
ከ 5 ሰአት በፊት
ጓደኛሞቹ ኒኮል ፋራጅ እና ዴላኒ ዶኒ ከኮሌጅ ከተመረቁ በኋላ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ ተከራይተው መኖር የጀመሩት። ነገር ግን በጤና መጓደል ምክንያት ሕይወታቸውን የሚያውክ ችግር ይገጥመናል ብለው አስበው አያውቁም።
ሎስ አንጀለስ ወደሚገኘው አዲሱ ቤታቸው ከገቡ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ነው የመተንፈስ ችግር የገጠማቸው። ዕድሜያቸው ገና በሃያዎቹ ቢሆንም ከፍተኛ ራስ ምታት፣ እንቅልፍ ማጣት እና ድካም ወጥሮ ያዛቸው።
“የተመረዝኩ ያህል ነው የተሰማኝ” ስትል ዴላኒ ለቢቢሲ ትናገራለች። “በአራት ቀናት ውስጥ የሁለት ሰዓታት እንቅልፍ ባገኝ ነው። በጣም ከባድ ነው” ትላለች።
መጀመሪያ ሰሞን ሕመማቸው ከጭንቀት የመነጨ መስሏቸው ነበር።
ወጣቶቹ ሴቶች ቀስ በቀስ እየተመረዙ እንደሆነ አልገባቸውም። የሚኖሩበት ቤት የበሰበሰ ግድግዳ እና ጣራ እየተስፋፋ መጥቷል።
የቤታችን ግድግዳ ላይ የሚፈጠር መበስበስ እና መሻገት ለጤና እጅግ ጎጂ ነው።
“ለሻጋታ መጋለጥ ለሳንባችን ከፍተኛ ጠንቅ ነው” ይላሉ ዶ/ር አንዲ ዊታሞር ናቸው። በዩናይትድ ኪንግደም የአስም እና የሳንባ የእርዳታ ድርጅት የክሊኒክ ባለሙያ ናቸው።
“የአተነፋፈስ ችግር ያመጣል። አለርጂ ሊፈጥር ይችላል። አስም ያስከትላል።”

በሻጋታ ምክንያት የሚከሰት ቶክሲን የተባለ መርዛማ ኬሚካል ጤና ላይ ጉዳት የሚያስከትል ሲሆን፣ የመተንፈሻ አካላትን ከመጉዳቱም በላይ ለካንሰርም ሊያጋልጥ ይችላል ይላል የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ።
የቤት ውስጥ ግድግዳ ላይ የሚፈጠር ሻጋታ ገዳይ መርዝ የማመንጨት ኃይል አለው።
“አስም አሁንም ገዳይ በሽታ ነው። ሰዎች ሻጋታ እና ሌሎች ቆሻሻዎች ባሉበት ቦታ የሚኖሩ ከሆነ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ ላይ ይወድቃሉ” ይላሉ ዶክተሯ።
ኒኮል ከመኝታ ቤቷ ጣራ ላይ የውሃ ጠብታ ስትመለከት ነው ጉዳዩ የገባት። ሁለቱ ሴቶች ቤታቸውን መፈተሽ ሲጀምሩ ግድግዳ እና ጣራቸው በሻጋታ ተሞልቷል።
“መጀመሪያ ሰሞን የበሰበሰው ክፍል አይታይም ነበር። ቀስ በቀስ ቤቱን እየወረረው ነበር” ትላለች ኒኮል።

ሻጋታ ምንድነው?
በእርጥበት ምክንያት ግድግዳ እና ጣራ አሊያም ኮርኒስ ሲበሰብስ የሚከሰት ነው። በቅዝቃዜ ምክንያት የሚከሰተው ይህ መበስበስ በዓይን የማይታዩ ፈንገሶች ይፈጥራል።
ሻጋታ መስፋፋት ሲጀምር ጠቆር ያለ፣ ነጭ አሊያም አረንጓዴ ቀለም ይፈጥራል። በተለይ በመኝታ ቤት፣ በመታጠቢያ ክፍል እንዲሁም በኩሽና አካባቢ ሊስፋፋ ይችላል። እየተንሰራፋ ሲመጣ ሽታው የሚቀመስ አይደለም።
በአሜሪካ እና በአውሮፓ 47 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ሻጋታ አለባቸው ይላል በአውሮፓውያኑ 2013 የተሠራ ጥናት።
ነገር ግን ትሮፒካል ቀጣና ውስጥ በሚገኙ ሀገራት ብዙ ጥናት ባይሠራም በሕንድ እና በታይላንድ በሚገኙ ቤቶች ውስጥ ሻጋታ እጅግ መስፋፋቱን አንድ የቅርብ ጊዜ ጥናት ያሳያል።

ለመታከም የሚከብድ
ዶክተር ጂል ክሪስታ እንደሚሉት በርካታ ሰዎች ሳያውቁት ለሻጋታ የተጋለጡ ናቸው።
“አብዛኞቻችን እየተመረዝን እንደሆነ እንኳን አናውቅም” ይላሉ ‘ብሬክ ዘ ሞልድ’ የተሰኘ መፅሐፍ ያላቸው አሜሪካዊት ዶክተር።
ይህ የሚሆነው ብዙውን ጊዜ ሻጋታ የሚፈጠረው በማይታዩ ሥፍራዎች በተለይ ከግድግዳ ጀርባ፣ ከቤት ውስጥ ዕቃዎች ሥር ስለሚሆን ነው። ሻጋታ ሳይታይ ለወራት አሊያም ለዓመታት ሊቆይ ይችላል።
ኒኮል እና ዴላኒ ምን እንደተፈጠ ሳያውቁ አንድ ዓመት አልፏቸዋል። ነገር ግን የጤናቸው ነገር እየተባባሰ መሔድ ያዘ።
“ጤናዬ በመቃወሱ ምክንያት ሥራየን ለመልቀቅ ተገደድኩ” ትላለች ኒኮል።
ኒኮል እና ዴላኒ በርካታ ዶክተሮችን ቢጎበኙም የችግራቸውን ምንጭ ማወቅ የሚችል ጠፋ። ድንገተኛ ክፍል ጭምር ገብተው “ደኅና ናቸው” ተብለው ያውቃሉ።
በሻጋታ አማካይነት የሚፈጠር የጤና መቃወስ በሕክምና ለማግኘት ከባድ የሚሆኑ ምልክቶች ከጉንፋን እና ከአለርጂ ጋር ስለሚመሳሰሉ ነው።
የዘርፉ ሰዎች በሻጋታ ምክንያት የሚፈጠር የጤና መታወክ ጉዳቱ ምን ያህል እንደሆነ እና እንዴት መለየት እንደሚቻል ለማወቅ አሁንም ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ።
በርካታ ሰዎች ያለባቸው የጤና ችግር በተለይ ደግሞ የአስም በሽታ በሻጋታ ምክንያት እንደሚባባስ ማወቅ ተችሏል።
በተለይ ሕፃናት ለዚህ ችግር የተጋለጡ ናቸው ይላሉ ዶ/ር ዊታሞር።
ሻጋታን እንዴት ማስወገድ ይችላል?
- በበጋም ሆነ በክረምት ቤታችን ቢያንስ በቀን ለ30 ደቂቃ አየር እንዲያገኝ ማድረግ
- ቤታችን የተወሰነ የሙቀት መጠን [ቴምፕሬቸር] እንዲኖረው ቢደረግ እና ከ18 ድግሪ ቢሆን ይመረጣል
- መፀዳጃ ቤታችን አየር የሚያገኝበት አማራጭ እንዲኖረው ማድረግ
- ምግብ ማብሰል እርጥበት ስለሚፈጠር ለሻጋታ መከሰት ምክንያት ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ኩሽናችን አየር የሚያገኝበት ክፍተት ቢኖረው ይመከራል
- ሻጋታ ስንመለከት ለባለሙያዎች መጠቆም እና እንዲወገድ ማድረግ ተገቢ ነው