አቢ ው ለመጀመሪያ ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገችው በ14 ዓመቷ ነበር።
የምስሉ መግለጫ,አቢ ው ለመጀመሪያ ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገችው በ14 ዓመቷ ነበር

ከ 5 ሰአት በፊት

አቢ ዉ ለመጀመሪያ ጊዜ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደረገችው በ14 ዓመቷ ነበር።

የሆርሞን ሕክምና ከተሰጣት በኋላ በሁለት ወራት ውስጥ ከ42 ኪሎግራም ወደ 62 ኪሎግራም ውፍረቷ ጨመረ።

የድራማ አስተማሪ የሆኑ እናቷ እሷም ድራማ ሠሪ ለመሆን ያደረገችው ውድድር ሲቃረብ “አንቺ ተስፋችን ነበርሽ አሁን ግን በጣም ወፍራም ሆንሽ። ወይ ቶሎ ቀንሺ ወይ ቶሎ ተስፋ ቁረጪ” እንዳሏት ታስታውሳለች።

እናቷ በሆዷ እና እግሯ ላይ ያለውን ሰብ እንድታስወጣ ሆስፒታል ወሰዷት።

“አትፍሪ፤ ከሕክምናው ስትወጭ ቆንጆ ትሆኛለሽ” አሏት።

ማደንዘዣ በከፊል ብቻ ስለተሰጣት ሕክምናው ከባድ ነበር።

“ምን ያህል ስብ እና ደም ከሰውነቴ እንደወጣ አይቻለሁ” ትላለች አቢ። አሁን 35 ዓመቷ ነው።

ግማሽ ሚሊዮን ዶላር አውጥታ ከ100 በላይ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

በማዕከላዊ ቤይጂንግ ውስጥ በቻይና ቀዳሚ የሆነ የቀዶ ሕክምና ተቋም ከፍታለች።

በቅርቡ ፊቷን የሚያቀጥን መርፌ ተወግታለች። ይሄ በየወሩ የምታደርገው ሕክምና ነው።

ፊቷን “ጠንካራ እና ትርፍ ሥጋ የሌለው” ማድረግ እንደምትፈልግ ትናገራለች።

አገጯን ለመቀነስ ሦስት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

እናቷ ከዓመታት በፊት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና እንድታደርግ ማስቻላቸው ትክክል እንደሆነና ምንም የሚጸጽታቸው ነገር እንደሌለ ይናገራሉ።

“ቀዶ ሕክምናው ሠርቷል። በራሴ የምተማመን ደስተኛ ሆንኩ። እናቴ ትክክል ነበረች” ትላለች።

ከገቢ መጨመር እና የማኅበረሰባዊ አስተሳሰብ መለወጥ ጋር በተያያዘ በአንድ ወቅት እምብዛም የማይደገፈው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለፉት 20 ዓመታት በቻይና እየተለመደ መጥቷል።

80 በመቶ ታካሚዎች ሴት ሲሆኑ፣ ዕድሜያቸው በአማካይ 25 ይደርሳል።

በቻይና ባህል ውበት ከፍ ያለ ዋጋ ቢኖረውም ቆንጆ ተብሎ የሚወሰደው መልክ እየተለወጠ መጥቷል።

ምዕራባውያንን ወይም የኬ-ፖፕ ሙዚቃ ታዋቂ ድምጻውያንን አልያም ገጸ ባህሪያትን መምሰል ብዙዎች ይመኛሉ።

ማስታወቂያ
የምስሉ መግለጫ,የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማስታወቂያ

በቅርብ ጊዜ ግን በጣም አደገኛ ነጥብ ላይ በሚያደርስ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በመታገዝ ቆንጆ ተብሎ የሚወሰደውን ገጽታ ለማምጣት እየሞከሩ ያሉ ተበራክተዋል።

ለሕክምናው የሚውለው ኬሚካል ቦቶክስ ከጆሮ ጀርባ እየተሰጠ ነው። ይህም ጆሮ ወደፊት እንዲመጣ የሚያደርግ ነው።

ከዓይን ሥር የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና በማድረግ ‘አኒሜ’ የተባለው የጃፓን አኒሜሽን ፊልም ላይ የሚታዩ ገጸ ባህሪያትን መምሰል እየተለመደ መጥቷል።

የላይኛውን ከንፈር ማሳጠር ከአፍንጫ እና ከንፈር መካከል ያለውን ስፋት ማጥበብም ይጠቀሳል።

እነዚህ ሁሉ ፊልም ላይ ሲታዩ ቢያምሩም በእውነተኛ ሕይወት ላይ ሲደረጉ ግን ከሰው ተክለ ሰውነት ያስወጣሉ።

ሶያንግ (ኒው ኦክስጂን) እና ጌንግሚ (ሞር ቢውቲፉል) የተባሉ የቀዶ ሕክምና ገጾች ታዋቂ ናቸው።

የሰውን ገጽታ አይተው መደረግ ያለበትን የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ምክር ይሰጣሉ።

ታዋቂ እና ተጽዕኖ ፈጣሪዎች እነዚህን ድረ ገጾች ያስተዋውቃሉ። በብዙኃኑ ተቀባይነት ያገኙበት ምክንያትም ይህ ነው።

አቢ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ቻይና ውስጥ እንዲለመድ ካደረጉ አንዷ ናት። ሶያንግ በተባለው መተግበሪያ ላይ እስካሁን ያደረገቻቸውን ቀዶ ሕክምናዎች ታስተዋውቃለች።

ከ100 በላይ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ብታደርግም መተግበሪያው አሁንም “የተሳሳቱ የሰውነት ክፍሎች እንዳሏት እና የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደሚያስፈልጋት” ይጠቁማታል።

“አገጭሽ መስተካከል አለበት ይላል መተግበሪያው። አፍንጫሽን ቀጭን አድርጊውም ብሏል። በድጋሚ አፍንጫዬን የሚያቀጥን የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ላድርግ ይሆን?” ትላለች አቢ።

ብዙዎች ከቀዶ ሕክምና በፊት እና በኋላ የተነሱትን ፎቶ በመተግበሪያው ይለጥፋሉ።

በቻይና የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና የሚፈልጉ ሰዎችን ለማዳረስ ሆስፒታሎች በፍጥነት ይሠራሉ።

አቢ ከቀዶ ሕክምና በፊት
የምስሉ መግለጫ,አቢ ከቀዶ ሕክምና በፊት

“ከፊቴ ሥር አሸዋ የተሸከምኩ ይመስለኝ ነበር”

‘አይሪሰርች’ የተባለው ተቋም ባወጣው ሪፖርት እአአ ከ2019 ወዲህ በቻይና 80 ሺህ ሕገ ወጥ እና 10 ሺህ ሕጋዊ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና መስጫ ድርጅቶች ተከፍተዋል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘም በየቀኑ የሕክምና ስህተቶች እየተፈጠሩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

ሕጋዊ የቀዶ ሕክምና ክሊኒክ ያላቸው ዶ/ር ያንግ ሉ እንደሚሉት የተሳሳተ ቀዶ ሕክምናን ለማረም ሌላ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና የሚያደርጉ ሰዎች ተበራክተዋል።

እነዚህ ሰዎች አገልግሎቱን በሚፈልጉ ሰዎች ቤት ውስጥ ሕክምና የሚሰጡን ጨምሮ ሌሎችም ሕገ ወጥ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ክሊኒኮች ነበር መጀመሪያ ላይ የሄዱት።

የ28 ዓመቷ ዩ ይ በ2020 ያደረገችው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ተበላሸ። ፊቷን ለማወፈር ቆዳዋ ውስጥ የገባው ኬሚካል ጠንካራ ሆኖ ነበር ያገኘችው።

“ከፊቴ ሥር አሸዋ የተሸከምኩ ይመስለኝ ነበር” ትላለች።

ፊቷን ለማስተካከል ደግሞ ያደረገችው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ነገሮችን አባባሰ።

የጠነከረውን ኬሚካል ከማውጣት ይልቅ የፊቷን ቆዳ አሰፉት። ሌላ ክሊኒክ ደግሞ ቆዳዋን ለማጥበብ ጆሮዋ አካባቢ ቆዳዋን ሰበሰበው።

በዚህ ሕክምና ምክንያት ፊቷ የተወጠረ ሆነ።

“መልኬ ጠፋ። ይህም ሥራዬ ላይ ጫና አሳደረ” ትላለች።

ከዶ/ር ያንግ ጋር የተገናኘችው በሶያንግ መተግበሪያ አማካኝነት ነበር።

ከዚህ ቀደም ባደረገቻቸው ቀዶ ሕክምናዎች የተሠራውን ስህተት ለማረም ሦስት ተጨማሪ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና አድርጋለች።

ዶ/ር ያንግ እንደሚሉት ማሻሻያዎቹ ቀዶ ሕክምናዎች ስህተቶቹን እያረሙ ነው።

ዩ ግን “ከዚህ በኋላ ቆንጆ መሆን አልፈልግም” ትላለች።

በየዓመቱ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሳሳተ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ያደርጋሉ።

ሕጋዊ የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ክሊኒኮችም ሕጉን ሙሉ በሙሉ አያከብሩም።

በ2020 ተዋናይቷ ጋዎ ሊዩ በቀዶ ሕክምና ምክንያት አፍንጫዋ ጠቁሯል።

“ፊቴ ላይመለስ ተበላሸ። በጣም አዘንኩ። የትወና ሥራዬንም አጣሁ” ትላለች።

ዶ/ር ሂ ሚንግ የተባለ የአፍንጫ ባለሙያ ቀዶ ሕክምናውን እንደሚሰጣት ቢነገራትም ባለሙያው ገና ፈቃድ ያላገኘ ነበር።

ከዚህ ክስተት በኋላ ክሊኒኩ ተዘግቷል። ባለሙያውም ለስድስት ወራት እንዳይሠራ ታግዷል።

‘ሺስ ታይም’ የተባለው ይህ ክሊኒክ ሲዘጋ በተመሳሳይ አድራሻ ኩዊንግያ የተባለ ክሊኒክ ተፈጥሯል።

ሁለቱ ክሊኒኮች ትስስር እንዳላቸው ቢቢሲ ደርሶበታል።

ዶ/ር ሂ በድጋሚ የአምስት ዓመት ዕግድ ቢጣልበትም በ2024 የሕክምና ፈቃድ አግኝቷል።

አዲስ የተከፈተው ክሊኒክ ከ30 በላይ ቅርንጫፎች አሉት።

ዶ/ር ሂ እና ክሊኒኩም ለቢቢሲ ጥያቄ ምላሽ ባይሰጥም በዩናይትድ ኪንግደም የቻይና ኤምባሲ “የቻይና መንግሥት ክሊኒኮች በአገሪቱ እና በዓለም አቀፍ ሕግ እንዲመሩ ያደርጋል” ብሏል።

ተዋናይቷ አፍንጫዋን ለማስተካከል ሁለት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ብታደርግም አፍንጫዋ እንደቀድሞው ሊሆን አልቻለም።

“በጣም ነው የሚጸጽተኝ። ለምን ያን አደረግኩ?” ትላለች።

የቻይና ብሔራዊ ጤና ተቋም ጠንካራ ሕግጋት በማውጣት እና በመተግበር ከደረጃ በታች የሆኑ ባለሙያዎችን ለማስወገድ እየሞከረ ነው።

አቢ
የምስሉ መግለጫ,የአፍንጫዋ ጫፍ በሕክምናው ምክንያት የጠቆረባት ተዋናይት

ውበት እና የሥራ ዕድል

ውበት በቻይና ሥራ ለማግኘት አስፈላጊ መስፈርት ሆኗል። መልክ የማያስፈልጋቸው ሥራዎች ሲወጡም ውበትን እንደ መስፈርት ያስቀምጣሉ።

ሥራ ፈላጊ ቻይናውያን ሴቶች አማራጭ ስለሌላቸው ወደ ፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ፊታቸውን ያዞራሉ።

በቻንግዱ ግዛት የውበት አማካሪ ለመሆን ሥራ ያመለከተችው ዳን ላን እንደምትለው በተቀጠረች በነጋታው ሥራውን ለመቀጠል የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ማድረግ እንደሚጠበቅባት ተነገራት። በአንድ ሰዓት ውስጥ መወሰን ነበረባት።

ጫና ሲበዛባት ከዓይን በታች ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ተስማማች። 13,000 ዩዋን (የቻይና ገንዘብ) ከፍላ ሦስት ቀዶ ሕክምና አደረገች። ከደሞዟ በላይ ስለከፈለች በዓመት 30 በመቶ ወለድ ያለው ብድር ወሰደች።

ብድሩ “የውበት ብድር” በሚል ዝርዝር ውስጥ ይገኛል።

አቢ እና ሦስት ጓደኞቿ በበኩላቸው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን እንደ በጎ ነገር ያዩታል
የምስሉ መግለጫ,አቢ እና ሦስት ጓደኞቿ በበኩላቸው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን እንደ በጎ ነገር ያዩታል

‘ውብ መሆን እፈልጋለሁ’

ዳን ላን ከቀዶ ሕክምናው በኋላ የሥራ ሕይወቷ ምንም አልተለወጠም። ከአለቃዋ በሚደርስባት ዝልፊያ ምክንያት በተቀጠረች በ10 ቀን ውስጥ ሥራ ለቀቀች።

የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናውን ዕዳ ለመክፈል ስድስት ወራት ወስዶባታል።

ቢቢሲ አይ ወደ 20 የሚሆኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች አነጋግሯል።

ቻንግዱ ግዛት የቀዶ ሕክምናው ማዕከል ሆናለች።

ብዙዎች ለዓመታት የሕክምና ዕዳ ለመክፈል ተገደዋል።

ዳን የተቀጠረችበት መሥሪያ ቤት በመገናኛ ብዙኃን ክስ ቢቀርብበትም አልተዘጋም። አሁንም ድረስ ቁንጅናን መስፈርት አድርጎ ሠራተኞች ይቀጥራል።

የበይነ መረብ ቀጥታ ሥርጭት የሚሠሩ ተቋማት ወጣት ሴቶች ለቀዶ ሕክምና ገንዘብ እንዲበደሩ ጫና ያደርጋሉ። ወጣቶቹ ሴቶች ከፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናው በኋላ ተጽዕኖ ፈጣሪ እንደሚሆኑ ቃል ይገባላቸዋል።

እነዚህ ተቋማት ከቀዶ ሕክምና ክሊኒኮቹ ጋር ስምምነት ስላላቸው ነው ሴቶቹ የፕላስቂክ ቀዶ ሕክምና እንዲያደርጉ ጫና የሚያሳድሩት።

አቢ እና ሦስት ጓደኞቿ በበኩላቸው የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምናን እንደ በጎ ነገር ያዩታል።

ቤይጂንግ በሚገኝ ካፌ ተገናኝተው ፎቶ ይነሳሉ።

ከሰውነታቸው የትኛውን ክፍል እንደሚወዱ ሲጠየቁ መለወጥ የሚፈልጉትን የሰውነት ክፍል ነው የሚጠቅሱት።

አቢ በድጋሚ አፍንጫዋን ማሠራት ትፈልጋለች። ለመጨረሻ ጊዜ አፍንጫዋን ያሠራችው ከስድስት ዓመት በፊት ነበር።

“ብዙ ቀዶ ሕክምና ስላደረግኩ የፊቴ ቆዳ ከዚህ በላይ ሊወጠር አይችልም” ትላለች።

ሆኖም ግን ቀዶ ሕክምና ማድረግ ማቆም አትፈልግም።

“ሁሌም የበለጠ ቆንጆ መሆን እፈልጋለሁ። ቀዶ ሕክምና ማድረግ የማቆም አይመስለኝም” ትላለች።