ሐኪም

29 ግንቦት 2025, 13:29 EAT

የደሞዝ፣ የጥቅማ ጥቅም እንዲሁም ሌሎች ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ በመጠየቅ የሥራ ማቆም አድማ ከመቱ ሦስት ሳምንታት የሆናቸው የጤና ባለሙያዎች ግንቦት 15/2017 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

‘የኢትዮጵያ ጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ’ በሚል ማዕቀፍ የሚታወቁት ባለሙያዎቹ “ብሶት” ያሰባሰባቸው እንደሆኑ ገልፀው፤ ባለፈው ሚያዝያ የኑሮ እና የሥራ ሁኔታቸው እንዲሁም የአገሪቱ የጤና ሥርዓት እንዲሻሻል 12 ጥያቄዎችን ለመንግሥት አቅርበዋል።

ባለሙያዎቹ ከመንግሥት ምላሽ ባለማግኘታቸው ከግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ አገራዊ የሥራ ማቆም ማድረጋቸውን ያሳወቁ ሲሆን፤ እስራትን ጨምሮ ከሥራ መባረር እና ጫናዎች እየደረሰባቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

ሥራ ማቆም አድማውን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ ግዙፍ ሆስፒታሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ማስታወቂያዎችን አውጥተዋል።

የባለሙያዎችን ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሠራ፤ ነገር ግን ሥራ ማቆሙ “ተቀባይነት” እንደሌለው ሲገልፅ የነበረው ጤና ሚኒስቴር፤ ባለፈው ሳምንት አርብ ለመጀመሪያ ጊዜ ከንቅናቄው አስተባባሪዎች ጋር መነጋገሩ ታውቋል።

አራት ሰዓታትን የፈጀው ንግግር በሚኒስቴሩ ጥሪ የተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ የተናገሩ የንቅናቄው አስተባባሪ እና በንግግሩ የተሳተፉ አንድ ሐኪም፤ አራት ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጣቸውን ተናግረዋል።

የታሰሩ የጤና ባለሙያዎች እንዲፈቱ፣ ከሥራ የተባረሩ ባለሙያዎች እንዲመለሱ፣ ማስፈራሪያ እና ዛቻ እንዲቆም እንዲሁም የጤና ተቋማት እያወጧቸው ያሉትን አዳዲስ የቅጥር ማስታወቂያዎችን እንዲያቋርጡ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች ማቅረባቸውን ገልፀዋል።

የጤና ሚኒስትሯ፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች፣ አማካሪዎች እና ሌሎችም የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት በዚህ ንግግር፤ የባለሙያዎቹ ጥያቄ “እውቅና” ማቅኘቱን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ ጥያቄዎቹን በምን መልኩ እንመልስ የሚለው ላይ ግን ልዩነት መፈጠሩን ገልፀዋል።

በጤና ሚኒስቴር በኩል “የእኛን ፕሮፖዛል ተቀበሉ” የሚል ሀሳብ መቅረቡን የጠቆሙት ተሳታፊው፤ ምንም እንኳ ከመንግሥት በኩል የቀረበውን ሀሳብ ይዘት ከመግለፅ ቢቆጠቡም ባለሙያዎቹን “አላሳመነንም” ብለዋል።

ይህ ንግግር በተደረገ በሰዓታት ልዩነት በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ የቀረቡት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጄ ዱጉማ፤ የባለሙያዎቹ ጥያቄ ለረጅም ጊዜ ሲንከባለል የመጣ “ውዝፍ” መሆኑን አንስተው ወደ ሥራቸው የማይመለሱ ባለሙያዎች ላይ የሙያ ፈቃድ እስከ መንጠቅ የደረሰ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።

ሐኪም

የንቅናቄው አስተባባሪ በመንግሥት በኩል ይበልጥ ጫናው መበርታቱን በመጠቆም፤ ለሁለተኛ ዙር ንግግር እንዳልተቀመጡ ተናግረዋል።

“አሁንም ማስታወቂያዎች ይወጣሉ፣ ማስፈራሪዎዎች፤ ዛቻዎች አሉ፣ ባለሙያዎቻችን እስር ቤት ነው ያሉት፤ አብዛኞቹ አልተፈቱም። ይህ ባለበት ሁኔታ ድርድር ለማድረግ ከባድ ሆኖ አግኝተነዋል” ብለዋል።

ሌላ የንቅናቄው አስተባባሪ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ሦስተኛ እና ገለልተኛ ወገን ሆኖ እንዲያደራድር “ቅድመ ውይይት” እየተደረገ መሆኑንም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ መንግሥት ለጥያቄዎች ትኩረት ሰጥቶ ግልጽ እና አሳታፊ በሆነ መንገድ መፍትሔ እንዲሰጥ እና ባለሙያዎቹም ጥያቄዎቻቸውን የኅብረተሰቡን የጤና እና በሕይወት የመኖር መብቶችን አደጋ ላይ በማይጥል መልኩ እንዲያቀርቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በመሀል ገብቶ ለማደራደር “ተነሳሽነቱ” ከኮሚሽኑ መምጣቱን የጠቆሙት አስተባባሪው፤ በመንግሥት በኩል ለመነጋገር ፍላጎት ቢታይም ከቃል በላይ ተግባራዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።

መንግሥት እና የጤና ባለሙያዎቹ ‘ተደራዳሪ ቡድን’ በሦስተኛ ወገን በኩል ፊት ለፊት ለመነጋገር ቀን ባይቆረጡም በቅርቡ እንደሚገናኙ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ ባለሙያዎቹ መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን ተንተርሰው የቁርጠኝነት ጥርጣሬ እንዳደረባቸው አልደበቁም።

“ግልፅ የሆነ መልስ መስማት እንፈልጋል። የቆምነው ለሕዝብ እስከሆነ ድረስ ከ12ቱ ጥያቄዎች በፊት አራቱ ጥያቄዎች እስካሁን አለመመለሳቸው እንኳ የቁርጠኝነት ጥያቄ ውስጥ ከቶናል” ብለዋል።

በአገሪቱ ካሉ ከ320 ሺህ በላይ የጤና ባለሙያዎች ውስጥ “ከ65 እስከ 75 በመቶ” ይሆናሉ የተባሉት ባለሙያዎች በንቅናቄው እየተሳተፉ እንደሆነ አስተባባሪዎቹ ተናግረዋል።

ምንም እንኳ መንግሥት ለሳምታት የጤና ተቋማት ሥራ አልተስተጓጎለም ቢልም፤ የጤና ተቋማቱ ላይ የተፈጠረውን ጫና የሚያሳዩ የደብዳቤ ልውውጦች እና ማስታወቂያዎች ግን በስፋት እየወጡ ነው።

የሥራ ማቆም አድማው “ትልቅ ጉዳት እያመጣ እንደሆነ እንገነዘባለን” ያሉ አንድ አስተባባሪ፤ “[ታካሚዎች] ብዙዎቹ አገልግሎት እያገኙ አይደለም። ቀጠሯቸው እየተራዘመ ነው። ላላስፈላጊ ወጪ እየተዳረጉ ነው ያሉት። ማኅበረሰቡ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ነው እየፈጠረ ያለው” ብለዋል።

ባለሙያዎቹ ታካሚዎች እና የጤና ሥርዓቱ ላይ ለሚደር ጫና ኃላፊነቱን የሚወስደው መንግሥት እንደሆነ ደጋግመው ተናግረዋል።

ከዚሁ የሥራ ማቆም አድማ ጋር በተያያዘ ባለፉት ሳምንት ውስጥ ከ80 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች ለእስር የተዳረጉ ሲሆን፣ ዘጠን ባለሙያዎች ደግሞ በፖሊስ ክስ ተመስርቶባቸው ፍርድ ቤት ቀርበው የቀጠሮ ጊዜ እንደተሰጠባቸው ይታወቃል።