
የጽሁፉ መረጃ
- ፀሐፊ,ዮጊታ ሊማዬ
- የሥራ ድርሻ,ቢቢሲ ኒውስ
- 29 ግንቦት 2025
ሮዲኒሲኪ ወደ ተሰኘችው የዩክሬን አንስተኛ ከተማ ስንደርስ የከባድ ጦር መሳሪያዎች ተተኳሽ ሽታ ነበር የተቀበለን። ወደ ከተማው እያሽከረከርን ስንዘልቅ ያ ሸታ ከየት እንደሚመጣ ማወቅ ቻልን።
250 ኪሎ ግራም የሚመዝነው ቦምብ የከተማዋ ዋነኛ የአስተዳደር ህንጻን አውድሞ ሦስት አነስተኛ የመኖሪያ ፎቆችን አፍርሷል።
ከስፍራው የደርሰነው ከዚህ ጥቃት አንድ ቀን በኋላ ቢሆነም ከፍርስራሾች ውስጥ ጭሶች ሲወጣ ይታያል። በከተማዋ መውጪያ ደግሞ የመድፍ እና የጥይት ደምጾች ይሰማሉ። ይህ ድምጽ የዩክሬን ወታደሮች ድሮኖችን መትተው ሲጥሉ የሚፈጠር ነው።
ሮዲኒሲኪ ከፍተኛ ፍልሚያ ከሚካሄደባት ፖክሮቭክ ከተማ በ15 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።
ሩሲያ ሮዲኒሲኪ ከተማን ለመቆጣጠር ለወራት ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች። ሆኖም የዩክሬን ጦር እስካሁን የሩሲያ ወታደሮች ወደ ከተማዋ እንዳይዘልቁ መከላከል ችለዋል።
እናም ሩሲያ የጦር ስልት ቀይራለች። ከተማውን ከመክበብ ወደ ከተማው የሚገቡ መጋቢ መንገዶችን ወደ መቁረጥ ተሸጋግራለች።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ሰላም ለማምጣት እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬ አላፈራም። በዚህ መሃል ሩሲያ ካለፈው ጥር ወር ወዲህ እጅግ ወሳኝ የተባሉ ድሎችን እያገኘች ነው።
በሮዲኒሲኪ ይህንን የሚያረጋግጥ እውነት አይተናል።
ወደ ከተማዋ በገባን በደቂቃዎች ውስጥ በላያችን ላይ የሚቋርጡ የሩሲያ ድሮኖችን ደምጽ ሰማን። የዘጋቢ ቡድናችን በቅርብ ወደ ሚገኝ መሸሸጊያ ተራወጠ። በቅርብ ያገኘነው መሸሸጊያ ዛፍ ነበር።
እንቅስቃሴያችንን ከድሮኑ በተቃራኒ በማድረጋችን ዒላማ ውስጥ አልገባንም። ብዙም ሳይቆይ ሁለተኛ ድሮን ጥቃት ፈጽሞ ከፍተኛ የፍንዳታ ድምጽ ተሰማ። ከእኛ በላይ ያለው ድሮን ግን ቅኝቱን ቀጥሏል። ለተጨማሪ ጥቂት ደቂቃዎች በጦርነቱ አውዳሚ ከሆነው መሳሪያ የሚመጣውን ያንን እጅግ የሚረብሽ ድምጽ ደጋግመን ሰማነው።
ያ ድምጽ ሲጠፋ ጠንካራ ከለላ ወደምናገኝበት ስፍራ መሮጥ ጀመርን። በግምት ከሰላሳ ሜትር ርቀት በኋላ አገልግሎት የማይሰጥ አንስተኛ የመኖሪያ ህንጻ አግኝትን ገባን።
እዚህ ህንጸ ውስጥ ተሸሽገን የድሮኑን ድምጽ በድጋሚ ሰማነው። ምን አልባት እንቅሰቃሴያችንን ተገንዝቦ የተመለሰ ሊሆን ይችላል።
ሮዲኒሲኪ በሩሲያ ድሮኖች ተወራለች። የዚህ ማረጋገጫው ደግሞ በከተማ ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች መነሻ ከሚታወቀው የሩሲያ የጥቃት መሰንዘሪያ ቦታዎችም እጅግ የቀረቡ ናቸው። እነዚህ ጥቃቶች ሩሲያ በቅርቡ ከተቆጣጠረቻቸው የዩክሬን ግዛቶች የሚነሱ ሊሆኑ ይችላሉ።
በተሸሸግንበት ህንጻ ለ30 ደቂቃ ያህል ከቆየን በኋላ የድሮኑ ድምጽ ሲጠፋ በፍጥነት ወደ መኪናችን አመራን። መኪናችን በዛፉ ሥር ቆማ ነበር። በከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከርን ከተማዋን ለቀን መውጣት ጀመርን። በመንገዳችን ላይ ጭስ እና እሳት እየተመለከትን ነበር። ምናልባት ተመተው የወደቁ ድሮኖች ሊሆኑ ይችላሉ።
ከጦርነቱ አውደማ እየራቀን ጉዟችንን ወደ ባይሊስክ ከተማ አደርገን። በመንገዳችን በአንድ ጀምበር በሚሳዔል ጥቃት የወደሙ በርካታ ቤቶች ይታያሉ። ከእነዚህ ቤቶች መካከል የ61 ዓመቷ ስቬትላና ቤት ይገኝበታል።
“ሁኔታዎች ከድጡ ወደ ማጡ እየሆኑ ነው። በፊት የፍንዳታ ድምጽን የምንሰማው በርቀት ነበር። አሁን ግን የእኛ ከተማም የጥቃት ዒላማ እየሆነች ነው። በሩቅ ስንሰማው የነበረው ደምጽ በራችን ላይ ደርሷል” ይላሉ።
ሉስኪሊ ስቬትላና ጥቃት ከደረሰበት ቤታቸው ቁሶችን ሲያነሱ ነበር ያገኘናቸው። ጥቃቱ ሲፈጸም ቤት ውስጥ አልነበሩም።
“እስኪ ወደ መሃል ከተማ ጎራ ብላችሁ ተመለከቱ። ከዚህ የባሰ ውድመት ታያላችሁ። ዳቦ ቤቶች እና መካነ እንስሳት ሳይቀር ወድመዋል” ሲሉ አክለዋል።
የድሮኖች ዕይታ እና ጥቃት ወደ ማይደርሰበት ቦታ ሆነን የአምስተኛ ብርጌድ መድፈኛ ወታሮችን አገኘን። ከወታደሮቹ መካከል ሴሪ ስላሉበት ሁኔታ አስረዳን።
“የሩሲያ ጥቃት እየጨመረ እንደመጣ ይሰማቹኋል። ወደ ከተማዋ ሚገቡ መጋቢ መንገዶችን ለመቁረጥ ሮኬት፣ ሞርታር፣ ድሮን ጨምሮ ያላቸውን ሁሉ እየተጠቀሙ ነው” ይላል።
የብርጌዱ አባላት ወደ ሥምሪታቸው ቦታ ለመድረስ የተፈጥሮ ከለላል ለማግኘት ሦስት ቀናት መጠበቅ ነበረባቸው።
ከድሮን ዕይታ ውጪ ለመሆን ደመና ወይም ከባድ ንፋስ እስኪመጣ ነበር የጠበቁት።
ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት ጦርነት ውስጥ ተሳትፈው የማያውቁት ወታደሮች በከፍተኛ ፍጥነት ከሚቀያየሩ የጦርነት ቴክኖሎጂዎች ጋር መላመድ ግድ ሆኖባቸዋል። እኛ በተገኘንበት ወቅት አዲሱ ቴክኖሎጂ ‘የፋይበር ኦብቲክ’ ድሮን ነበር።

‘የፋይበር ኦብቲክ’
‘የፋይበር ኦብቲክ’ ድሮን ‘ጭራ’ ላይ በ10 ኪሎ ሜትሮች የሚቆጠሩ ገመድ ይጠመጠምባቸዋል። በሌላኛው ጫፍ ድግሞ ድሮኑን ከሚቆጣጠረው መሳሪያ ጋር ይገናኛሉ።
“ወደ ድሮኑ የሚመጣውም ይሁን ከድሮኑ የሚወጣው ቪዲዮ እና የቁጥጥር ሲግናል የሚተላለፈው በኤሌክትሪክ ገመዱ (ኬብል) አማካኝነት እንጂ እንደሌላው ድሮን በሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ አይደለም። ይህ ማለት በኤሌክትሮኒክ የመከላከያ ሥርዓት የድሮኑን ጉዞ ማጨናገፍ አይቻልም ማለት ነው” ሲል አንድ የዩክሬን ድሮን መሃንዲስ ነግሮናል።
በጦርነቶች ወቀት ድሮን በስፋት ጥቅም ላይ ሲውሉ ተዋጊ ኃይሎች በቴክኖሎጂ ድሮን መግታት የሚያስችል ሥርዓቶችን ይጠቀማሉ።
ታዲያ ሩሲያ የታጠቀችው የፋይበር ኦፕቲክ ድሮን ይህንን ሥርዓት መና ያስቀረዋል። ዩክሬንም ይህንን ቴክኖሎጂ ለማምረት እየሠራች ነው።
“ሩሲያ ይህንን ድሮን ከእኛ በፊት በተሻለ ሁኔታ መጠቀም ጀምራለች። እኛ ግን ገና በሙከራ ደረጃ ላይ ነን። ይህ ዓይነቱ ድሮን ከተለመደው ድሮን ከፍታ በታች ዝቅ ብለን መጠቀም ላለብን ቦታዎች አንገለገልበታለን። ወደ ቤት ውስጥ ገብትን ዒላማዎችን ልንመለከትበት ሁሉ እንችላለን” ሲል ቬኒያ የተባለው የዩክሬን የድሮን ባለሙያ ተናግሯል።
“ይህንን ድሮን ለማጨናገፍ መቀስ መታጠቅ አለብን እያልን መቀለድ ሁሉ ጀምረናል” ሲል መደፈኛው ሴሪ ይናገራል።
ፋይበር ኦፕቲክ ድሮኖች እንከን አልባ ግን አይደሉም። ፈጥነታቸው ዝግ ያለ መሆኑ የመጀመሪው ችግር ተብሎ የሚጠቀስባቸው ነው።
ሌላው ገመዳቸው ዛፍ ወይም ሌላ አካል ላይ ሊጠመጠም ይችላል። የሆነው ሆኖ ሩሲያ እነዚህ ድሮኖች በስፋት ጥቅም ላይ ማዋሏን ተከትሎ ወታደሮች ከቦታ ቦታ ሲዘዋወሩ ከጦር ሜዳ የበለጠ እልቂት እየገጠማቸው ነው።
“ወደ ተመደብሽበት ቦታ ስትጓዢ በዕይታ ውስጥ መሆን አለመሆንሽን አታውቂም። እናም ዕይታ ውስጥ ሆነሽ አንቺ ሳታውቂ ለሰዓታት ሥራሽን ትቀጥያለሽ” ሲል ኦልስ የተባለው የዩክሬን ጦር ባልደረባ ይናገራል።
ይህ ፍይበር ኦፕቲክ ድሮን የደቀነው ስጋት ወታደሮች በሥምሪታቸው ቦታ ላይ ከሚገባው በላይ እንዲቆዩ እያደረገ ነው።
ይህ በመሆኑ ጋዜጠኞች ወደ ሥፍራው ማቅናት ከባድ ይሆንባቸዋል። እኛም ኦልስን እና ማክሲምን ወታደሮች እረፍት በሚወስዱበት ገጠራማ ቦታ ላይ በሚገኝ ድንኳን ውስጥ አግኝተን ነበር ያዋራናቸው።
“በአንድ የሥምሪት ቦታ ላይ እስከ 31 ቀን ቆይቻለሁ፤ ይህ የእኔ ረዥሙ ጊዜ ነው። ነገር ግን ከ90 እስከ 120 ቀን አንድ ቦታ ላይ የቆዩ ወታደሮች እንዳሉ ሰምቻለሁ። እነዚያ የፋይበር ኦፕቲክ ድሮኖች ከመምጣታቸው በፊት አንድ ቦታ ከ3 እስከ 7 ቀን ነበር የምንቆው” ይላል ማክሲየም።
ኦልስ ሩሲያ የጦርነት ስልት ለውጥ እያደረገች ነው ሲል ይገልጻል።
“ቀደም ብሎ የሚያጠቁት በቡድን ነበር። አሁን አንድ ወይም ሁለት ሰው ነው የሚላከው። አንዳንዴ ሞተር ሳይክል ይጠቀማሉ። አልፎ አልፎም ሳይክል ሊጠቀሙ ይችላሉ” ሲል ያስረዳል።
ይህ ማለት በአንዳንድ ቦታዎች በጦር አውድማ የሚደረጉ የፊት ለፊት ውጊያዎች እጅግ እየቀነሱ መጥተዋል ማለት ነው።
ይህ ሁኔታ ሁለቱም ኃይሎች ወደፊት ለመገስገስ አስቸጋሪ እንዲሆንባቸው አደርጓል።
ሩሲያ በቅርብ ጊዜያት ድል እያገኘች ቢሆንም ፖክሮቮስክ የምትገኝበትን የዶንቴስክ ግዛት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር በቅርቡ ወይም በቀላሉ የሚሳካላት አይደለም።
ዩክሬን ወደ ኋላ እያፈገፈገች ነው። በትግሉ ለመቀጠል የጦር መሳሪያ ድጋፍ ትፈልጋለች።
ይህ ጦርነት ወደ አራተኛው ክረምት እየተሸጋገረ ነው። የዩክሬን የሰው ኃይል ከሩሲያ ጋር ሲነጻጸር ዝቅ ያለ መሆኑም ነገሮችን አስቸጋሪ አደርጎታል።
እኛ ያገኘናቸው አበዛኞቹ ወታደሮች የዩክሬን ጦር ኃይልን የተቀላቀሉት ከጦርነቱ በኋላ ነው። ሥልጠና የወሰዱት ለአጭር ጊዜ ቢሆኑም በጦርነቱ ብዙ እየተማሩ ነው።
ማክሲም ጦሩን ከመቀላቀሉ አስቀድሞ በአንድ የመጠጥ አምራች ኩባንያ ውስጥ ይሠራ ነበር። አሁን ቤተሰቦቹ በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንዳሉ ጠየኩት።
“በጣም አስቸጋሪ ነው። የምር ከባድ ነው። ቤተሰቦቼ እኔን ይደግፉኛል። የሁለት ዓመት ልጅ አለኝ እሱን በደምብ የማይበት ጊዜ አልነበረኝም። በቪዲዮ አናግረዋለው። ስለዚህ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሁሉም ነገር መልካም እንደሆነ ሁሉ እየኖርኩ ነው” ብሎ ሲመልስልኝ ዓይኑ በእንባ ተሞልቶ ነበር።