፊት ይከበርበት ከነበረው መጋቢት 28 ወደ ሚያዝያ 27 ቀን ቀይሯል። ይህ የአዋጅ ማሻሻያም ቢሆን ግን ግንቦት 20ን በብሔራዊ በዓልነት አላካተተም።

ባለፈው ዓመት የወጣው አዲሱ አዋጅም በዘረዘራቸው ብሔራዊ በዓላት ውስጥ ይህ ቀን አልተጠቀሰም። ከዚህ ባሻገር አዋጁ “ከዚህ አዋጅ ጋር የሚቃረን ማንኛውም”፤ “ልማዳዊ አሠራር በዚህ አዋጅ በተሸፈኑ ጉዳዮች ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም” የሚል አንቀጽ በማካተቱ በአመላካች መንገድ የግንቦት 20ን አከባበር አስቀርቷል።