ኢላን መስክ

ከ 4 ሰአት በፊት

ኢላን መስክ ከትራምፕ አስተዳደር ራሱን ማግለሉን አስታውቋል።

መስክ በሺዎች የሚቆጠሩ የፌዴራል መንግሥት ሠራተኞች የተባረሩበት የዶጅ ንቅናቄ ኃላፊ ነበር። ዶጅ እየተባለ የሚጠራው የአሜሪካ የብክንት ቅነሳ መሥሪያ ቤት ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ሲያገለግል ቆይቷል።

መስክ በማኅበራዊ ሚድያው ኤክስ በኩል በለቀቀው መግለጫ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕን አመስግኗል።

ቢቢሲ እንደተረዳው ዋይት ሐውስ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ ኢላን መስክ የመንግሥት ልዩ መልዕክተኛ የተሰኘ መለያው እንዲነሳ አድርጓል።

የዓለማችን ቱጃሩ ሰው ዶጅን እየመራ እንደማይቆይ እና ኃላፊነቱ ጊዜያዊ እንደሆነ ሲያስታውቅ ቆይቷል።

“ፕሬዝደንት ትራምፕ ብክነትን እንድቀንስ ዕድሉን ስለሰጡኝ አመሰግናለሁ። ነገር ግን ዶጅ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ብሏል።

ደቡብ አፍሪካ የተወለደው ጉምቱ የቴክኖሎጂ ሰው “ልዩ የመንግሥት ሠራተኛ” የሚል ኃላፊነት ተሰጥቶት በዓመት 130 ቀናት እንዲሠራ ተፈቅዶለት ነበር።

ትራምፕ ሥልጣን ላይ ከወጡ ጀምሮ ባለፈው ጊዜ ስሌት መሠረት በያዝነው የፈረንጆቹ ግንቦት ወር መገባደጃ 130 ቀናት ይሞሉታል።

ነገር ግን መስክ በትራምፕ የበጀት ረቂቅ አዋጅ “እንደተከፋ” ባስታወቀ ማግስት ኃላፊነቱን መልቀቁ አነጋጋሪ ሆኗል።

የትራምፕ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በትሪሊ የን ዶላሮች የሚቆጠር የግብር እፎይታ እና የመከላከያ በጀት እንዲጨምር የሚያበረታታ ነው።

የስፔስኤክስ እና ቴስላ ኩባንያዎች ኃላፊ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ከሆነው ሲቢኤስ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ትራምፕ “ትልቁ እና ውቡ” ያሉት አዋጅ የፌዴራል መንግሥቱን ዕዳ ውስጥ የሚከት ነው ብሏል።

አክሎ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ዶጅ ሲሰራ የነበረውን “ሥራ የሚያወርድ” ነው ሲል ተደምጧል።

“አዋጅ ትልቅ ሊሆን ይችላል። ውብም ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በአንድ ጊዜ ሁለቱን ስለመሆኑ ጥርጣሬ አለኝ” ሲል ትችቱን አሰምቷል።

መስክ የትራምፕ አስተዳደርን ሲቀላቀል 2 ትሪሊየን ዶላር ብክነት እቀንሳለሁ ብሎ ነበር የተነሳው። ነገር ግን ይህን ቁጥር ወደ 150 ቢሊዮን ዝቅ አድርጎታል።

በዶጅ ምክንያት ከ2.3 ሚሊዮን የፌዴራል ሠራተኞች መካከል 260 ሺህ የሚሆኑት ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል።

መስክ ባለፈው ሚያዚያ ከመንግሥት ኃላፊነት ገሸሽ ብሎ ትኩረቱን የግል ኩባንያዎቹ ላይ እንደሚያደርግ አስታውቆ ነበር።

ኢላን መስክ የዋይት ሐውስ ልዩ ሠራተኛ ሳለ የቴስላ መኪና ሽያጭ 13 በመቶ አሽቆልቁሏል። የቴስላ የአክሲዮን ገበያም 45 በመቶ ወርዶ እንደነበር ይታወሳል።