
ከ 3 ሰአት በፊት
በዘመናዊ የአፍሪካ ሥነ-ፅሑፍ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ በ87 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።
ላለፉት ስድስት አስርታት በተለይ ኬንያ ከቅኝ ግዛት ወደ ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር የምታደርገውን ጉዞ ሲከትቡ ነበር።
በአፍሪካ ቋንቋ የአፍሪካን ሥነ-ፅሑፍ በመመዝገብ ስማቸው ከሚነሱ ደራሲያን መካከል አንዱ የሆኑት ንጉጊ በርካታ ጊዜ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ ይሆናሉ ተብሎ ቢጠበቅብም ሳያሳካላቸው ቀርቷል።
በአውሮፓውያኑ 1938 ኬንያ በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ሥር ሳለች የተወደሉት ንጉጊ ሊሙሩ በተባለች ከተማ ነው ያደጉት።
ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ አሊያንስ በተባለ በብሪታኒያ ሚሽነሪ የሚመራ አዳሪ ትምህርት ቤት ተማሩ።
በአንድ ወቅት በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከአዳሪ ትምህርት ቤት ሲመለሱ ያደጉበት መንደር በቅኝ ገዢዎች ወድሞ እንዳገኙት አውስተው ነበር።
በማው ማው ንቅናቄ ወቅት ቤተሰቦቻቸው እና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያዊያን በመጠለያ ካምፖች ውስጥ ለመኖር ተገደዋል።
ከአውሮፓውያኑ 1952 እስከ 1960 የቆየው የማው ማው ንቅናቄ የንጉጊን ሕይወትን የዳሰሰ ነበር።
የንጉጊ ወንድም ጊቶጎ የብሪታኒያ ወታደሮችን ትዕዛዝ አልቀበልም ተብሎ ጀርባውን በጥይት ተመትቶ የሞተው በንቅናቄው ወቅት ነበር።
ጊቶጎ የወታደሮችን ትዕዛዝ ያልሰማው መስማት የተሳነው ስለነበር ነው።
በ1959 ብሪታኒያ የኬንያውያንን አመፅ መቋቋም ባቃታት ወቅት ነበር ንጉጊ ለትምህርት ወደ ኡጋንዳ አቅንተው ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲን የተቀላቀሉት።
ማኬሬሬ ዩኒቨርሲቲ ሳሉ በአንድ የፀሐፊያን መድረክ ላይ የመጀመሪያ ልብ-ወለዳቸውን ቅጂ ለታዋቂው ናይጄሪያዊ ፀሐፊ ቺኑዋ አቼቤ አጋርተው ነበር።
አቼቤ ልብ-ወለዱን ዩናይትድ ኪንግደም ለሚገኝ አሳታሚ አስተላልፈው ‘Weep Not, Child’ የተባለው የንጉጊ ታዋቂ ሥራ በ1964 ታተመ።
ታይምስ ጋዜጣ በ1972 ንጉጊን “ከአፍሪካ ታላቅ ዘመናዊ ፀሐፊያን መካከል አንዱ” ሲል ሰይሟቸዋል።
በ1977 ደራሲው የትውልድ ስማቸው የሆነውን ጄምስ ትተው ንጉጊ ዋ ቲዮንጎ ተብለው መጠራት ጀመሩ። ይህን ያደርጉ ከቅኝ ግዛት ጫና ለመላቀቅ እንደሆነ ይነገራል።
ለመጨረሻ ጊዜ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የፃፉት ልብ-ወለድ ‘Petals of Blood’ ይባላል። ከዚህ መፅሐፍ በኋላ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ኪኩዩ ብቻ ለመፃፍ ወሰኑ።
ቅኝ ግዛት በመቃወም የሚታወቁት ንጉጊ አዲሱን የጆሞ ኬንያታ አስተዳደር በመተቸታቸው ለአንድ ዓመት ያክል ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ እንዲታሰሩ ተደረገ።
12 ወራት እስር ቤት በቆዩበት ወቅት በኪኩዩ ቋንቋ የፃፉት ‘Devil on the Cross’ የተሰኘው መፅሐፍ በመጸዳጃ ቤት ወረቀት ላይ እንደፃፉት ይነገራል።
ከእስር ከተለቀቁ ከአራት ዓመታት በኋላ ሊገድሏቸው የሚፈልጉ ሰዎች እንዳሉ በመስጋት በዩናይትድ ኪንግደም እና በዩናይትድ ስቴትስ በስደት ቆይተው ከ22 ዓመታት በኋላ ነው ወደ ኬንያ የተመለሱት።
ወደ ሀገራቸው ሲመለሱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን አደባባይ ወጥተው ተቀብለዋቸዋል። ነገር ግን የተወሰኑ ሰዎች የንጉጊን መኖሪያ ቤት ጥሰው ገብተው ፀሐፊውን ደብድበው ሚስታቸውን ደፍረው ወጡ።
ንጉጊ ወደ አሜሪካ ተመልሰው በዬል፣ ኒው ዮርክ እና ካሊፎርኒያ ኧርቪን ዩኒቨርሲቲ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ አገኙ።
ደራሲው ሁለት ጊዜ አግብተው ፈትተዋል። ንጉጊ ዘጠኝ ልጆች ያሏቸው ሲሆን፣ አራት መፅሐፍ አሳትመዋል።