
29 ግንቦት 2025
በደቡብ አፍሪካ የስድስት ዓመት ልጇን አግታ ሸጣታለች የተባለችው እናት ከሁለት ግብረ አበሮቿ ጋር የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደባት።
ኬሊ ስሚዝ በተባለችው እናት እንዲሁም የወንድ ጓደኛዋ ዩአኪን አፖሊስ እና ጓደኛቸው ስቴቨኖ ቫን ራየን የእድሜ ልክ እስራት የተበየነው ጆሽሊን ስሚዝ የተባለችው ህጻን በኬፕታውን አቅራቢያ ከሚገኘው ቤቷ ደብዛዋ ከጠፋ ከአንድ ዓመት በኋላ ነው።
የጆሽሊን መጥፋት በደቡብ አፍሪካውያን ዘንድ አነጋጋሪ ቢሆንም እስካሁን አልተገኘቸም።
የፍርድ ሂደቱ ስድት ሳምንታትን የወሰደ ሲሆን የበርካታ ደቡብ አፍሪካውያንን ቀልብ የሳበ እንዲሁም ምስክሮች እና አቃብያነ ህግ በርካታ አስደንጋጭ ክስተቶችን ይፋ ያደረጉበት ነው።
ዳኛው ናታን ኢራስመስ ሶስቱን ተከሳሾች ያለምንም ልዩነት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባቸዋል።
“በህገወጥ የሰዎች ማዘዋወር ወንጀል ክስ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶባችኋል። በተከሰሳችሁበት የእገታ ክስ አስር ዓመት ተበይኖባችኋል” በማለት ዳኛው ጮክ ብለው ሲናገሩ በችሎቱ ደማቅ ጭብጨባ ተሰምቷል።
ዳኛው ብያኔያቸውን ለማስተላለፍ ከአንድ ሰዓት በላይ የወሰዱ ሲሆን በዚህም ወቅት በፍርድ ሂደቱ ነጥረው የወጡ ጉዳዮችን በመጥቀስ እንዲሁም ማጠቃለያቸውን አሰምተዋል።
ሶስቱ ተከሳሾች ምንም አይነት ጸጸት አላሳዩም በሚል በከፋ ወቅሰዋቸዋል።
“እነዚህ ግለሰቦች የሚጸጸቱ አይደሉም። ያነሰ ቅጣትም ለመፍረድ ምክንያት አላገኘሁም” ብለዋል።
የግለሰቦቹ ተግባር ልጅቷ በምትኖርበት ሚዴልፖስ ማህበረሰብ ላይ ያሳደረውን ተጽእኖ የተናገሩት ዳኛው ማህበራዊ ትስስሩን “አፈራርሶታል” ብለዋል።

የህጻኗ መምህር በበኩላቸው በፍለጋው ወቅት ልጇ “በኮንቴይነር ውስጥ በመርከብ ወደ ምዕራብ አፍሪካ እያቀናች ነው” ስትል እናቲቱ መናገሯን ለችሎቱ ገልጸው ነበር።
የኬሊ ስሚዝ ጓደኛ እና ጎረቤት የሆኑት የአቃቤ ህግ ምስክር ሎረንቲያ ሎምባርድ አስደንጋጭ የሚባሉ መረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ መናገራቸው ተዘግቦ ነበር።
ለችሎቱ ምስክርነተቻውን የሰጡት ጎረቤት የጆሽሊን መጥፋት በደቡብ አፍሪካ ሳንጎማ ተብለው ከሚታወቁት የባህል ሐኪሞች ጋር ይገናኛል ብለዋል።.
ጓደኛዋ “አንድ የቂል ነገር አደረግኩኝ። ልጄን ለሳንጎማ ሸጥኳት” ስትል ገንዘብ ለማግኘት አማራጭ በማጣቷ ያደረገችው እንደሆነ ነግራኛለች ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።