
ከ 4 ሰአት በፊት
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ለሩሲያው መሪ ቭላድሚር ፑቲን የዩክሬንን ጦርነትን ለማስቆም የሁለት ሳምንት ቀነ ገደብ እንደሰጡ ጠቆሙ።
ክሬምሊን በቅርብ ቀናት ዩክሬን ላይ የሚፈፅመውን ጥቃት አጠናክሮ ቀጥሏል።
በኦቫል ኦፊስ ፑቲን ጦርነቱን ማቆም ይፈልጋሉ ወይ ተብለው የተጠየቁት ዶናልድ ትራምፕ “እሱን ልነግራችሁ አልችልም። ነገር ግን በሁለት ሳምንት ውስጥ ታውቁታላችሁ” ብለዋል።
ትራምፕ ባለፉት ጥቂት ቀናት የሩሲያው አቻቸው ፑቲን ላይ ጠንካራ ትችቶች ሲሰነዝሩ ቆይተዋል።
ካለፈው እሑድ ጀምሮ በማኅበራዊ ሚድያቸው ፑቲን “ፍፁም አብደዋል” እንዲሁም “በእሳት እየተጫወቱ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
ሩሲያ ከሰሞኑ ዩክሬን ላይ እያደረሰች ያለችው የአየር ጥቃት አራተኛ ዓመቱን በያዘው ጦርነት ታይተው የማይታወቁ መሆናቸው እየተነገረ ነው።
ባለፈው ቅዳሜና እሑድ ሩሲያ በዩክሬን መዲና ኪይቭ ላይ ባደረሰችው ጥቃት 13 ሰዎች ሲገደሉ ሕፃናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ሞስኮው ረቡዕ ዕለትም በኪይቭ ላይ የምታደርሰውን ጥቃት አጠናክራ ቀጥላለች።
ትራምፕ የሩሲያው መሪ ፑቲን ጦርነቱን ማቆም ይሻሉ ብለው ያምኑ እንደሆን ለተጠየቁት ጥያቄ “በሁለት ሳምንት አሳውቃችኋለሁ” የሚል ምላሽ ነው የሰጡት።
“በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ፑቲን ከኛ ጋር ነው ወይስ አይደለም የሚለውን እናውቃለን።”
ትራምፕ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ትዕግስታቸው እየተሟጠጠ መሆኑን የሰጡት ምላሽ ይጠቁማል። ዋይት ሐውስ ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማደራደር ያደረገው ሙከራም ውጤታማ አይመስልም።
ትራምፕ በቅርቡ ከፑቲን ጋር ሁለት ሰዓታት የዘለቀ የስልክ ውይይት ማድረጋቸውንና ውይይታቸውም “መልካም” እንደነበር ማስታወቃቸው አይዘነጋም።
ፑቲን በስልክ ልውውጡ ወቅት ከዩክሬን ጋር “ወደፊት የሰላም ስምምነት ለመፍጠር” ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ የስልክ ልውውጥ ከአንድ ሳምንት በኋላ ነው ሩሲያ በመቶዎች የሚቆጠሩ ድሮኖች እና ደርዘን የሚሆኑ ሚሳዔሎችን ወደ ኪይቭ የተኮሰችው።
ምንም እንኳ ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በተደጋጋሚ እርምጃ እንደሚወስዱ ቢያስጠነቅቁም እስካሁን ተጨባጭ የሆነ ነገር አልታየም።
የትራምፕ አስተዳደር እየተከተለ ያለው መንገድ ክሬምሊን የበለጠ እንዲጠናከር እያደረገ ነው የሚል ትችት ይቀርብበታል።
ረቡዕ ዕለት የጀርመኑ መራሔ መንግሥት ፍሬድሪክ ሜርዝ ለኪይቭ ረዥም ርቀት የሚጓዝ ሚሳዔል እንደሚሰጡ ለዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሞተዋል፤ የሀገሪቱ ምስራቃዊ እና ደቡባዊ ክፍል ወድሟል።
ሩሲያ ክሬሚያን ጨምሮ የዩክሬንን አንድ አምስተኛ ክፍል ትቆጣጠራለች።