
ከ 1 ሰአት በፊት
የዓለማችን ቁጥር አንድ ቢሊየነር እና በአሜሪካ እየተካሄደ ያለው ለውጥ ቁልፍ ሰው ኢሎን መስክ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን የግብር እፎይታ መተቸቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
የቅርብ አጋሩ ትራምፕ “ትልቅና ውብ” ሲሉ የጠሩትን የትሪሊዮን ዶላር ግብር መስክ ተችቷል።
ባለፈው ሳምንት የአሜሪካ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የግብር እፎይታ በማጽደቅ የአሜሪካን የመከላከያ ወጪ ለመጨመር ቃል ገብቷል። ረቂቁ በቀጣይ ወደ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት) ያመራል።
ቢልየነሩ የቴክኖሎጂ ሰው መስክ ለቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ እንደተናገረው በፕሬዝዳንት ትራምፕ ዕቅድ ተበሳጭቷል።
የመንግሥትን ወጪ ለመቀነስ የሠራውን ሥራ “የሚያጣጥል” እንደሆነና በዚህም “እንዳዘነ” ገልጿል።
መስክ ለውጪ አገራት የሚላክ እርዳታን ጨምሮ የተለያዩ የወጪ ቅነሳዎች አድርጓል። ከዚህ ኃላፊነቱ ከመራቁ በተጨማሪ ለፖለቲካ የሚያወጣውን ወጪ እንደሚቀንስም ገልጿል።
“እውነቱን ለመናገር ከፍተኛ ወጪ ያለው ረቂቅ መቅረቡ አስከፍቶኛል። የትራምፕ ዕቅድ የበጀት ጉድለቱን የሚጨምር እንጂ የሚቀንስ አይደለም” ብሏል።
የቀረበው ረቂቅ የበጀት ጉድለት እንደሚጨምር ተገልጿል። በየዓመቱ የአሜሪካ መንግሥት ወጪ ከገቢው በላይ የ600 ቢሊዮን ዶላር ልዩነት እንዲኖረው ያደርጋልም ተብሏል።
መስክ ረቂቁ “የዶጅን [የሚመራው መሥሪያ ቤት] ሥራ የሚያራክስ ነው” ሲልም ነቅፏል።
“ዕቅዱ ወይም ትልቅ ወይ ውብ ይሆናል። ሁለቱንም መሆን የሚችል አይመስለኝም” ብሏል።
በግብር ዕቅድ በሪፐብሊካኖች መካከል ያለውን ልዩነት የመስክ ተቃውሞም ያስተጋባል። ረቂቁ ብዙ ተቃውሞ ቀርቦበት ነው ያለፈው።
እአአ በ2017 የቀረቡ የግብር እፎይታዎችን የሚሽር ሲሆን ለመከላከያ ከፍተኛ የበጀት ጭማሪ የሚያስገኝ ይሆናል። ስደተኞችን ከአሜሪካ ለማባረርም ገንዘብ ፈሰስ ይደረግበታል።
ከ250 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለትራምፕ የለገሰው መስክ ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሱን ከትራምፕ እያራቀ መጥቷል።
መስክ ከዶጅ ራሱን በማራቅ የተስላ መሪነቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ለፖለቲካ የሚያወጣውን ገንዘብ እንደሚቀንስ ተናግሯል።
መስክ የዶጅ ኃላፊ ሲሆን ተስላ የኤሌክትሪክ መኪና የገበያ ድርሻው አሽቆልቁሏል። ከፍተኛ ተቃውሞም ገጥሞታል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የፌደራል መንግሥት ሠራተኞችን ማባረር እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ ተራድኦ ሥራዎችን ማቋረጥ መስክን አስተችቶታል።
መስክ በበኩሉ “መደረግ ያለበትን ነው ያደረግኩት” ሲል አስተባብሏል።